ፕሮፌሰር ባዬ ይማም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን እና የቋንቋ ተመራማሪ እና አስተማሪ ናቸው:: ኘሮፌሰር ባዬ ሥነ ልሳን እና ቋንቋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ45 ዓመታት አስተምረዋል:: ብዝሃ ቋንቋ ባላት ሀገራችን ውስጥ የግዕዝ ቋንቋ እና ሌሎች ቋንቋዎችን መማር ምን ጥቅም እንዳለው እና ለሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውናል::
መልካም ንባብ!
የግዕዝ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?
ጠቅለል ባለ አገላለፅ የግዕዝ ቋንቋ ለኢትዮጵያ የቅርሶቿ፣ የእድገቷ እና የሁለንተናዋ መገለጫ ነው::
ቋንቋን መማር ለምን እና ለማን ይጠቅማል?
የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ መማር እና ማስተማር ጥቅም እንጂ አንዳችም ጉዳት የለውም:: ቋንቋ ለየትኛውም ሰው ሆነ ማኅበረሰብ የመገናኛ መሣሪያው ነው፤ ይህንን መሣሪያ ለግንኙነት መጠቀም አልፈልግም የሚል ሰው ካለ ጤነኛነቱ ያጠራጥራል:: ማንኛውንም ቋንቋ መማሩ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ካልን ደግሞ ግዕዝንም መማር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም::
ሕጻናት ግዕዝና ሌሎች ቋንቋዎችን መማር ያለባቸው በየትኛው የእድሜ እርከን ላይ ነው?
ሕፃናት ከተወለዱበት ዕለት ጀምሮ ቋንቋን የማወቅ ችሎታ አላቸው:: ችሎታ ብቻ ሳይሆን መብትም አላቸው:: ሕፃናት ቋንቋን የማወቅ መብት የሚኖራቸው ሲያድጉ በዚያ ቋንቋ ስለሚጠቀሙበት ነው:: ሕፃናት በሕፃንነት ማወቅ የሚጀምሩትን ቋንቋ ካደጉ በኋላ ከቋንቋው ተናጋሪዎች በመስማት እና ለመናገር በመሞከር ይበልጥ ያበለፅጉታል:: ሕፃናት ቋንቋን ይበልጥ መልመድ የሚችሉት በተወለዱ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ነው::
ሕፃናት የግዕዝ ቋንቋን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የማወቅ ዕድል የላቸውም፤ ይህ የሆነው ደግሞ ግዕዝን በአፈ ፈትነት የሚናገሩ እናት እና አባት ወይም ማኅበረሰብ ባለመኖሩ ነው:: የሕፃናቱ እናት እና አባት ሊናገሩ የሚችሉት አማርኛ፣ ኦሮሞኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጌኛ ወይም ሌላ ቋንቋ ነው:: ሕፃናቱም ሊያውቁት የሚችሉት ያሉበት ማኅበረሰብ የሚናገራቸውን ቋንቋዎች ብቻ ነው::
ግዕዝን ጨምሮ ሀገር በቀል እውቀቶችን በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ አካትተን መጠቀሙ ምን ጥቅም ይኖረው ይሆን?
ማንኛውንም ቋንቋ ማወቅ እና መማር ይጠቅማል እንጂ አይጐዳም:: እንደ ኢትዮጵያ ባለች ባለ ብዙ ቋንቋ ሀገር ውስጥ ሁሉንም ቋንቋዎች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካትቶ ተማሪዎች እንዲማሯቸው ማድረግ በመርህ ደረጃ ጥሩ ነው:: በተግባር ደረጃ ግን ያስቸግራል:: ምክንያቱ ደግሞ የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት አቅም ይህንን ለማድረግ ስለማያስችል ነው::
ለዚህ ሁሉ ቋንቋ መምህራንን ማሰልጠን፣ ለዚህ ሁሉ ቋንቋ የትምህርት ሥርዓት ቀርፆ፣ መጽሐፎች አሳትሞ እና ሌሎችንም በርካታ ወጪዎች አውጥቶ ቋንቋዎችን ማስተማሩ ይቸግራል::
ሕፃናት ብዙ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች የሀገር እና የክልሎች አቅም በሚፈቅደው ልክ ቢማሯቸው ይጠቀማሉ:: እያንዳንዱ ቋንቋ ዓለምን ማየት የሚያስችል መስኮት በመሆኑ ለሕፃናት እነዚህን መስኮቶች መክፈት ያስፈልጋል:: እነዚህን መስኮቶች በሕፃናት ላይ መዝጋቱ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው::
የግዕዝ ቋንቋ በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው ለምን ይሆን?
ግዕዝ የኢትዮጵያ ሁለመና የሚገለፅበት ቋንቋዋ ነው:: የኢትዮጵያ ማዕድኖቿ፣ ማኅበራዊ መዋቅሯ፣ አሥተዳዳራዊ ሥርዓቷ፣ ታሪኳ፣ ሀይማኖቷ፣ ፍልስፍናዋ እና ሌሎችም እሴቶች በግዕዝ ይገለፃሉ:: ግዕዝ ተናጋሪ ማኅበረሰብ የሌለው የኢትዮጵያ የፅሑፍ ቋንቋ ነው::
ይህ ቋንቋ ምንም እንኳን ተናጋሪ ማኅበረሰብ ባይኖረውም የኢትዮጵያ ውስጠ ሚስጥር የሚገኘው በዚሁ የፅሑፍ ቋንቋ ውስጥ ነው፤ በብራናዎቹ ውስጥ ነው::
ከቅድመ ክርሥትና፣ ከይሁዲ ዘመን እና ከክርስትና ጀምሮ ባለው ዘመን እና እስከ መካከለኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ነገሯ የተከተበው በብራና ላይ እና በግዕዝ ቋንቋ ነው:: እነኚህን በግዕዝ ቋንቋ ብራና ላይ ያረፉ የኢትዮጵያ ምስጢራት ፈልጐ በማግኘት የትላንቷን፣ የዛሬዋን እና የነገዋን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መተለም ይቻላል::
በፅሑፋዊው የግዕዝ ቋንቋ ውስጥ የሚገኘው ሃይማኖት እና ፀሎት ብቻ ከመሰለን ተስትተናል:: በግዕዝ ውስጥ እውቀቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሥነ ጥበብ፣ መድሃኒት እና ሌሎችም በርካታ ነገሮች ይገኙበታል:: እነዚህን ጠቃሚ ነገሮች ከኛ ይልቅ የውጪ ዜጐች አውቀዋቸው ግዕዝን ከኛ በተሻለ እያስተማሩት እና እየተጠቀሙበት ይገኛሉ::
ባለ ብዙ ሀብቱ ግዕዝ በውጭ ሀገራት በትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደ አንድ ትምህርት መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን እኛ የግዕዝ ባለቤት የሆንነው ኢትዮጵያዊያንም የራሳችንን ግዕዝ ብዙ ብር እየከፈልን በውጭ ሀገር እንማረዋለን:: ግዕዝ የሚጠቅመው ለኛ ለኢትዮጵያዊን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር ነው፤ የላቲን ጠቀሜታም ለሮማዊያን ብቻ አይደለም:: እብራይስጥኛ፣ አረብኛ ወይም ሌሎችም ቋንቋዎች የተፈጠሩት ለሰው ልጆች መጠቀሚያነት ነው::
የግዕዝ ቋንቋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማስተማሪያ እና ንብረቷ አድርጐ መውሰድ ይቻላል?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ሀይማኖቷን የሰበከችው በግዕዝ ስለመሆኑ ድርሳናት እማኝ ናቸው:: በመቀጠል ደግሞ ግዕዝን ወደ አማርኛ በመተርጐም ማስተማሩ ቀጥሏል:: ከአማርኛ በኋላ ደግሞ በትግርኛም፣ በኦሮምኛ እና በሌሎችም ቋንቋዎች ግዕዙን እየተረጐሙ በማስተማር ላይ ይገኛሉ::
ግዕዝ በአክሱም መንግሥት ለነበረው ማኅበረሰብ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር፤ ተናጋሪዎችም ነበሩት:: አግአዚያን ለሚባሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች ግዕዝ ብሔራዊ ቋንቋቸው ነበር፤ እነዚያ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቋንቋቸውን በተለያየ ምክንያት ቀይረው ትግርኛ ወይም አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነዋል:: ከዚያ በኋላ የቀጠለው ትውልድ ደግሞ ግዕዝን የማወቅ ዕድል ስላላገኘ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ቀጥሏል:: ግዕዝም በፅሑፍ ቋንቋነቱ ብቻ ተወስኖ ቀጥሏል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግዕዝን ጠብቆ ከማስቀጠል አንፃር ትልቅ ባለውለታ ናት:: የግዕዝ ቋንቋ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እና በኛም ሀገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አሁን ደግሞ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር እንዲሰጥ ለማስቻል የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች ሚና የሚናቅ አይደለም:: አሁን ላይ ግዕዝ በቤተ ክርስቲያናት አካባቢ መወሰኑ ልክ ባለመሆኑም ነው በዓለማዊው የትምህር ቤቶች እንዲሰጥ የተፈለገው::
የግዕዝ ቋንቋ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች ቢሰጥ ጥቅሙ ምን ይሆን?
እጅግ በጣም ይጠቅማል:: የህንን ለማድረግ ግን አስተሳሰብ ላይ መሥራት ያስፈልጋል::
ግዕዝን እንደ ሀገር ይጠቅመኛል ብሎ የማሰብን ቅንነትም ይፈልጋል:: ከተበላሸ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወጥቶ ወይም ግዕዝን የሰሜኖቹ በተለይም የኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመጨቆኛ መሣሪያ ነው ከሚል መጥፎ እሳቤ መውጣት ካልቻልን ግዕዝን በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ለማስተማር ያስቸግራል::
የግዕዝ ጠቃሚነት ዓለም አቀፋዊ በሆነበት በዚህ ዘመን ላይ በቆሻሻ ፖለቲካዊ ወይም ሀይማኖታዊ አመለካከት የግዕዝን ቋንቋ የኢትዮጵያ ሀብትነት መካድ ስህተት ብቻ ሳይሆን በጣም ስህተትም ጭምር ነው:: የግዕዝ ቋንቋን በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ለማስተማር በቅድሚያ የተበላሸውን አመለካከት ቀስ በቀስ ማስተካከል ያስፈልጋል::
ግዕዝ የኢትዮጵያን ማንነት እና ምንነት በውስጡ የያዘ የፅሑፍ ቋንቋ በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ማስተማር ቢቻል ጥሩ ነው:: በወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በደብረ ብርሃን እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱ መሰጠቱም በጥሩ ጐኑ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው:: በብዙ የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የግዕዝ ትምህርት በኛ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አለማስፋፋትም ጥሩ አይመስለኝም:: ያም ሆኖ ግን የግዕዝ ቋንቋን ማስፋፋት የሚያስፈልገው በግድ ወይም በኃይል በመጫን ሳይሆን ጥቅሙን አስገንዝቦ በፍላጐት ላይ ተመሥርቶ መሆን አለበት::
ከግዕዝ በተጨማሪ ያሉ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካትተን ብንማራቸው ምን እንጠቀማለን?
ቋንቋን ማወቅ እና መማር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም:: ቋንቋ ጐጂ ሊሆን የሚችለው በፖለቲከኞች ጐጂ እንዲሆን ሲሰራበት ብቻ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ የቻይና ዜጐች በሥራ ምክንያት በስፋት ይገኛሉ፤ በዚህ አጋጣሚ የቻይንኛ ቋንቋን ማወቅ ለኢትዮጵያዊያን ቢጠቅማቸው እንጂ አይጐዳቸውም::
ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በአረብኛ ቋንቋ የሚናገሩ በርከት ያሉ ዲኘሎማቶች ስለሌላት የግብፅን ሴራ ማጋለጥ አልተቻለም:: የአረብኛ ቋንቋን በስፋት ማወቅ ለኢትዮጵያዊያን ቢጠቅማቸው እንጂ የሚጐዳቸው ነገር የለም:: እንግሊዘኛን ማወቅ ቴክኖሎጂዎችን ለማወቅ እንደጠቀመን ሁሉ ሌሎች የዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ማወቁም የሚጐዳን ነገር የለም:: እነዚህን ሁሉ ቋንቋዎች በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ አካትተን ለማስተማር ግን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል::
አንስታይን የገለፀውን እውቀት ሂትለር ቦንብ ሠርቶ ሕዝብን ጨርሰቦታል:: ያ ጥፋት የአንስታይን እና የእውቀቱ አይደለም:: ቋንቋንም ለበጐ እና ለመጥፎ መጠቀማችን በአጠቃቀማችን ላይ የሚወሰነው በዚህ ምክንያት ነው::
እንግዳችን ስለሆኑ ከልብ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም