ሁለት ብስክሌት አድናቂ ወይም ልዩ ፍላጐት ያላቸው የፈረንሳይ ዜጐች ሰባት ሜትር ከሰባ ሰባት ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ብስክሌት ሰርተው አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገባቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::
ኒኮላስ ባሪዮዝ እና ዴቪድ ፔይሮ የተሰኙት ፈረንሳውያን ከአምስት ዓመት በፊት ነበር በዓለማችን ግዙፉን ብስክሌት የመስራት ሀሳብን አንስተው ከስምምነት ላይ የደረሱት:: ሀሳባቸውን እውን ለማድረግም እቅድ አውጥተው ወደ ተግባር ለመለወጥ ወራት ወስዶባቸዋል::
ብስክሌቱን ከብረት እና እንጨት ሰርተው ለማጠናቀቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዓታት ፈጅቶባቸዋል:: ግዙፉን ብስክሌት መሥራት እንደመንዳት ቀላል ባለመሆኑም ሥራው ፈታኝ እንደነበር ድረ ገጹ አስነብቧል::
በብስክሌቱ የታሰረው ሰንሰለት (ቺንጋ) 16 ሜትር የሚረዝም ሲሆን የብስክሌቱ ፍጥነት በሰዓት ከ15 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል:: ፍጥነቱ ዝቅተኛ የሆነውም ግራ እና ቀኝ ሚዛኑን ጠብቆ ለማሽከርከር ፍጥነቱን መቀነስ ግድ ስለሚል እንደሆነ ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::
የብስክሌቱ አሽከርካሪ መቀመጫ እና የፊት እና የኋላ ጐማ ተመጣጣኝ ሆኖም ተገጥሞለታል:: ከጐማው እስከ አሽከርካሪው መቀመጫም ሰባት ሜትር ተለክቷል::
የብስክሌቱ ሰሪዎች ከኮርቻው እስከ ተሽከርካሪው ጐማ ላለው ክፍል ብረታ ብረት መጠቀም ውድ ስለሆነባቸው አሮጌ ከተጣሉ የቤት እቃ እንጨቶችን አካተው መስራታቸውን ይፋ አድርገዋል::
የግዙፉ ብስክሌት ሰሪዎች ዴቪድ እና ኒኮላስ የፈለጉትን ሰርተው ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት ፈጅቶባቸዋል:: የድካማቸውን ውጤት ለዓለም ለማሳየት በክሊሞንት ከተማ በተዘጋጀው ዓመታዊ ፌስቲቫል ማቅረብ ችለዋል::
ግዙፉን ብስክሌት በትክክል የሚጋለብ መሆኑን ለማሳየት ከሁለት አንዳቸው በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸው ነበር:: ለአሽከርካሪ ወይም ለጋላቢነት ዴቪድ ፔይሮ ይሁን በሚለው ተስማምተው ሰሪዎቹ 100 ሜትር ያለምንም ረዳት አሽከርክሮ በተግባር ማስመከርም ችሏል::
ግዙፉ ብስክሌት ቀደም ብሎ ከታያው ክብረ ወሰን 36 ሴንቲ ሜትር የበለጠ ሆኖ አዲስ ክብረ ወሰን መያዙንም ድረ ገጹ ጠቅሷል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም