በህንድ ሙምባይ ከተማ በሚገኘው ባለ አምስት ፎቅ የንግድ ማዕከል ህንፃ ላይ የተገጠመው 235 ሰዎችን መያዝ የሚችለው መውጫ መውረጃ የዓለማችን ግዙፉ አሳንሰር መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በ2022 እ.አ.አ “kone” የፊንላንድ ኩባንያ በህንድ ሙምባይ ጂዮ ወርልድ ሴንተር ህንፃ ውስጥ 25 ነጥብ 78 ስኩዌር ሜትር ስፋት ያለውን አሳንሰር መግጠሙን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የአሳንሰሩ መጠን እና ልዩ ንድፍ በህንፃው ላይ ለሚከወን ዐውደ ርዕይ፣ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ወዘተ. ባንድ ጊዜ በርካታ እንግዶችን ለማጓጓዝ ታሳቢ ማድረጉ ነው የተብራራው – በባለሙያዎች፡፡
በህንድ የ“kone” ማኔጂንግ ዳይሬክተር አሚት ጎሳይን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የየቅርንጫፍ ባለሙያዎች የግዙፉን አሳንሰር ንድፍ በትብብር መስራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻ በተገኘው የምርት ውጤት አሳንሰሩ የዓለማችን ትልቁ አሳንሰር መሆኑንም ነው ያሰመሩበት፡፡
ግዙፉ አሳንሰር ዙሪያውን የተለያዩ የዕይታ አማራጮችን ያስቃኛል፡፡ የአሳንሳሩ ግድግዳዎች በአራት ቋሚዎች ተከፋፍሎ መስታዎት የለበሰ ነው፡፡ በመስታዎቱ ተጓዦች የዕይታ አድማስ እስከሚገድባቸው ድረስ ውጪውን መቃኘት እንዲችሉ ባለሙያዎቹ የተጠበቡበት መሆኑ ነው በድረ ገጹ የሰፈረው፡፡
አሳንሰሩ ወደ ላይ እና ወደታች በህንፃው ውስጥ በሰከንድ አንድ ሜትር ለመንቀሳቀስ ያስችል ዘንድም 18 ተሽከርካሪ ጥርስ መዘወር ዘጠኝ ጠንካራ የብረት ገመዶች እና ወደ ላይ እና ወደታች መሽከርከር የሚያስችሉ ሀዲዶች አሉት፡፡
አሳንሰሩ ከሚይዛቸው ተጓዦች ብዛት አንፃር ጥንካሬው አስተማማኝ ይሆን ዘንድ የኩባንያው ባለሙያዎች ንድፉን ወደ ተግባር ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ነው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ያስታወቁት፡፡
ግዙፉ አሳንሰር በአምስት ፎቅ መካከል ለመውጣት እና ለመውረድ ፍጥነቱ በሴኮንድ አንድ ሜትር መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
የግዙፉ አሳንሰር ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ አለመገለፁንም የድረ ገጹ ጽሑፍ በማጠቃለያነት አስፍሯል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም