ግዙፉ የአውሮፓ መድረክ

0
157

ከስልሳ አራት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1960 በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አማካኝነት ግዙፉ የአውሮፓ እግር ኳስ መድረክ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የእግር ኳስ መድረክ ከዓለም ዋንጫ ቀጥሎ ብዙ ትኩረት የሚሰጠው እና ብዙ ተመልካች ያለው ውድድር ነው። ውድድሩ በየአራት ዓመቱ የሚከናወን ሲሆን 24 ሀገራትም ይሳተፉበታል።

ከተጀመረበት 1960 ጀምሮ እስከ 1972 እ.አ.አ ባሉት 12 ዓመታት ድረስ አራት ሀገራት ብቻ ነበር በውድድሩ የተካፈሉት። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ቀስ በቀስ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ ስምንት እና 16 አድጓል። ከ2016ቱ የፈረንሳይ የአውሮፓ ዋንጫ ጀምሮ ግን 24 ሀገራት በውድድሩ እየተሳተፉ ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለእያንዳንዳቸው የተሳታፊ ሀገራት ከዘጠኝ ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገንዘብ ሽልማት አዘጋጅቷል። ከዚህ በተጨማሪ አሸናፊው ሀገር ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት ይበረከትለታል። ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለሚጨርሰው አምስት ሚሊዮን ዩሮ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ለሚያጠናቅቅ አራት ሚሊዮን ዩሮ የገንዝብ ሽልማት ይሰጣቸዋል። በተመሳሳይ ሁሉም ሀገራት ባሳዩት አቋም ልክ ከሽልማቱ ይቋደሳሉ።

ተጫዋቾቻቸው በመድረኩ ለሚሳተፉ ክለቦችም የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን ለአብነት ቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከሚያገኙት መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣሉ። የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን አስተናጋጅነት ከሰኔ ሰባት ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን ልሳነ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው በ1988 እ.አ.አ ነው። ሀገሪቱ ከተዋህደች በኋላ የአውሮፓ ዋንጫን ስታስተናግድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። የጀርመንን ያህል በመደረኩ በተደጋጋሚ የተሳተፈ ሀገር የለም። ምዕራብ አውሮፓዊቷ ሀገር ለ13ኛ ጊዜ እየተሳተፈች ሲሆን ስፔንም ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ በመሳተፍ ከቀዳሚዎች ተርታ ተሰልፋለች።

አነሰም በዛም በውድድሩ እየተካፈሉ ያሉት ብዙዎቹ ሀገራት ለመድረኩ እንግዳ አይደሉም። በውድድሩ እንግዳ የሆነችው ብቸኛዋ ሀገር ጆርጂያ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የምድብ ጨዋታዎች እየተከናወኑ ሲሆን ገና ከወዲሁ ዋንጫውን ማን ሊያሸንፍ ይችላል? የሚለው ትኩረትን ስቧል። እንደ ኦፕታ አናሊስት  መረጃ ስምንት ሀገራት ዋንጫውን የማንሳት ዕድል አላቸው።

የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በአውሮፓ ዋንጫ ለ11ኛ ጊዜ ነው እየተሳተፈ የሚገኝው። ይሁን እንጂ ሦስቱ አናብስት አንድም ጊዜ ዋንጫውን አለማሳካታቸው ይታወቃል። በጋሪዝ ሳውዝጌት የሚመራው ቡድን ዘንድሮ ግን ከሁሉም ብሄራዊ ቡድኖች የተሻለ ለዋንጫ ግምት ተሰጥቶታል። 11 ሀገራት በጥምረት ባዘጋጁት የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ድረስ በመጓዝ ዋንጫውን በጣሊያን መነጠቃቸው ይታወሳል።

በኦፕታ አናሊስት ትንታኔ በዘንድሮው የአውሮፓ  ዋንጫ እንግሊዝ ሰፊ የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታለች። አሥራ ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷታል-እንግሊዝ። ምንም እንኳ ሦስቱ አናብስት እስካሁን የመድረኩን ዋንጫ ለማንሳት ዐይን አፋር ቢሆኑም የካበተ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ዘንድሮም ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ ሀሪ ኬን፣ ጁዲ በሊንግሀም፣ ፊል ፎደን፣ ቡካዮ ሳካ፣ ዴክላን ራይስ እና የመሳሰሉትን ኮከቦች ይዟል። ምርጥ የተጫዋቾች ስብስብን የያዘው የጋሪዝ ሳውዝጌት ቡድን ጃክ ግሪልሺን፣ ጀምስ ማዲሰንን ጃራድ ብራንትዋይት፣ ከርቲስ ጆንስን እና ሌሎችንም መቀነሳቸው ስብስቡ ምን ያህል ጥልቀት ያለው መሆኑ ያሳያል።

የአማካይ ክፍሉ ባለፉት ዓመታት የአሠልጣኝ ሳውዝጌት ዋና የራስ ምታት ነበር። አሁን ላይ ግን ችግሩ መቀረፉን ስካይ ስፖርት አስነብቧል። ዴክላን ራይስ፣ ጁዲ በሊንግሀም እና ኮቢ ማይኖን የመሳሰሉት ባለተሰጥኦ ችግሩን ቀርፈዋል ብሏል ስካይ ስፖርት።  በወጣቶች እና ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረ መሆኑ ቡድኑን ይበልጥ አስፈሪ አድርጎታል።

በስብስባቸው የቡንደስ ሊጋውን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መያዛቸው ደግሞ ለዋንጫ እንዲታጩ አድርጓቸዋል። ባለፉት ሁለት የዓለም እና የአውሮፓ መድረኮች ማለትም በዓለም ዋንጫ እና በኔሽንስ ሊግ ውድድር ሀሪኬን ለሀገሩ በ18 ጨዋታዎች 12 ግቦችን በማስቆጠረ ከኬሊያን ምባፔ ጋር እኩል ክብረ ወሰን ተጋርቷል።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ምርጥ የሚባል እንደነበር ያስነበበው ስካይ ስፖርት አሠልጣኝ ሳውዝጌት ዘንድሮም የመድረኩን ምርጥ ቡድን እየመሩት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። ምንም እንኳ ስብስቡ ወረቀት ላይ አስደናቂ ነው ቢባልም በደጋፊዎች ዘንድ ግን ብዙ እምነት አልተጣለበትም። እናም አሠልጣኙ እና ተጫዋቾች የዋንጫውን እርግማን በመስበር የ2024ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ወደ ሀገራቸው የማምጣት ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። እንግሊዝ በምድብ ሦስት ከስሎቫኒያ፣ ዴንማርክ እና ሰርቢያ ጋር የምድብ መርሐ ግብሯን እያከናወነች ነው፡፡

የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ እና የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዋ ሀገር ፈረንሳይ ወርቃማ ትውልዷ አሁንም አልደበዘዘም። ፈረንሳይ ልክ እንደ እንግሊዝ በመድረኩ የካበተ ልምድ ያላት ሲሆን ዋንጫውንም ሁለት ጊዜ አሳክታለች። እ.አ.አ በ1984 እና በፈረንጆች ሚሊኒየም ዋንጫውን ያነሳችበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

በኦፕታ አናሊስት ትንታኔም ፈረንሳይ 19 ነጥብ አንድ ከመቶ ዋንጫውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝታለች። የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በደንብ የተደራጀ እና ብዙ ጥራት ባላቸው አማራጮች የተሞላ ስብስብ ነው። አሠልጣኝ ዲዲየር ዴሾ በሁሉም የሜዳ ክፍል የሚተማመኑባቸው በርካታ ተጫዋቾች አሏቸው። ለአብነት በመጀመሪያው የሚዳ ክፍል ማይክ ሚኞን፣ ሉካስ ሄርናንዴዝ፣ ኢብራሂም ኮናቴ፣ ዊሊያም ሳሊባ፣ ዊስሊ ፎፋና፣ ጁሊየስ ኩንዴ፣ ዳዮት አፓሜካኖን እና የመሳሰሉትን አካቷል።

በኬሊያም ምባፔ ፊታውራሪነት የሚመራው የፊት መስመርም በአሠልጣኙ እና በደጋፊው እምነት የሚጣልበት ነው። በአሠልጣኝ ዴሾ ከአጥቂነት ይልቅ የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና የተሰጠው አንቷን ግሪዝማን ቦታውን ካገኝ እና በእያንዳንዱ ጨዋታ በመጀመሪያው አሰላለፍ ከተካተተ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በዋንጫ ታጅቦ ሊያጠናቅ ይችላል ብሏል፤ የኦፕታ አናሊስት መረጃ።

በዋናነት አዲሱ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ኬሊያን ምባፔ በስብስቡ ውስጥ መገኘት ፈረንሳያውያን ባዷቸውን ወደ ሀገራቸው እንደማይመለሱ እምነት አሳድረዋል። አሠልጣኝ ዲዴየር ዴሾ ባለፉት 11 ዓመታት ከፈረንሳይ ጋር ሁለት ዋንጫዎችን አሳክቷል። የሩሲያውን የዓለም ዋንጫ ያሳካችው ፈረንሳይ፣ በ2021ዱን የኔሽንስ ሊግ ውድድር ዋንጫንም ማንሳቷ ይታወሳል፡፡ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ደግሞ ፍጻሜ ድረስ መጓዟ አይዘነጋም።

ታዲያ እስከ መጨረሻው የውድድሩ ምዕራፍ ድረስ በመጓዝ ልምድ ያለው አሠልጣኙ ዘንድሮም ፍጻሜ ለመድረስ ብዙ አይችገርም ተብሏል። የፈረንሳይ ብሄራዊ  ቡድን ከፖላንድ፣ ኔዘርላንድስ እና ኦስትሪያ ጋር በምድብ አራት ጨዋታዋን እያደረገች ትገኛለች።

የውድድሩ አስተናጋጇ ሀገር ጀርመን በሦስተኛ ደረጃ ዋንጫውን ታነሳለች ተብሎ በኦፕታ አናሊስት  ቅድመ ግምት የተሰጣት ሀገር ነች። ጀርመን ከስኮትላንድ ፣ ሀንጋሪ እና ስዊዘርላንድ በምድብ አንድ መርሀግብሯን እያከናወነች ትገኛለች።ጀርመን ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫ ከምድብ ማለፍ ተስኗት በጊዜ መሰናበቷ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጄ የድግሱ አጋፋሪዋ ሀገር ዋንጫውን በቤቷ የማስቀረት ቅድመ ግምት ከእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ቀጥሎ ተሰጥቷታል። ቅድመ ግምቱን ያስቀመጠው ኦፕታ አናሊስትም 12 ነጥብ አራት በመቶ ዕድል እንዳላት አስቀምጧል። ይሁን እንጂ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ አስተናጋጅ ሀገር ዋንጫውን ካነሳ 40 ዓመታት ተቆጥሯል። ፈረንሳይ በ1984 እ.አ.አ ያስተናገደችውን ዋንጫ በቤቷ ማስቀረቷ በታሪክ ሰፍሯል።

ይህንን የፈረንሳይ ታሪክ ለመድገም በአንጋፋዎች ቶኒ ክሩስ፣ ማኑኤል ኑዬር፣ ቶማስ ሙለር እና ኤካይ ጉንዶጋን በመታገዝ ዋንጫውን ያነሳሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም አሠልጣኝ ጁሊያን ኔግልስማን ጀማል ሙሲያላ እና ፍሎሪያን ዊርቲዝን የመሳሰሉ ወጣት ኮከቦችን ማካተቱ ለቡድኑ የተለየ ጥንካሬ ይሰጥዋል ተብሎ ይገመታል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በጀርመን እግር ኳስ አብዮት ትልቅ መነቃቃት የተፈጠረበት እንደነበር የሚታወስ ነው። ባየርን ሊቨርኩሰን ዋንጫውን ሲያነሳ ስቱትጋርትም የሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ የሚያሳትፈውን ውጤት ማግኝቱ አይዘነጋም። እነዚህ ክለቦች ከባየር ሙኒክ እና ቦርሺያ ዶርትመንድ በተጨማሪ በርካታ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኑ አስመርጠዋል። ይህም ቡድኑ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀርብ አግዞታል። ከላይ ከተጠቀሱት ሀገራት በተጨማሪ ስፔን፤ ፖርቹጋል፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን እና ቤልጂየም ለዋንጫ የታጩ ሀገራት ናቸው።

በጀርመን እየተከናወነ ባለው በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር በርካታ ተጫዋቾች በበሄራዊ ቡድናቸው መለያ የመጨረሻቸው መድረክ ነው። የሠላሳ ዘጠኝ ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ደግሞ ከብዙዎች አንዱ ነው። ፖርቹጋላዊው ኮከብ በአውሮፓ ዋንጫ 43 ግቦችን በማስቆጠር ባለክብረ ወሰን ነው።

ተጫዋቹ ከአራት ዓመታት በኋላ እድሜው 43 ስለሚደርስ በ2028ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ይሳተፋል ተብሎ አይገመትም። በተመሳሳይ ጀርመናዊያኖቹ ቶኒ ክሩስ እና ማኑኤልኑዪር፣ ክሮሺያዊው ሉካ ሞድሪች እና ፈረንሳያዊው ኦሊቨር ጅሩድ የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ የመጨረሻቸው መሆኑ ተነግሯል።

ጀርመን እና ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን እኩል ሦስት ጊዜ በማንሳት ክብረ ወሰኑን ተጋርተዋል። ጣሊያን እና ፈረንሳይ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አሳክተዋል። ሩሲያ፣ ቼክ ሪፐፕሊክ፣ ፖርቹጋል፣ ስሎቫኪያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ዴንማርክ እና ግሪክ አንድ አንድ ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል። ዘንድሮስ ማን ዋንጫውን ያነሳል? ከሦስት ሳምንት በኋላ አብረን የምናየው ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here