ግግር በረዶ የለበሰዉ መኖሪያ ቤት

0
41

በካናዳ ኩቤክ  ትሮይስ- ራቪዬሪስ በተሰኘ ቀጣና የጋራ መኖሪያ ህንፃ ባለንብረት  ግለሰብ ባጋጣሚ  ጐራ ባሉበት አንዱን በሩን ሲከፍቱ ግድግዳ እና ጣሪያው፣  የቤት እቃዎቹ ጭምር  በግግር በረዶ ተሸፍነው ማግኘታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::

ባለንብረቱ ዣክ ናውልት ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የአንዱን በር ሲከፍቱ በበረዶ የተሰራ የቤተመንግሥት ፍርስራሽ የተመለከቱ እንደመሰላቸው ነው የተናገሩት:: ግድግዳው፣ ወለሉ፣ ጣሪያው፣ በየጥጋ ጥጉ የተቀመጡ ቁሳቁስ ሳይቀሩ ረቂቅ  ቅርፃ ቅርፅ መሰለዋል – በግግር በረዶ::

ባለንብረቱም የሁነቱን መንስኤ ተዟዙረው ለመመልከት ሞክረዋል::  በፍተሻቸው ተከራዩ ግለሰብ ለቀናት ከቤት ለእረፍት ሲሄዱ የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን ለመቆጠብ በማሰብ ማሞቂያውን ማጥፋታቸው ወይም ኃይል መቋረጡ መንስሄ መሆኑን አረጋግጠዋል::

ተከራዩ የማሞቂያ ክፍያውን ለመቆጠብ ኃይል በማቋረጣቸው የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ፈንድተው ግድግዳዎች ሻግተው ለከፍተኛ ወጪ ዳርጓቸዋል:: በዚህም  አከራዩ ተከራዩን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ነው የተጠቆመው- በድረ ገጹ::

ዣክናውልት ሁሉም ነገር ውድ መሆኑን እና ወጪ መጨመሩን ጠቁመው ተከራዩ ወጪ ለመቀነስ  የፈፀሙት ስህተት የበለጠ ወጪ ማስከተሉን ነው ያሰመሩበት::

አከራዩ ባጠቃላይ የተከሰተውን ጥፋት ወይም በመኖሪያ ቤቱ እና ቁሳቁስ ላይ የደረሰው ጉዳት በአስር ሺህ ዶላሮች እንደሚገመትም ነው ያሰመሩበት::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here