ግጥም ዓይነቱ፣ ይዘቱ እና ባህሪው ልዩ ልዩ ማንነት ሰጥቶታል። በየዘመናቱ የተለያዩ ትርጓሜዎች ተሰጥተውታል።
ግጥም የተጨባጭነት ባህሪ አለው፤ በእውነት እና ለአንባቢው የስሜት ህዋስ እንዲሰማ አድርጎ የማቅረብን ጥበብ ይከተላል። ከነባራዊው ዓለም እውነት ይነሳል።
ግጥም ምናባዊ ነው፣ ግጥሙን ስንሰማ ወይም ስናነብ በሐሳብ ያየናቸው ወይም የሰማናቸው እስኪመስለን ድረስ በገጣሚው ዓለም ውስጥ እንድንመላለስ ያስገድደናል።
ግጥም ቁጥብ ነው፣ በጥቂት ቃላት፣ በጥቂት መስመሮች፣ በጥቂት ገጾች ግዙፍ ሐሳብን ማስተላለፍ ይችላል። ሐሳብን በአጭሩ ማስተላለፍ ያስችላል።
ግጥም ሙዚቃዊ ባህሪም አለው። ቅላጼ፣ የድምጽ ከፍታ እና ዝቅታ፣ ድምጸትም አለው። አቀራረቡ የሙዚቃ ባህሪ አለው። ምት፣ ምጣኔ እና ሌሎች የሙዚቃ ባህሪያትን ይዟል። ግጥም ሕግ እና ስርዓት ቢኖረውም እንኳን የማፈንገጥ ባህሪም አለው። ምስል የመከሰትም ባህሪ እንዲሁ።
በዚህ ጽሑፋችን ቁጥብነት የሚለውን የግጥምን አንዱን ባህሪ መሰረት አድርገን ከሀገራችን ገጣሚያን ስራዎች መካከል የተወሰኑትን እያነሳን እንመረምራለን።
ግጥም ከዝርው ጽሑፍ የሚለይበት አንዱ ባህሪው ቁጥብነቱ ነው፤ ይህም ሲባል አንድ የመጽሐፍ ሐሳብን፤ የአንድ ቀን ስብሰባን፣ የሦስት ሰዓት ቴሌቪዥን ወይም የሬዲዮ ፕሮግራምን በሁለት ወይም በአራት መስመር ስንኞች ማስተላለፍ መቻሉ ነው። በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት እንዲሉ አበው ግጥም ልቡ እንደ ሐይቃችን ጣና ሰፊ ነው። አንደ አዋሽም በውስጡ ብዙ መያዝ ይችላል።
ጌትነት እንየው “የህይወት ክረምት” በሚል ጥሩ ግጥም ፣ ማራኪ መልዕክት ጽፏል።
“ናላ በጭጋግ ሲሸፈን
ልቦና በስጋት ሲባባ
መርሳት በራስ ቤት ሲሰራ
ፍርሀት ግንቡን ሲገነባ
ጭንቀት ጓዙን ሲያሰፍር
መጠርጠር ጫፉ ሲተባ
ለአወቀ መንቃት ያኔ ነው
የህይወት ክረምት ሲገባ”
እርጅና በጣም ቀፋፊ ነገር ነው። ማርጀትን በጸጋ የሚቀበል ሰው አላጋጠመኝም። የሆነ ፍርሀት አለው። ጉዞው በልጅነት ወንበር ወይም የወላጆችን እግር ተደግፈን፤ ወድቀን ተነስተን ጥለነው ወደ መጣንበት ምድር ይሉት አፈር ነውና ያስጠላል። ጊዜ ይነጉዳል፣ የገደልነው ይመስለናል እኛ ስናረጅ እሱ ይታደሳል።
በእውቀቱ ስዩም፣
“እኛኮ ለዘመን ክንፎች አይደለንም፤
ሰንኮፍ ነን ለገላው፣
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው”
እንደሚለው የእድሜያችን ጀንበር ትጠልቃለች እንጅ ጊዜ እያደረ አዲስ ነው። እንደ እባብ ሰንኮፍ እያወለቀ እየጣለን ይገሰግሳል።
የልጅነት ዘመን ስጋት፣ መርሳት፣ ፍርሀት፣ ጥርጣሬ በእርጅና ዘመንም ተመልሰው ይመጣሉ። ሕይወት ክብ ነገር አለው። በጀመርንበት ጫፍ እንጨርሳለን። ጌትነት “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ቃል ወስዶ ግጥሙን የጻፈው ይመስላል።
“እርጅና ብቻህን ና” ይላሉ አበውም። እሱ ግን እሽ አይልም፤ የሰው ምክር አይሰማም። ጎረምሳ በመሆኑ በጉልበቱ ይመካል። አጃቢዎቹን ይዞ ነው የሚመጣው። ጌትነት ያን ጊዜ ምልክቱን አይታችሁ ንቁ። መላ ፍጠሩለት ነው የሚለን።
ክረምት ቀዝቃዛ ነው፤ ብርድ ነው፤ ጭጋግ ነው። መራራቅ፤ መነጣጠል ነው። እርጅናን ነው ጌትነት ክረምት ሲመጣ ብልህ የሆነ ቤቱን አሙቆ፣ እሳት አንድዶ፣ የውጪውን ወደ ጓዳ አስገብቶ ይጠብቀው የሚለው።
ዓለም ፀሐይ ወዳጆ “የማታ እንጀራ ስጠኝ” በሚለው ግጥም በእርጅና ዘመን መቸገር፣ መለመን፣ እንዴት ቀፋፊ እንደሆነ በሚገባ ገልጻዋለች።
“የማታ እንጀራ ስጠኝ
የጠዋት አታስመርጠኝ
ዘግይተህ በኋላ አስጊጠኝ
ማታ በክብሬ ደብቀኝ
ከሰው በር አንተው አርቀኝ
ጉልበቴ ጽናቱን ይዞ
አቅሜም እንደ አቅሙ ተጉዞ
ያልጠየቁኝን ሳልመልስ
መንገዴን በወግ ልጨርስ”
እያለ ይቀጥላል ግጥሙ።
ጠዋት ወጣትነት ነው። ጠዋት አዲስ ጉልበት፣ ጥንካሬ፣ የምርጫ ጊዜ፣ የሀብት እና ዝና ጊዜ ነው። ታግሎ መጣያ፣ ሮጦ ማሸነፊያ ነው። ማታ ደግሞ እርጅና ነው። መስከን፣ መጸለይ፣ ማስታረቅ፣ መመረቅ፣ መስበክ፣ መጫዎት የሚመጣበት የእርጅና ምእራፍ ነው።
እርጅና እዚህ ተግባር ውስጥ የሚያስገባን ፈልጎ አይደለም፤ ጉልበት እና አቅም ስለሚያንሰን እንጂ። ተገፍተን ነው ከጉልበት እና እውቀት ውጪ ባሉ ተግባራት የምንሰማራው። ዓለም ፀሐይ እንደ ወጉ ጠዋት ልቸገር ማታ ላግኝ ነው የምትለው። ብዙዎች ጠዋት ሰርግ የመሰለ ሕይወት ኖረው፤ ማታ የለቅሶ ሕይወት ኖረዋል።
በዚሁ ወደ ዮሐንስ ሞላ ግጥሞች ልለፍ።
“በቧልት ላላገጠ በፌዝ ለዘለለ
ብሩህ ተስፋን ነፍጎ ጸጸትን ካደለ
የሰው ፊት ካሳዬ ዝቅ አርጎ ካዋለ
ጊዜ ገደለ እንጂ መቼ ተገደለ”
በልማድ ጊዜ እንግደል እንላለን። እውነታው ግን ጊዜን መግደል ጊዜን ሳይሸራርፉ ተጠቅሞ በፍሬ የሚመዘን ተግባር መከወን ነው ይላል ዮሐንስ።
ዓለማችን አሁን ያለችበት የኢኮኖሚ ችግር ልዩነቱ ጊዜን ከመጠቀም እና ካለመጠቀም ጋር የሚገናኝ ነው። በቧልት፣ በቀልድ፣ በተስፋ ቢስነት የምናሳልፈው ጊዜ በውጤቱ እንጸጸትበታለን፤ ከሰው አሳንሶም ለልመና ይዳርገናል።
አርሶ አደሮቻችን “ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቅ፤ ወፍጮው እንዳጓራ መስከረም ዘለቀ” እንደሚሉት ነው። ያረሰ ገበሬ በሐምሌ እና በነሐሴ የሚፈጨው እህል አያጣም። በእርሻ ወቅት ከበሮውን ይዞ ሲዘፍን የከረመ ሰነፍ ገበሬ አቅማዳውን ይዞ እህል ልመና በሰው ፊት ይገረፋል። ከሐምሌ ተሻግሮ መስከረም ለመድረስ ይለምናል። የሚላስ የሚቀመስ ከቤቱ ይጠፋል። ዮሐንስ ይህን ሰፊ ሐሳብ ነው እንዲህ በአጭር ያስቀመጠው።
የደበበ ሰይፉን ግጥሞችም በነካ እጃችን እንመልከት። ቋንቋ አስተማሪ፣ ገጣሚ እና ባለቅኔ ነበር ይባላል፤ ደበበ ሰይፉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነ ጽሑፍ መምህር ነበር። ማህበራዊ ጉዳዮችን በስፋት በግጥሞቹ ዳስሷል። “እሱ ነው እሱ” የሚለው ግጥሙ ባልበላው ጭሬ ልድፋው፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት አስተሳሰባችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“ዓይን ባይኖረው ለምን ብርሃን ኖረ የሚለው
እግር ባይኖረው ለምን መንገድ ኖረ የሚለው
እሱ ነው እሱ
ከቀናቴ ፀሐይቱን የሰረቀው
በመንገዴ አሜኬላ ያጸደቀው”
የሰው ልጆች የክፋት ጥግ በዚህ ግጥም ቀርቧል። የሰዎች በልቶ ማደር ያበሳጨናል፤ የሰዎች መለወጥ ያንገበግበናል። እኛም አብረን እስካልበላን እና እስካልተለወጥን ጊዜ ድረስ። ሰው ወደ ከፍታው ሽቅብ ሲቧጥጥ የእኛን ስንፍና ስለሚያሳብቅብን ቁልቁል ልንጥለው እንለፋለን። ደበበ በአንድ ሰው እሱ ብሎ አቀረበው እንጅ ይህ የቅናት ባህሪ የሰው ልጆች መገለጫ ነው።
ከጥንት አቤል እና ቃየል ጀምሮ ያለ ነው፤ ቅናት። እርግጥ ነው እንደየ አካባቢው፣ እንደ የማህበረሰቡ የእድገት ደረጃ የቅናት መጠናችን ይለያይ ይሆናል።
በሀገራችን በርካታ አንጋፋ እና ወጣት ገጣሚያን አሉ። አሁን ደግሞ ወደ መድረክ እየመጡ ያሉ ጎበዝ ገጣሚያን አሉ። የሁሉንም ግጥም መዳሰስ ከባድ ነው። የዛሬውን ጽሑፋችንን በኑረዲን ኢሳ “የትንሽ ሰው መርህ” በተሰኘች ግጥም እንቋጨው።
በተለይ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ዝና እና ትኩረት ለማግኘት ትንሽ ሰዎች የያዙትን መርህ በሚገባ ይገልጻል ግጥሙ።
“አልሆን ያለህ ጊዜ መጉላት እና መግዘፍ
ከትልቆች መሀል አንዱን መርጠህ ዝለፍ”
አበቃሁ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም