በከንፈርሽ በራፍ የተሰኘ የግጥም መድብል ለአንባቢዎች በቅርቡ አበርክቷል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን በስታስቲክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በስነ ህዝብ ጥናት ሰርቷል፡፡ ከቁጥር ጋር ያለው ቁርኝት ባልተለመደ መልኩ ውበትን ከማድነቅ እና ከመቀኘት አልከለከለውም፡፡ “የንግግር እና የመግባባት ወዳጅ ነኝ፤ ብዙ ጊዜ ንግግሬን ለማሻሻል፣ ከሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት (ውህደት) ለመፍጠር እንዲሁም ራሴን በተሻለ ለመግለጽ አማርኛዬን ለማቅለል ስሞክር አሳልፌያለሁ፤ በዚህም የተነሳ ያልኩት ቀጥታ ተወስዶልኝ ተደስቼ አውቃለሁ፤ ያልኩት ካሰብኩት በላይ ተቃንቶ ተጨምሮ ተወዶልኝ የማይገባኝን ምስጋና እና ክብር አግኝቼ አውቃለሁ፤ ያልኩት በሌላ ተተርጉሞ ባላልኩት ተወቅሼ ካለ ጥፋቴ ተቀጥቼ አውቃለሁ፤ ካልኩት ውስጥ ያላልኩትን ለመፈለግ የደከሙም አሉ…” ሲልም ስለገጠመው ይገልጻል፤ ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ፡፡ ገጣሚ ዮሐንስ ከአሚኮ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡
መልካም ንባብ!!
በከንፈርሽ በራፍ ግጥምህ ውስጥ ተስሜ ስለማውቅ የምትል ስንኝ አለች፤ ምን ማለት ናት?
ሁሉም ልጅ የመሳም እድል ላያገኝ ይችላል፡፡ እንደተኖረበት ጊዜ እና አካባቢ ይወሰናል፡፡ ሰዎች ቀልብ ሳይኖራዋቸው ህጻን ለመሳም ላይታደሉ ይችላሉ፡፡ የኑሮ ውጣ ወረዱ እና ሩጫው ፋታ የማይሰጥህ ጊዜ እና ቦታ ላይ ከሆንክ ውበት እንዳታደንቅ የሚሳም ልጅ እያየህ እንዳትስም ያደርግሀል፤ በራስህ ጉዳይ ተጠምደህ ለሌላ ነገር ትኩረት እንዳትሰጥ የሚያስገድዱህ ጊዜያት አሉ፡፡ እኔ እድለኛ ሆኜ ከልጅነት እስከ እውቀት እንደተሳምኩ ነው፡፡
መሳም የሚለው ቃል በቀጥታ አንድ ትርጉም ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ፈሊጣዊ አነጋገር አለው፤ እንደ እድል ልትወስደው ትችላለህ፡፡ በሌላ አተያይ ደግሞ መሳም ማለት የሆነ ነገር ሄዶ ከሌላ ነገር ጋር ተላትሞ መስተጋብር አድርጎ ንዝረት ሲፈጥር፣ ግጭቱ ደስታ ሲያመጣ፣ ሰላማዊ ግጭት ሲሆን ማለት ነው፡፡ ከአንድ ሰው ጋር ክርክር ውስጥ ተገብቶ እያለ በሰላማዊ መንገድ መግባባት እና አንድነት መፍጠር ሲቻል ሀሳብ ተሳመ እንላለን፡፡ በተፈለገው መንገድ መውሰድ ይቻላል፡፡
የብርሃን ሰበዞች በሚለው ሁለተኛው መጽሐፌ ላይ በከንፈርሽ በራፍ ሳልፍ የሚል ግጥም አለ፡፡ ይህ ግጥም ደግሞ ከላይ ካነሳሁት ሀሳብ በተለየ የፍቅር ግንኙነትን፣ የመጀመሪያ ጾታዊ መሳሳምን የሚገልጽ ነው፡፡ እድልን፣ መግባባትን፣ አንድ መሆንን እና ተቀባይነትን ከመግለጽ ባሻገር ጾታዊ ፍቅርንም ገልጬበታለሁ፡፡
ግጥም ውበት እና ጥልቀቱ አንባቢው በሚፈልገው እና ስሜት በሚሰጠው መንገድ መተርጎም መቻሉ ነው፡፡ አንተ ስለፍቅር የጻፍከው ግጥም በፖለቲካ ተተርጉሞብህ ያላሰብከውን ጣጣ ሊያመጣብህም ይችላል፡፡ የፖለቲካ መልዕክት አለው ያልከውን ደግሞ ፍቅረኛህ እንዴት በግጥም አሽሙር ተናገርከኝ ብላ አኩርፋ ልትጠረቅምህ ትችላለች፡፡ ስለዚህ ግጥም የሚወሰደው እንደ አንባቢው እና ተርጓሚው ነው፡፡
ሀሴት ካለቦታው ግጥም አትሌት አበባ አረጋዊን መነሻ አድርገህ የጻፍከው ነው፤ ምን መግለጽ ነው የተፈለገው?
የሰው ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ በሀብትም ይሁን ድህነት፣ ማግኘትም ሆነ ማጣት ውስጥ ተቀባይነትን ይፈልጋል፡፡ ሀሳብ ሼጦ ሀሳብ ገዝቶ ማደር ይፈልጋል፡፡ ዓለምን ያነቃነቀ ሀብታም ወይም ዓለምን ያስደነቀ ደሃ ብትሆን ዋጋ በምትሰጠው ሰው ካልተገለጡ ወይም ካልታዩ ዋጋ ያጣሉ፡፡ አበባ አረጋዊን መነሻ አድርጌ የጻፍኩት ግጥም በዚህ ላይ ያጠነጥናል፡፡ አበባ ለሌላ ሀገር ነበር የምትሮጠው፡፡ ኢትዮጳያዊት ናት፤ አሸንፋ የሌላ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ ይዛለች፤ እኔ ሳያት ሰንደቅ ዓላማውን እንደነገሩ ነው የያዘችው፡፡ ደስታ ካለቦታው ሲሆን ያሳያል፡፡ አበባ ማሸነፉን አሸንፋለች፡፡ ነገር ግን መስቀል አደባባይ ወጥተን ሳንጨፍርላት፣ እንኳን ደኅና መጣሽ ሳንላት፣ ጀግናችን ሳንላት ወርቁን ማግኘቷ ጎዶሎ ነው፡፡ ህመሟ ህመሙ የሆነ፣ ደስታዋ ደስታው የሆነ ህብረተሰብ አለ፤ ነገር ግን በደስታዋ መደሰት አይችልም፡፡ ግጥሙን በአጠቃላይ መታሰቢያ ያደረኩት ለራሴም፣ ለሀገርም፣ ለማኅበረሰቡም ነው፡፡
ለምስጋና ትልቅ ቦታ ትሰጣለህ ይባላል፤ በግጥም መጽሐፎችህም ሰፋ ያለ ምስጋና አለ፡፡ ምንድን ነው ምክንያቱ?
እኔ በሕይወቴ ብዙ የተረዳሁ (የታገዝኩ) ሰው ነኝ፡፡ ቀደም ሲል ተስሜያለሁ እንዳልኩት በትንሽ ትልቁ የሚገባኝንም የማይገባኝንም ብዙ በረከት አግኝቼያለሁ፡፡ የማማርርበት ነገር የለም፡፡ ከሰዎች ጋር በተገናኘሁባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሰዎች ለእኔ መልካም ናቸው፡፡ የሰዎችን ምስጋና አልረሳም፡፡ አንድ የምስጋና መጽሐፍ ካልወጣ በስተቀር በቁንጽል ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ደግ ነገር ለማድረግ ፈልገው አይደለም ክፋት አስበው እንኳ ያገዙኝ ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉም ሰው ጥሩ ሊሆን እንደማይችል የሚታወቅ ነው፡፡ የሆነ ነገር ወደ አንተ ሲወረወር የምትቀበልበት መንገድ ውጤቱን ይወስነዋል፡፡ ድንጋይ ወደ አንተ ሲወረወር ቆስለህ ትቀመጥበታለህ ወይስ ጡብ አድርገህ ቤትህን ትገነባበታለህ ነው ጉዳዩ፡፡
እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፤ በርካታ ሰዎች ያግዙኛል፤ አንዳንድ ሰዎች አሉታዊ ነገር ለማድረግ እንኳ አስበው የሠሩት ተግባር ወደ ጥሩ ይቀየርልኛል፡፡ እናም ምስጋና የተቀበልከውን ለሁሉም ዋጋ በመስጠት ለመመለስ የምትሞክርበት መንገድ ነው፡፡ እናም የእገዛ ጥጋቤን ያክል ነው ለማመስገን ብዙ የጣርኩት፡፡
አንባቢ ግጥሞችን በፈለገው ይረዳ ስትል ትደመጣለህ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግጥሞቼ ቅርጾች ብለህ ማብራሪያ ትሰጣለህ፤ በተለይ ሁለተኛው ሀሳብ የአንባቢን የመተርጎም መብት መጋፋት አይሆንም?
አይሆንም! የግጥሞቼን ሀሳብ እና ትርጉም ሳይሆን ቅርጻቸውን ነው ለማስረዳት የሞከርኩት፡፡ ቅርጻቸውን ለማስረዳት የሞከርኩት ከዚህ በፊት ተጽፎባቸው ስለማያያውቅ ነው፡፡ ተጽፎባቸው አላየሁም፤ እንግዲያ ያላየሁት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ሌላ ያጣቀስኩት ጽሑፍ የለም፡፡ እንደሚገባኝ አዲስ ቅርጽ እየሞከርኩ ስለሆነ እግረ መንገዱን ሌሎች ሰዎች ከወደዱት እና ካመኑበት እንዲከተሉት፣ ዝም ብሎ በአጋጣሚ እንዳልሆነ አንዲታወቅ ነው ማስገንዘቢያውን ያሰፈርኩት፡፡
የግጥሜን ቅርጽ ሳስረዳ ክብነት አለው የምለው ስንኞቹ ተደርድረው ሲያልቁ መዝጊያው ከርዕሱ ስለሚገጥም ነው፡፡ በሀሳብ ቤት ይመታል፤ በቃል ቤት ይመታል፡፡ ያ ማለት ከላይ የተነሳው ሀሳብ ከታችኛው ጋር ይጋጠማል፤ ክብ ቅርጽም እንደዚሁ ነው፡፡
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም