ግጭቱ እና የትምህርት እንቅስቃሴዉ

0
305

በአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ያስታወቀው የትምህርት ዓመቱ አንድ ብሎ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ነበር:: ለዚህም መማር ማስተማሩን ውጤታማ ያደርጋሉ የተባሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ በ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት ሲከናወን ቆዬ:: የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ማሻሻል፣ በጅምር ላይ የነበሩ የትምህርት ተቋማትን ማጠናቀቅ እና ለአዲሱ ዓመት ዝግጁ ማድረግ፣ የተማሪ መቀመጫ ወንበር ወደ ትምህርት ቤቶች ለማስገባት ጥረት ሲደረግ እንደነበር የቀደሙ ዘገባዎቻችን ያረጋግጣሉ:: የአዲሱን ሥርዓት ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ የትምህርት አሰጣጡ በምን አይነት መንገድ እንደሚሰጥ ለተማሪዎች እና ለመምህራን ግንዛቤ መፍጠር፣ የመማሪያ መጻሕፍትን ቀድሞ ማሟላት እና ሌሎችም በተወሰነ መንገድ ሲከናወኑ ቆይተዋል::

ተማሪዎች መደበኛውን የትምህርት ዓመት አጠናቀው ለቀጣዩ ዓመት የማጠናከሪያ ትምህርት ለመከታተል እና የተማሪ ምዝገባ ለማድረግ   እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ሁኔታ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ አጋጠመ:: ከወርሀ ሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በመደበኛ የትምህርት አጀማመር ላይ ብቻ ሳይሆን የማጠናከሪያ ትምህርቶች እንደቀደሙት ዓመታት በተሳካ ሁኔታ እንዳይሰጡ አድርጓል:: በተመሳሳይ ቀን በክልሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይጀመር የነበረው የተማሪ ምዝገባ እና መማር ማስተማር እውን ሳይሆን ቀረ::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በዓመቱ መዝግቤ አስተምራቸዋለሁ ካላቸው ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ትምህርት ገበታቸው አልመጡም::  በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በየተለያዩ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸው በሚከታተሉ ተማሪዎች እና መምህራን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና መፍጠሩ እየተነገረ ነው::

በጸጥታ መደፍረሱ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች መካከል የሰሜን ጎጃም ዞን ተጠቃሽ ነው:: ይህም የጸጥታ ችግር በዞኑ በሚገኙ 503 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን መከታተል የነበረባቸው 400 ሺህ 987 ተማሪዎች እና ከአሥር ሺህ በላይ መምህራን እና ሠራተኞች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን መምሪያው አስታውቋል ሲል የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል::

በ2016 ዓ.ም በ115 ትምህርት ቤቶች 38 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ገብተው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ግጭቶች ከፍታውራሪ ሐብተ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጪ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥራ ማቆማቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ ተናግረዋል::

ትምህርት ቤቶቹን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ግጭቶች ባለመቆማቸው እና ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አምነው ባለመላካቸው አለመሳካቱንም ጠቁመዋል:: የሕጻናትን የመማር መብት  ማደናቀፍ ሕገ መንግሥታዊ እና ዓለማቀፋዊ ስምምነቶች ጋር ከመጣረሱ በተጨማሪ በትምህርት ማኅበረሰቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና እያደረሰ ሕጻናትንም ለያለዕድሜ ጋብቻ እና ለጉልበት ብዝበዛ እየዳረገ መሆኑን ገልጸል::

ለትምህርት ዘመኑ የተለያዩ መጻሕፍት እና ወንበሮች፣ ጥቁር ሰሌዳ እና 224 ሺህ 635 አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የሚውል ደብተር ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ጭምር የመምሪያዉ ኃላፊ ጠቁመዋል:: ይሁን እንጅ የሰላም እጦቱ በትምህርት ሥርዓቱ  ትግበራ ላይ ከፍተኛ እክል መፍጠሩን  አስታውቀዋል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሜን ጎጃም እና ባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ የትምህርት አመራሮች ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በገመገመበት ወቅት በከተማ አሥተዳደሩ ከመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ እና 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥራ ማቆማቸው ተመላክቷል::

በቀሪ ትምህርት ቤቶች ግን የስድስተኛ፣ የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የመምሪያው ኃላፊ ኃይለማርያም እሸቴ መግለጻቸውን ከትምህርት ቢሮው የማኅበራዊ ትስስር  ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል:: ተፈታኞችን በዕውቀት፣ በሥነ ልቦና እና በፈተና አወሳሰዱ ላይ የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተመላክቷል::

የሰላም መደፍረሱ በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ትምህርት ተቋማት ላይም የከፋ ተጽእኖ አሳድሯል:: አቶ ታደሰ ሸዋፈራው የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ናቸው:: የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ መፈተኑን ተናግረዋል::፡ የትምህርት ሥራው በታቀደለት ጊዜ እንዳይከናወን ማድረጉንም አንስተዋል::

በዞኑ 119 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖሩን ያስታወቁት ምክትል መምሪያ ኃላፊዉ፣ በዓመቱ በመማር ማስተማር ላይ የሚገኙት 84 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል:: ከ59 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 54 ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል::

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመዝግበው መማር ከነበረባቸው ከ228 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 150ሺ ወይም 66 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እየተማሩ መሆኑን ተናግረዋል:: በሁለተኛ ደረጃም ከ46 ሺህ 635 ተማሪዎች ውስጥ 36 ሺህ፣ በቅድመ መደበኛ ከ73 ሺህ 123 ተማሪዎች በትምህርት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል:: የተማሪ ቁጥሩ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑን ምክትል ኃላፊዉ፣ ያስታወቁት በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት  59ሺ ተማሪዎች ወደ ትምህርት መመለሳቸውን በማስታወቅ ነው::

ዘግይተው ትምህርት በጀመሩ ተማሪዎች ምክንያት የትምህርት የማጠናቀቂያ ጊዜውን ለማራዘም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ምክትል ኃላፊዉ ገልጸዋል:: የማጠቃለያ ፈተና አሰጣጡም እንደ ትምህርት አጀማመሩ በሁለት ዙር እንደሚሰጥ ምክትል ኃላፊዉ አረጋግጠዋል::

ምንም እንኳ የመማር ማስተማር አሰጣጡ በጸጥታ ችግር ክፉኛ የተፈተነ ቢሆንም ትምህርታቸውን በተለያዩ ጊዜያት ጀምረው ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ለክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ይቀመጣሉ:: የሰሜን ሸዋ ዞንም ተፈታኞችን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ፣ የተሻለ ውጤትም ለማስመዝገብ ለሁለት ወራት የሚቆይ የፈተና ዝግጅት ዘመቻ በማስጀመር ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከምስራቅ አማራ ቀጣና የዞን እና የወረዳ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህር ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ  በትምህርት ዘርፉ ላይ ባሳደረው ተጽኖ በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆች እና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ የስነልቦና ጫና እንዳሳደረ ተናግረዋል:: የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በመቋቋም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል::

በትምህርት ዓመቱ ካጋጠመው የሰላም መደፍረስ ባሻገር በተፈጥሮ የአየር ንብረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ፣ የጀመሩትም ትምህርትም እንዳያስቀጥሉ ስለማድረጉ በተደጋጋሚ ተነስቷል:: ታዲያ ቢሮው በድርቅ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የትምህርት ማቋረጥ ለመታደግ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የትምህርት ቤት ምገባ አስጀምሯል:: ኃላፊዋ በመንግሥት በኩል ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ማኅበረሰቡን እና አጋር አካላትን በማስተባበር 224 ሺህ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል::

የጸጥታ ችግሩ ምንም እንኳ የመማር ማስተማር ሥራውን ቢፈትነውም 14 ነጥብ 3 ሚሊዮን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት የታተመ ሲሆን ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው መሠራጨቱም ተመላክቷል:: 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት መጻሕፍትም በትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ ሦስት ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆነው ስለመሰራጨቱ ተገልጿል:: ቀሪውንም በመጭው ክረምት ለማሰራጨት ዕቅድ ተይዟል::

ወቅቱ ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የሚሰጡበት ነው:: በመሆኑም ተፈታኞችን በስነ ልቦና ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት በየአካባቢው ያሉ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች፣ መምህራን እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ተላልፏል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here