ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ ክልል ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተፈጥረዋል። አንበጣ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ግጭት እና መፈናቀል በክልሉ ተከስቷል። እነዚህ ችግሮች መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አስከትለዋል፤ እያስከተሉም ነው። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከትምህርት ቢሮ እና ከሴቶች ህፃናት እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በግጭቱ ምክንያት ማኅበረሰቡ በደረሰበት የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የስነ ልቦና ጫና ዙሪያ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ በሁሉም የማኅብረሰብ ክፍል ግጭቱ ያደረሰውን የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የስነ ልቦና ጫና ምን እንደሚመስል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዳሰሳ ጥናት ተዘጋጅቶ ቀርቧል። በተለይ ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነት ሳያገግም በአማራ ክልል ሌላ ግጭት መቀስቀሱ ችግሩ እንዲባባስ እና አሁንም መቀጠሉ በማኅበረሰቡ ዘንድ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የስነ ልቦና ጫና ማሳደሩን የዩኒቨርሲቲው የዳሰሳ ጥናት አመልክቷል።
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት አራት ሺህ 917 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ከእነዚህ መካከል እስከ ጥር ወር መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ ሦስት ሺህ 805 ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አለማከናወናቸውን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ለዓለም መኩሪያው ተናግረዋል። ይህም የአዕምሮ ጤና ችግር በትምህርት እና ትምህርት ተቋማት ላይ እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት። ጭንቀት፣ ሀዘን፣ ድባቴ፣ የትኩረት ማጣት፣ የእንቅልፍ ማጣት እና የመሳሰሉት ችግሮች በተማሪዎች እና መምህራን ላይ የሚታዩ የአዕምሮ እና የጤና ችግሮች መሆናቸውን ባለሙያው አንስተዋል።
መፍትሄውም ትምህርት ቤቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ትምህርት ቤት ሄደው የሚማሩበት ዕድል መፍጠር ነው ብለዋል። በተጨማሪም ህፃናት የመማር መብታቸውን የትኛውም አካል ማክበር እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሦስት ሺህ 91 ሴቶች እና ህጻናት ጥቃት እንደ ደረሰባቸው የተናግሩት በክልሉ ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያው አቶ አስናቀ ለወየ ናቸው።
ችግሩን ለመቅረፍም በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻቸውን መወጣት እንዳባቸው ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ግጭቶች እና መፈናቀሎች ካልቆሙ በሴቶች እና ህፃናት እንዲሁም በመላው ሕዝባችን የሚደርሰው ሰቆቃ ሊቆም እንደማይችልም አስረድተዋል። ታዲያ በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጥታ የሚሠሩ ተቋማት በጋራ መሥራት አለባቸውም ነው ያሉት ባለሙያው።
ክልሉ ረዘም ላለ ጊዜ ግጭት ውስጥ መቆየቱ፣ ብዙ ተፈናቃይ ያለበት መሆኑ እንዲሁም ወባ እና ኮሌራን በመሳሰሉ ወረርሽኞች እየተጠቃ ያለ መሆኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ አዕምሯዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶችን አድርሷል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በአማራ ክልል ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች የአዕምሮ ጤና እና ስነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ያሉት በአማራ ክልል የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት አደጋ መከላከል እና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ቢረሳው ታዛዬ ናቸው። እንዲሁም ከጥቂት ተቋማት በተገኘ መረጃ ከአምስት ሺህ በላይ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋልም ብለዋል።
በአማራ ክልል በሁሉም ጤና ተቋማት የአዕምሮ ጤና እና ስነ ልቦና ድጋፍ መጀመር እንዳለበት ያነሱት አስተባባሪው፤ ይህን ለማድረግ ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ ግብአት ማቅረብ እና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ያለምንም ተጽእኖ ወደ ክልሉ ገብተው እርዳታ እንዲሰጡ መፍቀድ ያስፈልጋል ብለዋል። ታዲያ ይህን ሥራ ለማከናወን የአዕምሮ ጤና በአንድ ተቋም ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ሊያግዙን ይገባል ነው ያሉት። ግጭቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በርካታ ስዎች የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የስነ ልቦና ጫና ይደርስባቸዋል ነው የተባለው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም