ግጭቱ ያስከተለው ስብራት እና መውጫ መንገዱ

0
84

የውስጥ ግጭት ለአንድ ሀገር ህልውና እና ለሉዓላዊነቷ ትልቁ ስጋት የሚሆነው ለውጪ ጠላቶች እና ለታሪካዊ ተቀናቃኞች ምቹ የጣልቃ ገብነት በር ስለሚከፍት ነው። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ታሪክ በተደጋጋሚ የታዬ እውነታ ነው።

የውስጥ ግጭት ለውጪ ጠላት በር የመክፈቱ እውነታ በተለይ በዘመነ መሳፍንት እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የታዩ ታሪኮች ሁነኛ ማሳያ ስለመሆናቸው “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ልብነ ድንግል እስከ ዓፄ ቴዎድሮስ” የተሰኘው የተክለጻድቅ መኩሪያ መጽሀፍ እና ‘ጆርናል ኦፍ ኢትዮጵያን ስተዲስ’ (JES) ላይ የታተሙ ጥናቶች አስረጂ ናቸው፡፡

በዘመነ መሳፍንት የታየው ውስጣዊ ሽኩቻ ለግብፅ ወረራ በር እንደከፈተ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ በሚጥሩበት ወቅት በውስጥ ያሉ መሳፍንት እና መሪዎች ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ መግባት፣ የአጼ ዮሐንስ አራተኛ መስዋዕትነት እና የደርቡሾች ኢትዮጵያን መውረር ተጨማሪ የውስጥ ግጭት አስከፊ ውጤት ማሳያዎች ናቸው፡፡

አሁንም ያለው የውስጥ አለመረጋጋት ለውጭ ኃይሎች በተለይ የባሕር በር እና የዓባይ ግድብ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሀገራት ትልቅ ዕድል እንደሰጣቸው በተደጋጋሚ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ በፕሮፓጋንዳ እና በሌሎችም ጉዳዮች የኢትዮጵያን አቅም ለማዳከምም ሲጣጣሩ ይታያሉ።

በአጠቃላይ የውስጥ ሰላም የሀገር ሉዓላዊነት ዋናው ምሰሶ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የውስጥ ልዩነቶች በንግግርና በድርድር ካልተፈቱ፣ የግል ጥቅማቸውን ለሚያሳድዱ የውጭ ኃይሎች በር ይከፍታል።

በግጭቶች ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገው በጀት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር ካለው ዓመታዊ ገቢ ጋር ሲነጻጸር ትልቅ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

እንደ የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት መረጃዎች ከሆነ ግጭቶች የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦትን ከመገደብ ባለፈ የውጭ ምንዛሪንም ያሳጣሉ፡፡ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚመረቱ ምርቶች (ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ እና ቡና ምርቶች) ወደ ውጭ እንዳይላኩ በማገድ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ያሳጣታል፡፡ የጉብኝት መዳረሻዎች እንዲቀዘቀዙ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስም ምክንያት ሆኗል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች ጦርነትና አለመረጋጋት ባለበት ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ አይፈልጉም፤ እንዲያውም ያሉትም ስጋት ውስጥ ስለሚገቡ ሥራቸውን ያቆማሉ። ይህም የውጪ ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ በማድረግ በምርት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡

የምርት ሰንሰለት እንዲቋረጥ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ያባብሰዋል፡፡ ዋና ዋና መንገዶች በግጭት ምክንያት ሲዘጉ፣ ምርቶች ከሚመረቱበት ወደ ተጠቃሚው አካባቢ መግባት አይችሉም። ይህም በከተሞች የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል።

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ከቀዬው ሲፈናቀል ወይም ማዳበሪያ በወቅቱ ሳይደርሰው ሲቀር ምርት ይቀንሳል። ይህም ሀገሪቱ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ (ስንዴ፣ ዘይት…) በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከሌሎች ሀገራት እንድትገዛ ያስገድዳታል፡፡

በተመሳሳይ በግጭት ወቅት በሕጋዊ ባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጪ ምንዛሪ ልዩነት ይሰፋል። ዶላር በቤት ውስጥ እንዲከማችም ምክንያ ይሆናል፤ ይህም በገበያው ውስጥ የዶላር እጥረት እንዲፈጠርና የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲዳከም ያደርጋል።

የግጭትን ዘርፈ ብዙ አውዳሚነት በመረዳት ታዲያ ለመፍትሔው መረባረብ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ግጭት እና የሰላም እጦት ይዞት ከሚመጣው ዘርፈ ብዙ መዘዝ ለመውጣት የመመካከር እና የመደራደር ባሕል ሊያድግ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ10ኛ መደበኛ ሥብሠባው ላይ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ የምክር ቤት አባላት ያለፉት ዓመታት ግጭቶች ያደረሱትን ጉዳት፣ ከችግሩ ለመውጣት የተደረጉ ጥረቶችን እና ቀጣይ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ምን መደረግ አለበት በሚል ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሰላም እጦቶችን ለመፍታት በተደጋጋሚ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር እውነተኛ ድርድር እንዲደረግ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የንጹሃን ጥቃት እንዲቆም ላለፉት ሥስት ዓመታት እንዲደረግ ሲጠየቅ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

መንግሥት ቀደም ብሎ ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር በቅርቡ ደግሞ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ መሪዎች ጋር ድርድር መደረጉን ያነሱት የማክር ቤት አባላቱ ነገር ግን ከአንጻራዊነት በዘለለ በዘላቂነት ሰላምን ማጽናት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታታት ደግሞ በተለይም በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጠቂ ኃይሎች ጋር የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ሀሳቦች እና ጥያቄዎችም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል፡፡ “በሰላም እጦት እንድንኖር ካደረጉን እና ካልተላቀቅንባቸው ምክንያቶች መካከል ዋናዎቹ ልዩነቶችን በኃይል ብቻ  የመፍታት እንዲሁም ከጥንት የመጣ የባንዳነት ልምምድ እና የጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ካደገች የሚል ያልተቋረጠ ስጋት ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭቶች በዛሬዎቹ ሕጻናት እና በነገዎቹ ሀገር ተረካቢዎች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ “አሁን ባለው ዓለም ውስጥ ልጆችን ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የከለከለ ታጋይ እና ነጻ አውጭ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሚሆን ማሰብ በቂ ነው፤ ይህም አደገኛ ስብራት ነው፤ መግራት እና ማስተካከል ያስፈልጋል” ብለዋል።

እንደ ሀገር እያጋጠሙ ላሉ ተደጋጋሚ የጸጥታ መደፍረሶች ውይይት ዋናው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “መልካም ውይይት ከመኝታ ይበልጣል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በመወያየት ውስጥ ብዙ ያላየናቸው እና የማናውቃቸው ስብራቶች ይጠገናሉ” ነው ያሉት፡፡

አሁን ያለውን የውስጥ ግጭት ለመፍታት ከታሪካዊ ስህተቶቻችን መማር እና ዘላቂ መፍትሔ ላይ ማተኮር ይገባልም ተብሏል። በጦርነት የሚገኝ ፍጹም ድል እንደሌለ ተረድቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት (መንግሥትን፣ የታጠቁ ኃይሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አረና የሲቪክ ማኅበራትን) ያሳተፈ ውይይት ማድረግ ደግሞ መፍትሔው ነው፡፡

የቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምላሻቸው “የትውልዱ ዋና ተልዕኮ በውይይት ሀገረ መንግሥት የመሥራት ሊሆን ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ለዚህም የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደት ነፃ፣ ገለልተኛ እና ሁሉንም ድምፆች የሚያካትት እንዲሆን በማድረግ የቆዩ የታሪክ እና የፖለቲካ ቂሞችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የተረጋጋች እና ለልጆቻችን የምትመች ሀገር ማስረከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡ “እስካሁን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ በርካታ ወገኖች ሰላምን ቀዳሚ ጉዳያቸው አድርገው እየተመለሱ ነው”ም ብለዋል፡፡ ይህም ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለው አረዳድ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በበርካታ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች እየተመለሱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገልጹም ተፈናቃይን መያዣ ያደረገ ፖለቲካ ግን አሁንም ፈተና መሆኑን አንስተዋል፡፡ የወልቃይት አካባቢ የማንነት ይገባኛል ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ዴሞክራሲያዊ እና ህገ መንግሥታዊ አካሄድ በሆነው ሕዝበ ውሳኔ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ ማንኛውም የሥልጣን ወይም የፖለቲካ ጥያቄ ሀገርን በማፍረስ ሊመለስ እንደማይችል በመረዳት እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሠሩ ካሉ ተግባራት በተጨማሪ የታጠቁ ወገኖች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡

መንግሥት ሁሌም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን እና ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። የታጠቁ ኃይሎችም የሰላም አማራጭን መቀበል፣ የንጹሃን ዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እና ጥያቄዎችን በፖለቲካዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባቸው ነው የተመላከተው፡፡

በተመሳሳይ የፖለቲካ መሪዎች ከጥላቻ ንግግር መቆጠብ፣ የጋራ ሀገራዊ ዕሴቶች ላይ ማተኮር እና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ይገባቸዋል፡፡

ምሁራን እና የሃይማኖት አባቶች እውነትን መናገር፣ ሕዝቡን ማስተማር እና ገላጋይ በመሆን ግጭቶችን ለማርገብ መሥራት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አብዝታ የምትሻው ጉዳይ ነው፡፡

እያንዳንዱ ዜጋም ልዩነቶችን በትዕግሥት በማስተናገድ እና ለሰላም ዘብ በመቆም ለዘላቂ ሰላም መረጋጋጥ የበኩሉን ሊወጡ ይገባል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here