የዓለም ጤና ድርጅት የአዕምሮ ጤንነት እያንዳንዱ ግለሰብ ስለ እራሱ ወይም ስለ እራሷ ያላቸውን ችሎታና አቅም ማወቅ፣ በሕይወት የሚያጋጥምን የኑሮ ጫና መቋቋም መቻል፣ ውጤታማ እና ፍሬ ያለው ሥራ ማካሄድ መቻል፣ እናም ለእርሱ ወይም ለእርሷ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ለማድረግ አቅምን ማወቅ ማለት ነው ሲል ትርጉም ሰጥቶታል።
ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ ከአዕምሮ ጤንነት ጋር የተዛመደ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። አስፈላጊውን የማኅበረሰብ እና የስነ ልቦና ባለሙያ ድጋፍ ካገኙ ግን ብዙዎቹ እነዚህን ችግሮች ይወጣሉ። ከችግራቸው በማገገም ውጤታማና ጤናማ ሕይወትንም ይኖራሉ።
የድርጅቱ መረጃ እንደሚጠቁመው አሰቃቂ ክስተቶችን ማየት ወይም ማስተናገድ የአዕምሮ ጤና የመታወክ አጋጣሚን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። የሚወዱትን ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ እና በድንገት በሞት ማጣት ረዘም ላለ ጊዜ ለሀዘን እና ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች እንዲፈጠሩ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በሥራ ወይም በገቢ ማጣት ምክንያት የገንዘብ እና የእርዳታ እጦት ስሜትን ይፈጥራሉ። ይህም ቀጣይነት ያለው ጭንቀት እና ድብርት ያሉ ሁኔታዎችን የመፍጠር አደጋን ያባብሳል። የአዕምሮ ጤናን እና ደኅንነትንም ይጎዳል።
በዚህ ሳምንት በጤና አምዳችን ግጭት እና የአዕምሮ ጤናን በተመለከተ ከወራቤ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው ጋር ቆይታ አድርገናል፣ መልካም ንባብ::
ባለሙያው እንደሚሉት የአዕምሮ ጤና ጤናማ አስተሳሰብ እና ጤናማ የሆነን ባሕርይን የሚመለከት ነው:: የአዕምሮ (አንጎል) ጤና የሚጎዳባቸው ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ የገለጹት ዶክተር እስጢፋኖስ ስነ-ሕይዎታዊ ምክንያቶች አንደኛው ስለመሆኑ ያነሳሉ፤ አንጎል ላይ የሚደርስ አደጋ፣ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (ስትሮክ) እና የሚጥል ሕመም የአዕምሮ ጤናንን ይጎዳሉ ነው ያሉት::
ባለሙያው ማብራሪያቸውን እንዲህ ይቀጥላሉ፤ አደንዛዥ እጾች የአንጎልን የመልዕክት የማስተላለፍ ሥርዓትን (Neurochemical messaging system) በማዛባት ተጓዳኝ የአዕምሮ ጤና እክል ሊያደርሱ ይችላሉ:: ለአብነትም የአንጀት መቆጣት ያለበት ሰው ለጭንቀት እና ለሌሎች የአዕምሮ በሽታዎች ሕመም ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው::
በተመሳሳይ የአካላዊ ጤንነት መጓደል በራሱ የአዕምሮ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ነው ዶክተር እስጢፋኖስ ያብራሩት::
በሁለተኛነት ያነሱት የአዕምሮ ጤና መታወክ መንስኤ ደግሞ ስነ ልቦናዊ ምክንያቶችን ነው:: እነሱም ኢኮኖሚያዊ ችግር፣ አስተዳደግ ላይ የሚያጋጥሙ አስደንጋጭ አዕምሯዊ ክስተቶች (ትራውማ) እና በልጅነት ጊዜ የደረሰ ጉዳት (ቻይልድ ትራውራማ) የአዕምሮ ሕመም አጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው:: ጦርነት፣ መፈናቅል፣ የአዕምሮ ሕመም፣ ማሕበራዊ ችግሮች፣ ድህነት እንዲሁም ትዳር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለአዕምሮ መታወክ ተጠቃሽ ናቸው::
በአካባቢው ሁኔታ እና በመንፈሳዊ እምነት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ደግሞ በሦስተኛ ምክንያትነት የጠቀሷቸው ናቸው::
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው እንደሚሉት ከግጭት እና ጦርነት ውስጥ ካለፉ ከዓለማችን አምስት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጥመዋል:: በኢትዮጵያ ደግሞ ከሦስት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤናው የታወከ ነው:: ጦርነት ሲከሰት ስነ-ልቦናዊ ሕመም ያጋጥማል:: ለነዚህ ሰዎች ስነ ልቦናዊ (ሳይኮሎጂካዊ) የሆኑ መሠረታዊ እርዳታዎች ሊቀርብላቸው ይገባል::
ከጦርነቱ በፊት የአዕምሮ ሕመም የነበረባቸው ሰዎች ጦርነት ሲያጋጥማቸው አዕምሯቸው ሥራ ያቆማል:: ሰው ሲገደል ማየት፣ መፈናቀሉ ከዚያም እርዳታ ቶሎ አልቀርብ ሲል፣ ወላጆች ልጆቻችን ምን ይበላሉ?፣ ይጠጣሉ? በሚል ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ:: ጦርነቱ ካለፈ በኋላ ያሳለፉትን ነገር በማስታወስ አዕምሯቸው ይታወካል::
ግጭት ወይም ጦርነት ወደ ሥር የሰደደ ውጥረት፣ ጭንቀት እና ድብርት በማምራት የአዕምሮ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራል:: በጦርነት ጊዜ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ለጥቃት መጋለጥ፣ መሸማቀቅን ያስከትላል:: እንዲሁም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል:: የመንፈስ ጭንቀትም ሊያስከትል ይችላል። የቤተሰብ አባላት ወይም የጓደኛ ሞትም ከአቅም በላይ የሆነ ሀዘን እና ጉዳት ሊፈጥር ይችላል። ይህ ሁሉ ለአዕምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል:: እነዚህም አንዳንድ ጊዜ ራስን ከማጥፋት ጋር ሊያያዙ ይችላሉ።
ጦርነት ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል የአዕምሮ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑ ነው። በአጠቃላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጦርነት እና ግጭት ውስጥ ባሉ ማኅበረሰቦች የአዕምሮ መታወክ በሽታዎች መከሰት እና መስፋፋት ጨምረዋል።
ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በጦርነት ይጠቃሉ። በጥቅሉ አረጋዊያን፣ ሴቶች እና ሕጻናት በግጭት ጊዜ ለሚከሰት የአዕምሮ ጤና እክል ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው:: ለጦርነት የሚሠማሩም የድሕረ አዕምሮ ጤና መታወክ ይደርስባቸዋል::
ዶ/ር እንዳላማው እንደሚሉት በግጭት የሚፈጠርን የአዕምሮ ጤና መታወክን ለመጠበቅ (ግጭት ወይም ጦርነት ሰው ሠራሽ ስለሆነ) አስቀድሞ መከላከል ይቻላል:: ከተከሰተ ደግሞ የሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ማከም ይቻላል:: የሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት:: በመሆኑም ሰው ሠራሽ ጦርነትን ማስቀረት እና መከላከል ተገቢ ነው:: መሠረታዊ ፍላጎቶች( ምግብ፣ ውኃ፣መጠለያ..) እንዲሟሉላቸው ማድረግም ይገባል:: በተቻለ መጠንም የአዕምሮ ጤናቸው እንዲመለስ ከስነ አዕምሮ ባለሙያ ጋር በማገናኘት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ሙያዊ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል::
ጤና አዳም
* የአዕምሮ ጤና መታወክ በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችን፣ በድርጊታችን እና በሕይወታችን ውሳኔዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
* ከዓለም አቀፍ የበሽታዎች ሸክም 14 በመቶ የሚሆነውን የአዕምሮ ሕመም ይይዛል።
*በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም የተለመዱት የአዕምሮ ሕመሞች ድብርት፣ ጭንቀት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ ከአሰቃቂ ጭንቀት በኋላ እፅ አላግባብ መጠቀም እና ሌሎችም ናቸው።
* አንዳንድ የአዕምሮ ሕመሞች በአንዳንድ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እያዛለሁ የሚል ስጋትን በመጨመር ረገድ ሚና አላቸው።
* የአዕምሮ ጤንነታችንን መንከባከብ ያለብን አካላዊ ጤንነታችንን በመንከባከብ፣ በቂ እንቅልፍ በመተኛት፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ጨምሮ በተለያዩ ተግባራት በመሳተፍ ነው::
* ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ሊገጥማቸው እንደሚችል ማወቅ አለባቸው::
* የአዕምሮ ሕመም ብዙውን ግዜ በሕክምና ሊድን እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


