ሁለት ዓመታትን ሊደፍን በጣት የሚቆጠሩ ወራቶች የቀረው የአማራ ክልል ግጭት የበርካታ ንጹሀን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል፣ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ አድርጓል፤ ማኅበረሰቡ እንደ ልብ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በንግድ ሥራው፣ በማህበራዊ ሕይወቱ… ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በጤና ሥርዓቱ ላይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ጉዳት ደርሷል።
“ከድጡ ወደ ማጡ“ እንደሚባለው ከባለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በክልሉ የተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርገውታል። የሰሜኑ ጦርነት ካስከተለው ከባድ ሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ በክልሉ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ አንበጣ እና የመሳሰሉት ተፈጥሯዊ አደጋዎች ደርሰዋል፤ እየደረሱ ነው። ይህ ተደራራቢ ችግር በማኅበረሰቡ ዘንድ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና አሳድሯል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ ከትምህርት ቢሮ እና ከሴቶች ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በግጭቱ ምክንያት ማኀበረሰቡ በደረሰበት የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ዙሪያ ባለፈው ወር መገባደጃ በባሕር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዶ ነበር፡፡
በመድረኩ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ በሁሉም የማኅብረሰብ ክፍል ግጭቱ ያደረሰው የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ምን እንደሚመስል በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በተለይ ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነት ሳያገግም በአማራ ክልል ሌላ ግጭት መቀስቀሱ እና አሁንም ድረስ መቀጠሉ በማኅበረሰቡ ዘንድ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ማሳደሩን ዩኒቨርሲቲው ያደረገው የዳሰሳ ጥናት አመልክቷል።
ግጭቱ በአብዛኞቹ ቦታዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን አስተጓጉሏል። በጥናቱ መሰረት በግጭቱ ምክንያት 4 ሺህ 917 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው አንዳንዶቹ ለተፈናቃይ መጠለያ ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥ 3 ሺህ 805 ትምህርት ቤቶች እስከ ጥር ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ምዝገባ አለማከናወናቸውን በክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያው አቶ ለዓለም መኩሪያው ተናግረዋል።
ትምህርት ባለባቸው ቦታዎችም ቢሆን ተማሪዎች ለትምህርት የተዘጋጀ የነቃ አዕምሮ እንደሌላቸው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎች የሚያዩት እና የሚሰሙት ነገር ለትምህርት ዝግጁ ሊያደርጋቸው ቀርቶ የደህንነት ስሜት እንዳይሰማቸው እያደረጋቸው መሆኑም ነው ባለሙያው የተናገሩት።
ተማሪዎች መንገድ ላይ እና ትምህርት ቤት ውስጥ ‘ችግር ይገጥመናል‘ የሚል ትልቅ ስጋት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል። ይህም የአዕምሮ ጤና ችግር በትምህርት እና ትምህርት ተቋማት ላይ እንዲፈጠር ማድረጉን አቶ ለዓለም ጠቁመዋል።
ጭንቀት፣ ሀዘን፣ ድባቴ፣ የትኩረት እና የእንቅልፍ ማጣት…ችግሮች በተማሪዎች እና መምህራን ላይ የሚታዩ የአዕምሮ እና የጤና ችግሮች መሆናቸውንም ባለሙያው አንስተዋል። በእነዚህ ወገኖች የደረሰው የአዕምሮ ጤና መታወክ የሥነ ምግባር ችግር አምጥቶባቸዋል፤ እርስ በእርሳቸው እና ከመምህራን ጋርም እንዳይግባቡ አድርጓቸዋል።
በተለይ መምህራን በገጠማቸው ከፍተኛ የሥነ አዕምሮ እና የሥነ ልቦና ችግር ከማንበብ፣ ከመጻፍ እና ከመመራመር ተግባራቸው ተነጥለዋል። ክፍል ውስጥም ለተማሪዎቻቸው እውቀት ለመስጠት የአዕምሮ ዝግጁነት እንደሚጎድላቸው የትምህርት ባለሙያው አስረድተዋል።
እነዚህ ችግሮች የትምህርት ጥራቱን እየጎዱት እንደሆነ ነው አቶ ለዓለም የተናገሩት። ግጭቱ አሁንም መቀጠሉ ደግሞ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀውሱን ሽሽት አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፤ ላለ እድሜ ጋብቻም ተዳርገዋል።
እንደ አቶ ለዓለም ማብራሪያ ችግሮችን ለመፍታት ለተማሪዎች እና መምህራን የሥነ የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና ክትትል ያስፈልጋቸዋል። በትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪ ከተማሪ፣ መምህራን ከመምህራን የሚረዳዱበት እና የሚደጋገፉበት አደረጃጀቶች መፈጠር አለበት፡፡ ሀብት እና የምክር አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውም ተማሪዎች ተለይተው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ትምህርት ቤቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው የሚማሩበት ዕድል መፈጠር እና ሕፃናት በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የመማር መብት የትኛውም አካል ማክበር እንዳለበት አቶ ለዓለም አጽንኦት ሰጥተዋል። ከዚህ ባለፈ ትምህርት ቤቶች ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ መሆናቸውን ለተማሪዎች እና ለወላጆች ማስገንዘብ የሁሉም ባለድርሻ አካል ተግባር መሆኑንም ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ ከ100 ሺህ በላይ መምህራን በአዕምሮ ጤና መቃወስ እና በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዳሉ የተናገሩት ባለሙያው፤ ተቋማቸው መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር መምህራን ከገጠማቸው የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና እንዲላቀቁ ሥልጠና ጀምሯል። የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ተማሪዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲመለሱ ትምህርት ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገር መሆኑም ተገልጿል።
በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በነበረው የኮርኖና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና የአማራ ክልል ግጭት በርካታ ሴቶች እና የተለየ እንክብካቤ የሚሹት ሕጻናት ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ተጎድተዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሴቶች እና ሕጻናት ከመፈናቀል ጀምሮ አካላዊ፣ ሥነ ልቦና እና ጾታዊ ጥቃቶች ደርሰውባቸዋል። ከ700 ሺህ በላይ ሴቶች እና ሕጻናት ባለፉት አምስት ዓመታት ጥቃት እና ጉዳት እንደደረሰባቸው የዳሰሳ ጥናቱ ያመለክታል። ከደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በተጨማሪ በርካታ ቁሳዊ ውድመትም ደርሷል።
የአማራ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰበት 2015 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ ብቻ ከሦስት ሺህ በላይ ሴቶች እና ሕጻናት የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ክልሉ ረዘም ላለ ጊዜ ግጭት ውስጥ መቆየቱ፣ ብዙ ተፈናቃይ ያለበት መሆኑ እንዲሁም ወባ እና ኮሌራን በመሳሰሉ በተለያዩ ወረርሽኞች እየተጠቃ ያለ መሆኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚደርሰውን አዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አስከፊ አድርጎታል።
ከችግሩ እንዲያገግሙ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ የተናገሩት በክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያው አቶ አስናቀ ለወየ ናቸው። የማገገሚያ ማዕከል በማቋቋም ሴቶች እና ሕጻናት ከገጠማቸው የሥነ አዕምሮ እና የሥነ ልቦና ችግር አገግመው እንዲወጡ እየተደረገ እንደሚገኝም ባለሙያው አብራርተዋል።
ሀብት እና ንብረት የወደመባቸውንም መልሶ በማቋቋም ተጠቃሚ እየሆኑ ነው የተባለው። ግጭቶች እና መፈናቀሎች ካላቆሙ በሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም በመላው ሕዝብ የሚደርሰው ሰቆቃ ሊቆም እንደማይችል ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በአማራ ክልል ከ60 ሺህ በላይ ሕዝብ የአዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት አደጋ መከላከል እና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ቢረሳው ታዘብ ናቸው።
እንደ አስተባባሪው ገለጸ ከጥቂት ተቋማት በተገኝ መረጃ በርካታ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ራሳቸውን ባጠፉ እና ሙከራ ባደረጉ ሰዎች ላይም በተደረገ ጥናት ከ10 ሺህ ሰዎች በላይ ራሳቸውን ለማጥፋት መሞከራቸው ከጤና ተቋማት የተገኘው ሪፖርት ያመለክታል።
በጤና ተቋማት የግብዓት እጥረት መኖሩ፣ በአብዛኞች የጤና ተቋማት የሥነ ልቦና ባለሙያ አለመኖር ችግሩን ለመቅረፍ እንቅፋት ሆኗል። ይህን ለማድረግ ባለሙያዎችን ማሠልጠን፣ ግብዓት ማቅርብ እና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ያለምንም ተጽእኖ ወደ ክልሉ ገብተው እርዳታ እንዲሰጡ መፍቀድ እንደሚያስፈልግ አስተባባሪ ጠቁመዋል።
ግጭቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በርካታ ስዎች የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና እንደሚደርስባቸው የዳሰሳ ጥናቱ መረጃ ያመለክታል። ታዲያ ይህን ችግር የሚያቃልል ሥራ ለማከናወን የአዕምሮ ጤና በአንድ ተቋም ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላትም ሊያግዙ እንደሚገባ አቶ ቢረሳዉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም