በባሕር ዳር ከተማ ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያንን እልፍ ብሎ ባለው መንገድ በቀኝ በኩል ብዙ ሳንጓዝ በእግረኛ መንገዱ ላይ ሁለት ልጆቿን በመያዝ ጫማ የምታሳምር ሴት ተመለከትን፡፡ ባለታሪካችንን በነሐሴ ወር ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም የፈለገ አንድ ግለሰብ ደግሞ ጫማውን ሲያስጠርግ ልጆቿ ሲረብሹ ተመልከቶ ልጆቿን በማዋል ሊያግዙ የሚችሉ አካላት አይተው ድጋፍ እንዲያደርጉላት በሚል በማኅበራዊ ሚዲው መነጋገሪያ አድርጓት ነበር – ወ/ሮ ሃይማኖት ተገኝን፡፡
በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል እንደምትገኝ የገለፀችልን ወ/ሮ ሃይማኖት ትውልድ እና እድገቷ ደቡብ ጎንደር አካባቢ ነው፡፡ ከ27 ዓመት በፊት የቤተሰቧን ሕይወት ለመቀየር ወደ ባሕር ዳር እንደገባች ታስታውሳለች፤ ያኔ በቤት በሠራተኝነት በመቀጠር የባሕር ዳር ኑሮዋን ጀመረች፡፡ ለዓምስት ዓመታትም በአንድ ቤት ሠራች፡፡
የወ/ሮ ሃይማኖትን ሥራ ወዳድነት፣ ታማኝነት፣ ቅንነት የተመለከቱ አሠሪዎቿ እንደልጆቻቸው ያስቡላት ስለነበር ከአምስት ዓመት በላይ እንድታገለግላቸው አልፈለጉም፤ የራሷን ኑሮ እንድትጀምር በማሰብ ከመረጡላት ሰው ጋር ትዳር መሠረተች፡፡
በአሠሪዎቿ መልካም ምኞት የተጀመረው የትዳር ሕይወት በልጅ ደመቀ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ በተጀመረው ትዳር መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ በፍቺ ተጠናቀቀ፡፡ ወ/ሮ ሃይማኖት ልጇን ለባለቤቷ ሰጥታ እሷ የእለት ጉርሷን ፍለጋ መንገድ ላይ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ጎመን… በመሸጥ ሕይወቷን መምራት ቀጠለች፡፡
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ወ/ሮ ሃይማኖት ሌላ ትዳር መሰረተች፤ ሁለት ልጆችንም አፈራች፡፡ እርሷ የቤቱን ባለቤቷ ደግሞ በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ በጥሩ መንገድ መምራት ቻሉ፡፡ የጥንዶቹ ኑሮ ግን እንደ ጅምሩ አልቀጠለም፡፡ ባለቤቷ የባጃጅ መንጃ ፈቃዱን ለማደስ በወጣበት አጋጣሚ በተነሳ ግጭት እንደ ወጣ ሳይመለስ ቀረ፡፡ የሷ እና የልጆቿ ኑሮ ፈተና ገጠመው፡፡
“የተወሰኑ ጊዜያት ቤት ውስጥ ያለውን እቃ በመሸጥ መቆየት ብችልም በዘላቂነት ግን የልጆችን ፍላጎት ፣ የቤት ኪራይ እና ምግብ መሸፈን የማይቻል በመሆኑ በትንሹ መፋቂያ በመያዝ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መሥመር በመዟዟር መሸጥ ጀመርሁ” ትላለች፡፡
ወ/ሮ ሃይማኖት እንደምትለው ሲገኝ በቀን 50 ብር አንዳንዴ ደግሞ ምንም ገንዘብ ሳታገኝ የምትገባበት ቀን እንደ ነበር ዛሬ ታስታውሳለች፡፡ የጎዳና ላይ ንግዱም እንደልብ የማይሠራ በመሆኑ ሌላ ሥራ ለመሥራት ስታስብ የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ኮርፓሬሽን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ በመታወቂያ ብቻ አምስት ሺህ ብር እንደሚያበድር ሰማች፡፡ በዚያን አጋጣሚም ወደ ተቋሙ በማቅናት ብሩን በመቀበል ወደ ጫማ ማሳመር ሥራ ገባች፡፡
የሥራው ልምድ ባይኖራትም ሰዎችን በመመልከት ሥራውን ሥትጀምር የተወሰነ ስህተት ቢኖርም በየቀኑ በማሻሻል ቤት ተከራይታ ኑሮን መግፋት ጀመረች፡፡ ልጆችን የምታቆይበት ቦታ ስለሌለ ትንሿን ልጇን በማዘል እስከ ማታ የሚቆዩበትን ምግብ በመያዝ ወደ ሥራ ቦታዋ ትመጣለች፡፡ “ሁለቱም ገና ሕፃናት በመሆናቸው በሥራ ላይ እያለሁ ምግብ ወይም ረፍት ፈልገው የሚበጠብጡበት ጊዜ ብዙ ነው፤ አንድ ደንበኛ ጫማ ማሳመር ላይ ባለሁበት አጋጣሚ ይሄንን በሀዘኔታ ከተመለከተ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየውን ፎቶ አንስቶ ለተጠቃሚው አጋራ” በማለት ችግሯን እንዳሳወቀላት ገለፀችልን፡፡
“ጤነኛ በመሆኔ የማንንም እገዛ ሳልጠይቅ አሁንም ወደ ፊትም መሥራት እችላለሁ” የምትለው ባለታሪካችን ልጆችን ይዞ ጎዳና ላይ መዋሉ ግን በርካታ ፈተና እንዳለው ነው የምትገልፀው፡፡ “አንድ ቀን ሥራ ላይ እያለሁ ልጄ ሕፃናት ‘ዳቦ ግዙልኝ?‘ እያሉ ሲለምኑ ትኩር ብሎ አይቶ ‘እማዬ እኔም ዳቦ ግዙልኝ ልበል?‘ ብሎ ሲጠይቀኝ በጣም ነበር የተሰማኝ፡፡” በማለት አጋጣሚውን ስታነሳ ጎዳና ላይ ክፉ ደጉን የሚመለከቱበት በመሆኑ ልጆችን አንፆ ለማሳደግ ከባድ ቦታ እንደሆነ ነው የምትገልፀው፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ መታየቷን ሰዎች መጥተው እስኪነግሯት አለማወቋን የገለፀችው ወ/ሮ ሃይማኖት፤ መረጃውን የተመለከቱ ሰዎች አልባሳትን እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንደለገሷት ነው የገለፀችው፡፡
የወ/ሮ ሃይማኖት ችግር ከማህበራዊ ሚዲያ የተመለከተው ዝግባ የሕፃናት እና አረጋዊያን መርጃ ድርጅት ቤተሰቧን በንግዱ ዘርፍ እንድትመራ ያደረገላትን የ10 ሺህ ብር ልባሽ/ቦንዳ/ ልብስ ድጋፍ መነሻ በማድረግ በእሁድ ገበይ/በሰንደይ ማርኬት/ በመሸጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ መርጃ ማእከሉ ሁለት ዓመት ያልሞላትን ልጇንም ቀኑን ሙሉ ምግቡን ሸፍኖ ማዋል የሚችልበትን እድል ፈጥሮላታል፡፡
ወ/ሮ ሃይማኖት ሠርታ ለመለወጥ የምታደርገው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ ያደረጉላትን ሁሉ አመስግናለች፡፡ ወደፊት በእሁድ ገበያ እና በጫማ ማሳመር ሥራዋ ጠንክራ በመሥራት ልጆቿን ቁምነገር ማስያዝ እና ገቢዋን ማሳደግ እንደምትፈልግም ተናግራለች፡፡
ማናት
ካትሪን ናካሌምቤ
ካትሪን ናካሌምቤ (ዶ/ር) ከመካኒክ አባቷና ምግብ ቤት ከምታስተዳድረው እናቷ የተወለደችው በኡጋንዳዋ ዋና ከተማ ካምፓላ ነው። ከእህቶቿ ጋር ባድሜንተን መጫወት ታዘወትር ነበር። ሕልሟም በስፖርት ሳይንስ ዲግሪ መጫን ነበር። ነገር ግን ያለሽ ውጤት በታዋቂው የማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ክፍል ለመግባትና ለመማር አይበቃም ስትባል ወደ ኢንቫይሮንሜንታል [የአካባቢ] ሳይንስ ክፍል አቀናች።
ትምህርቷን ለመማር ያግዛት ዘንድ ለኡጋንዳ ዱር እንስሳት ባለሥልጣን ለመሥራት አመለከተች።
“ካርታ ማጥናት እወድ ነበር” የምትለው ካትሪን ለመጀመሪያ ጊዜ ካርታ ለማጥናት ተራራ ላይ ወጥታ የተሰማትን ሐሴት አትዘነጋውም። አሁን በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ውስጥ እየተዘዋወረች ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስለ ምግብ ዋስትና ምክር የምትለግሰው ካትሪን በወቅቱ የማስተርስ ድግሪዋን ለመማር ለጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ማመልከቻ አስገባችና እድሉን አገኘች። ሁለተኛ ዲግሪዋን እንደጨረሰች ደግሞ የዶክትሬት ድግሪዋን ለመከታተል እዚያው አሜሪካ ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ገባች።
አሁን በምድራችን ቀዳሚ ከሚባሉት የህዋ ምርምር ተቋማት አንዱ በሆነው የአሜሪካው ናሳ ውስጥ ሳይንቲስት ናት።ሳይንቲስቷ ካትሪን (ዶ/ር) የእራሷን ተሞክሮ መሰረት አድርጋ ወጣት ጥቁር ሴቶች ወደ አካባቢ ሳይንስ ጥናት እንዲገቡ ምክር ትለግሳለች።
በአሜሪካው ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ሳይንስ ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ካትሪን (ዶ/ር) የሳተላይት ምስል ተጠቅማ ግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥን ታጠናለች።
ከሳተላይት የሚገኘው ምስል መሬት ካለው መረጃ ጋር ተዳምሮ የሰብሎችን ቀመር የሚያጠና ቴክኖሎጂ ለመሥራት ይውላል።
ካትሪን (ዶ/ር) በዚህ ሥራዋ ነው እ.አ.አ የ2020 ‘የአፍሪካ ፉድ ፕራይዝ’ ሽልማትን ከቡርኪናፋሶው አንድሬ ባቲዮኖ (ዶ/ር) ጋር የተጋራችው። ካትሪን (ዶ/ር) በአሁኑ ጊዜ ናሳ ውስጥ የአፍሪካ ምግብና ግብርና ፕሮግራም ኃላፊ ናት። ምንጭ ቢቢሲ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም