ጠላቂዎቹ ባለክብረ ወሰኖች

0
111

ካናዳዊው ስቴቨን ሀኒንግ ከሞዴል ባለሙያዋ ሲያራ አንቶስኪ ጋር በባህር ውስጥ 50 ሜትር ጥልቀት ለ52 ደቂቃ ፎቶ ግራፎችን በማንሳት አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

ፎቶግራፍ አንሺው ባለሙያ ስቴቨን ሀኒንግ ከረዳት አጋሮቹ ጋር በሰኔ 2021 እንዲሁም በመስከረም ወር 2023 እ.አ.አ በ30 ሜትር ጥልቀት ለክብረ ወሰን ቢበቃም፣ በታህሣስ ወር 2023 በካናዳዊው ኪም ብሩኒ እና ፒያ  በ40 ሜትር ጥልቀት የተነጠቀውን ክብረ ወሰን ማስመለስ ችሏል፡፡

ፎቶ ግራፍ አንሺው ስቴቨን ላስመዘገበው አዲስ ክብረ ወሰን የተለያዩ እገዛ እና ድጋፍ ያደረጉለት አጋሮቹ ጥምር ውጤት መሆኑንም ነው ያረጋገጠው፡፡ ከሁሉም በላይ የሞዴል ባለሙያዋ ሲያራ አንቶስኪ 50 ሜትር ጥልቀት ላይ ለሚደረገው ቀረፃ ብቁ ትሆን ዘንድ ቅድመ ስልጠና በተለያዩ የውኃ ገንዳዎች ውስጥ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡

በአሜሪካ ፍሎሪዳ በሀይድሮ አትላንቲክ ባህር ፓምፓኖ ዳርቻ ታህሳስ 19/2024 በዚሁ ባህር ዳርቻ የሰመጠ መርከብን ዳራ በማድረግ አስገራሚ እና አስደናቂ ፎቶ ግራፎችን ለረጅም ሰዓት ወስዶ በማንሳቱ ነው ክብረ ወሰኑን ያገኘው- ስቴቨን ሀኒንግ፡፡ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ለመስፈርም ዝቅተኛው የቆይታ ጊዜ 15 ደቂቃ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ፎቶ ግራፍ አንሺው ስቴቨን ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ በአጋሮቹ  የብርሃን፣ የመተንፈሻ ኦክስጂን አቅርቦት እና  ባልተጠበቀ የባህር ውስጥ እንስሳ መስተጓጐል እንዳይደርስ በመጠበቅ የተደረገለት እገዛ ከፍተኛ መሆኑን አስምሮበታል፡፡

ሞዴሊስቷ ሲያራ አንቶስኪ በተለያዩ ዳራዎች፣ በማራኪ አለባበስ እና የአካል እንቅስቃሴ የተዋጣለት ቀረፃ ማካሄድ እንዲችል ከልምምድ እስከ መጨረሻው እለት በብቃት መውጣቷ ለክብረ ወሰን እንዳበቃውም በማጠቃለያነት አስፍሯል – ስቴቨን ሀኒንግ፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here