በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረ-ምሕረት ቅድስት ኪዳነ-ምሕረት ቤተ-ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል መምህር በትረ ወንጌል ካሳ ስቅለትን እና ትንሳኤን አስመልክተው የሰጡንን መረጃ በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል።
መልካም ንባብ!
ስቅለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሀይማኖታዊ አስተምሮዉን ወይም ትርጓሜዉን ቢያብራሩልን?
ስቅለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ዘንድ ታላቅ ቦታ አለው:: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በአዳም ሞት ምክንያት በዕለተ ዓርብ በቀራኒዮ አደባባይ የተሰቀለበት ዕለት ነው” ዕለተ ዓርብ የስቅለት ቀን::
ዕለተ ዓርብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የተለየች ቀን ተብላለች:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ታምናለች፣ ታመልካለች፤ ስለተሰቀለላት መታሰቢያ ሁሌም በህይወት ዘመን ሁሉ ምዕመኖቿ ሲያስቡ እና ሲመለከቱ እንዲኖሩ ታደርጋለች::
ለዓለም ሁሉ ድኅነት ያደረገለትን ፣የተከፈለለትን የደም ዋጋ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የዋለው ውለታ እና የከፈለው ዋጋ አድኅኖት በማስታወስ ቤተ-ክርስቲያን ዘወትር ይህንን ስትማር፣ ስታስተምር እና ስታምን ትኖራለች::
ስቅለት የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ የሰው ልጅ ከዲያብሎስ አገዛዝ ነጻ የወጣበት ነው:: ለዚህም “የድኅነት ቀን” ወይም መልካም ዓርብ ይባላል:: የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ሐጢያትን ያጠፋበት፣ ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተዋጅታ ነጻ የወጣችበት፣ የሰው ልጆችም የደም ዋጋ ተከፍሎላቸው ነጻነት ያገኙበት ነው::
በተለይ በሮማዊያን እና በፈሪሳዊያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበር:: በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይረው ነገርን የሚገለብጠው አምላክ በወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት ፣የህይወት ግርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ እንዲሁም የገዳማት ዘውድ ስላደረገው እና ዕለተ ዓርብ በሞቱ ህይወትን ስላገኘን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰበት መከራ የሚታሰብበት ዕለት ነው:: በሰሙነ ህማማት ዕለተ አርብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ልዩ ቀን ነው:: የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣የወደቁትን ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት ፣ህመምተኞችን የሚፈውስ ሲሰቃይ የዋለበት፣ አሳሪው ዲያቢሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው:: ዕለተ ዓርብ የስቅለት ዓርብ ይባላል:: ይህም የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም እና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት ነው:: በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ቁጥር 35 እንደተገለጸው::
“ኢየሱስ የጸሎተ ሐሙስ ማታ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻውን ራት መግቦ ካስተማረ እና ምሥጢረ ቁርባንን ከመሠረተ በኋላ ሌሊቱን በአይሁድ ጭፍሮች እና በሊቃነ ካህናት ሎሌዎች ተይዞ ስቃይ እና እንግልት ደርሶበታል:: በስቅለት ዕለት ልዩ ልዩ ስርዓቶች ሲከናወኑ ይውላሉ:: ክርስቶስ ከተያዘበት አንስቶ እስከ ተሰቀለበት ሰዓት ቤተ-ክርስቲያን ሙሉ ሰዓቷን በጸሎት ታሳልፋለች:: መከራውን፣ መገረፉን፣ መደብደቡን፣ ለሰው ልጅ ብሎ መሰቀሉን ፣ሞቱን እና ወደ መቃብር መውረዱን የሚነገሩበት ስርዓቶች ይካሄዳሉ::
በዕለተ ዓርብ (የስቅለት ዕለት) የኢየሱስ ክርስቶስ ውሎ እንዴት ይገለጻል?
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት እስከ ስድስት ሰዓት በመጀመሪያ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ፣ ቀጥሎም ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ ደግሞ ወደ ሔሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ እያመላለሱ እንዲንገላታ እና እንዲሰቃይ አድርገውታል፤ ፌዝ፣ ዛቻ እና ድብደባም አድርሰውበታል:: ስድስት ሰዓት ላይ ደግሞ በሁለቱ ወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ:: ፌያታዊ ዘየማን (ጥጦስ) በቀኝ በኩል እንዲሁም ፌያታዊ ዘፀጋ (ዳክሮስ) በግራ እንደነበሩ ይታወቃል:: ክርስቶስ ሳይበድል ከበደለኞች ጋር ተሰቀለ:: ዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱ ከቅድስት ሥጋው የተለየችበት የሥጋ የአገልግሎት ዘመኑ የተፈፀመበት ሰዓት ነው::
በዕለተ ዓርብም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ እስከለየባት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ብዙ መከራዎች ተቀብሏል፤ በጅራፍ ተገርፏል፤ መስቀሉን ተሸክሞ እንዲወድቅ እንዲነሳ ተደርጓል፤ ምራቃቸውንም እየተፉበት ወደ ቀራንዮ ተራራ ወጥቷል፤ እጆቹን እና እግሮቹን በችንካሮች መትተው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፤ በጦር ወግተውታል፤ የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ በማጥለቅም ተሳልቀውበታል:: እሱ ግን በመስቀል ላይ ሳለ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ ተናገረ:: በመጨረሻም “እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ” በማለት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በራሱ ፈቃድ ለይቶ ለሰው ልጆች ሕይወት ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ:: አስራ አንድ ሰዓት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው::
በዕለቱ የታዩ ታምራት ምንድን ናቸዉ?
ፀሐይ ጨለመች፤ ጨረቃ ደም ሆነች፤ ከዋክብት ረገፉ:: በምድርም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ (የጥል ግድግዳ አበቃ)፤ ምድር ተናወጠች፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ ብዙ ዘመን ያሳለፉ ሙታንም ተነሱ:: በሰማያትም በሲኦልም ሲሰቃዩ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነት ተሰበከ:: መቃብር ስልጣኑን ለቅቋል፣ ሞትም ኀይሉን ተነጥቋል:: የሰው ልጆችም ከባርነት ወጥተው በነጻነት ኖረዋል::
ስቅለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በምን ታስቦ ይውላል?
ዓርብ ዕለት ጌታ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ ፈጸመ:: ምዕመኑም “አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበን” እያሉ ዕለቱን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ እያሰቡ፣ ስለ ኃጢያታቸው እያዘኑ፣ ስለ ማዳኑም እያመሰገኑ በስግደት ያሳልፋሉ:: የጾማቸውን ፍጻሜ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ማኅተም ይዘጋሉ::
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ስቅለት ሲታሰብ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የከፈለው መስዋዕት እንዴት እንደወደደን ያሳየበት፣ የሰውን ልጅ ሞት የተቀበለበት፣ የተቸነከረበት፣ እሱ የሞተበት ለሰው ልጅ ፍቅር ስላለው ነው:: ለዚህም ነው በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ መስቀል ትልቅ ቦታ አለው የሚባለው፤ ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የኛ ድኅነት መንስኤ እና የሐጢያት ስርኤት ያገኘንበት ነው፤ለዚህም ሲባል ንጹህ ደም ፈሷል፣ ክቡር ሥጋ ተቆርሷልና ክርስቲያኖች ባንገታቸው የመስቀል ማተብ ያደርጋሉ::
ሐጢያት የሌለበት ጌታ ስለ ሁሉ ሐጢያት ሲል ተላልፎ የሞተባት ዕለት ለሰው ልጅ የሚሰጠው መንፈሳዊ አስተምህሮት ከፍ ያለ ነው:: ደብድበው የሰቀሉት በፍርድ አደባባይ መቆም የማይችሉ ሐጢያተኞች ቢሆኑም፤ ክርስቶስ ግን ገርፈው የሰቀሉትን ይቅር ብሏል፤ ያልበደሉትን ብቻ ሳይሆን በደለኞችን መታገስ እንደሚገባ አስተምሯል:: የሰው ልጅ የራሱ በደል ይኖርበታል እና መታገስን፣ ጠላትን እስከመውደድ ድረስ ፍቅርን መለማመድ እንዳለብን ያስተማረን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::
ማህተመ ጋንዲ ዓለም ልዩ ልዩ ሕግ እያወጣች እና እያረቀቀች በየጊዜው ትውልዱ ሲነቃ ደግሞ የሚቀጥለውን ትውልድ የሚመራ እየተባለ ሕግ ይሻሻል ነበር:: ከዚህ ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ወንጌል ብናስተምረው ለዓለም በቂ ይሆናል:: ምክንያቱም ከሱ በላይ በቂ ሕግ ማንም ሊሠራም አይችልም ብለዋል:: ዘመናችን ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የምንሰብክበት፣ አንዱ ባንዱ ላይ የሞት አዋጅ የሚያውጅበት እና የጦር ነጋሪት የሚጎስምበት ሆኗልና ማንም ቢሆን መማር ያለበት ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን ፣ታማኝነትን፣ ቃል ጠባቂነትን፣ ደግነትን ፣ሩህሩህነትን፣ አዛኝነትን፣ ታጋሽነትን ፣ግልጸኝነትን ፣ራስን ዝቅ ማድረግን፣ ቂም አለመያዝን፣ ጠላትን መውደድን አስተምሯል::
የኢየሱስ ክርስቶስ የድኅነት ሰነድ ወንጌል የዓለምን ሕግ ሁሉ ቅርጽ ማስያዝ የሚችል ኃይል ያለው ነው:: ጦር ሰብቆ፣ ዘገር ነቅንቆ ቢመጣብህ በፍቅር አብርደው:: ፍቅር ኃያል እና ጉልበታም ነው:: ዓለም የትውልድን ህይወት ከሚቀጥፍ ኒዩክሌር ከማብላላት ይልቅ የክርስቶስን ፍቅር ቢሰብክ ሰላም በሰፈነ ነበር:: ለኒዩክሌር ማብላያ እና የጦር መሣሪያ መግዣ የሚያውሉትን ገንዘብ ለዳቦ መግዣ ቢያውሉት ትውልድ ይድን ነበር ::
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለበደለኞች ድኅነት የመሰቀሉ ምክንያት የሰው ልጆች በይቅርታ ማለፍን፣ ከመግደል ይልቅ አንዱ ስለ አንዱ ተላልፎ መሞትን፣ እየሞቱም ቢሆን ማስተማር እደሚገባ ለማሳየት ነው:: ሁሉን ማድረግ እየተቻለው ማስተማርን መርጧልና፤ የሰው ልጅ ማድረግ ስለቻለ ብቻ ጥፋትን ሁሉ ማድረግ እንደሌለበት ሊማር ይገባል::
ትንሳኤ ምን ማለት ነዉ?
“ኢየሱስ ክርስቶስ ያን ሁሉ መከራ አሳልፎ የሞትን ችንካር ሰብሮ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተበት ዕለት ፣ ዳቢሎስን ድል የነሳበት፣ ህያውነቱን ያስመሰከረበት ፣ መቃብር መስበር የሚያስችል ሥራ የተሠራበት ዕለት ነው :: ትንሳኤ የመከራው ግልባጭ የድል አክሊል የተቀናጀበት ነው:: በዕለተ ዓርብ የፈሰሰ ደም እና የተቆረሰ ሥጋ እሁድ ዕለት ትንሳኤዉ ታይቷል::
ዳግማዊ ትንሳኤስ?
ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ (በትንሳኤ ሳምንት ) እንደተነሳ የታያቸው የሰው ልጆች ዳግም ወደ ህይወት መመለሳቸውን እና መነሳታቸውን የሚያሳይ ነው::ከሥጋዊ ሞት በኋላ የሰው ልጅ በዳግመ ትንሳኤ መኖር የመቻሉ እውነታ ነው -ዳግመ ትንሰኤ::
ከኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንማር?
ከኢየሱስ ክርስቶስ ልንማር የሚገባው ፍቅርን ፣ትውልድ ማሻገርን፣ለወገን ማሰብን እና በጎ ማድረግን ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ ሐጢያት ሳይኖርበት ለሰው ልጆች ጥፋት እና ሐጢያት ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ እኛ የሰው ልጆች ግን የኢየሱስን አርዓያነት በከፊል እንኳን መከተል ተስኖን ከደግነት ይልቅ ክፋትን እንፈጽማለን፤ ከክርስቶስ ብዙ ነገሮችን ነው መማር ያለብን::
ከምዕመኑስ ምን ይጠበቃል?
የሰውን ልጅ እንደ ድልድይ ሆኖ ማሻገር ሲገባን የሰውን ልጅ እንደ ድልድይ ተጠቅመን ለመሻገር የምናደርገውን ድርጊት ክርስቶስ አይወደውም:: ምዕመኑ መተዛዘንን፣ መረዳዳትን፣ አንዱ ለአንዱ መድረስን፣ ለተሰደዱ እና ለተፈናቀሉ በአጠቃላይ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቸ የተለመደ ደግነቱን ማድረግ ይኖርበታል።
በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለበዓለ ስቅለቱ እና ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን ማለት እፈልጋለሁ:: በዓላቱን ስናከብር ለኛ ለሰው ልጆች ሲል ያለ ሐጢያቱ የሞተልንን ክርስቶስን እያሰብን መሆን አለበት። የሱን መልካምነት እና ሞቶ በትንሳኤው የመነሳቱን ምስጢር በልባችን ውስጥ በማኖር እኛም ለአምሳያዎቻችን ፍጹም ደጎች መሆን ይጠበቅብናል። ይቅር ማለትንም ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ይኖርብናል:: በበዓላቱ ለተጎዱ እና ርዳታችንን ለሚፈልጉ ሰዎች ያለንን በማካፈል ደግነታችንን ማሳየት ይኖርብናል::
ለሰጡን መረጃዎች ከልብ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም