ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል ከመማር ማስተማር ሥራው ባለፈ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ይገለጻል። ተማሪዎች፣ ወላጆች እና መምህራን የሚኖራቸው መስተጋብርም ለተማሪዎች የነገ ሕይወት መሠት ነው፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤተሰብ አስፈላጊውን የትምሕርት ቁስ ለማሟላት አቅቶት ከትምሕርት ገበታ ውጪ የሚሆኑ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም::
በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ሰዎች ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ ፈተና ሆኗል፤ በርካታ ትምሕርት ቤቶችም እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል:: ከዚህ በተጨማሪም ወላጆች ለልጆቻቸው አስፈላጊውን የትምሕርት ግብዓት ለማሟላት ባመቻላቸው ከትምሕርት ገበታ ውጪ ለመሆን ይገደዳሉ::
በሌላ በኩል መሰል ችግሮች ሲከሰቱ የቆየው የመረዳዳት ባሕል የበርካታ ታዳጊዎችን ትምሕርት አስቀጥሏል፤ በሰሜን ጎንደር ዞን መዲና ደባርቅ ከተማ ያስተዋልነውም ይህንኑ ዕሴታችንን የሚያረጋግጥ ነው::
መምህርት ባዩሽ አሰፋ ይባላሉ፤ በደባርቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ናቸው፤ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ እርፍ ጨብጠው፣ በሬ ጠምደው ያመርታሉ:: የተቸገረ አይተው ማለፍ እንደማይችሉም በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ::
አሚኮ በደባርቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ ያነጋገራቸው በጎ አድራጊ መምህርት ባዩሽ አሰፋ ለመማር ፍላጎት እያላቸው የኢኮኖሚ አቅም ያነሳቸውን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማስቀጠል ገቢ በማሰባሰብ እና ካላቸው ገቢም በመቀነስ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
መምህርት ባዩሽ እንዳሉት በአካባቢያቸው እና በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸዎን ሲያቋርጡ በተደጋጋሚ ታዝበዋል፤ ይህም የበጎ ተግባሩን እንዲጀምሩ አነሳሳቸው። ተማሪዎች የመማር ፍላጎት እና ተነሳሽነት እያላቸው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ካሰቡበት ለመድረስ፣ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ሲቸገሩ ማየታቸው ልብን የሚሰብር ሐዘን እንዳጫረባቸው ነው የነገሩን።
ድጋፉን የጀመሩት በቤት ውስጥ መሆኑንም ይናገራሉ። የቤት ውስጥ የሥራ ረዳታቸው የመማር ፍላጎት እያላት ነገር ግን ኑሮን ለማሸነፍ ወደ ከተማ በመምጣት በቤት ውስጥ ሠራተኝነት እየሠራች ትምህርት ማቋረጧን እንደነገረቻት ያስታውሳሉ፤ ይህን ሲሰሙ ይበልጥ አዘኑ:: ነገሩንም በማዘን ብቻ ሳይተውት ከልጆቻቸው ጋር እኩል በማስተማር ለቁም ነገር ማብቃታቸውን መምህርት ባዩሽ ገልጸዋል።
መምህርት ባዩሽ በሚያስተምሩበት ት/ቤት የሥርዓተ ጾታ እና በጎ አድራት ክበብ አስተባባሪ ናቸው፤ በክበቡም የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በመደገፍ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዘለቀ ክትትል እና ድጋፍ አድርጋዋል፤ እያደረጉም ይገኛል።
መምህርቷ ተማሪዎቹን ለመደገፍ የሚያስችላቸውን ገቢ ለማግኘት ከትምህርት ቤቱ የተወሰነ ቦታ በመቀበል የግብርና ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ነግረውናል።
የመምህርቷ አገልግሎት በመማሪያ ክፍል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሞፈር እና ቀንበር አዋድደው፣ ማረሻም ጨብጠው ያመርታሉ:: በዚህም ገቢ ለሌላቸው ተማሪዎች በማገዝ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ።
የኢኮኖሚ አቅም ያነሳቸውን ተማሪዎች ለመደገፍ ሲሉ ያርሳሉ፣ ይዘራሉ፣ ያርማሉ፣ ወቅቱን ጠብቀው ያጭዳሉ፤ ይህ ተግባር ደግሞ የግል ኑሯቸውን ለማሻሻል ሳይሆን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎቻቸውን ለመደገፍ ነው።
መምህርነትን ከቀለም እናትነት በዘለለ የዓመት ልብስ እና የዕለት ጉርስ በማቅረብ ለተማሪዎች ያልተገደበ ድጋፍ በማድረግ ባለውለታ መሆናቸውን ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች ይመሰክራሉ።
መምህሮቷ ገቢ አሰባስበው የሚያደርጉላቸው ድጋፍ ባይኖር መማር ምኞት ብቻ ይሆንባቸው እንደነበርም ነው የነገሩን። ተማሪ አሚኑ ሰዒድ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ ነው፤ በመምህርት ባዩሽ አስተባባሪነት የተደረገለት ድጋፍ የሱን እና የጓደኞቹን የመማር ማስተማር ተግባር እንዳቀለለላቸው ነው የተናረው።
ትምህርት የአዕምሮ ሥራ በመሆኑ የተሻለ የስነ – ልቦና ዝግጅትን እና በቂ የቁሳቁስ አቅርቦትን ይፈልጋል። ተማሪ አሚኑም በተሻለ የስነ ልቦና ዝግጅት ትምህርቱን እየተከታተለ ነው፤ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው በርካታ ተማሪዎች እንዳሉ በማንሳትም ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ሁሉም የሚችለውን እንዲያግዝ ጠይቋል።
መምህርት ባዩሽ የተማሪዎቹ የግል ችግር እንደሚያስጨንቃቸው እና ችግራቸው ተፈትቶ በተመቻቸ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርጉት ብርቱ ጥረት ለተማሪዎች የነገ የበጎ አድራጎት ሕይዎት አርያ የሚሆን እንደሆነም አክሏል።
ሌላኛዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ተማሪ ታድሳ ፈቃዴ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ስለሚያደርጉት ድጋፍ አመስግናለች፤ ድጋ ባይደረግላቸው እርሷን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ይችሉ እንደነበር ነው ያነሳችው፤ የመምህርት ባዩሽን አርዓያነት ሌሎችም በመውሰድ በችግር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ማገዝ እንደሚገባ ተናግራለች።
ከኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በተጨማሪ ሴት ተማሪዎች ሊደርስባቸው የሚችሉ ጫናዎችን በመረዳት ልዩ ልዩ ምክረ ሃሳቦችን በመለገስም ጭምር መምህርቷ ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች።
የት/ቤቱን የሥርዓተ ጾታ እና በጎ አድራጎት ክበብ እና የመምህርቷን በጎ አድራጎት ተግባር ለበርካታ ችግረኛ ተማሪዎች በጎ ያደረገ ሲሉ የገለጹት ደግሞ የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማሕበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ የሺወርቅ ሞላ ናቸው፤ ኃላፊዋ እንዳሉት መምህርቷ እያደረጉት ያሉት አስተዋጾ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን ነው። መምህርቷ የሚያደርጓቸውን ተግባራት በመደገፍ እና በማበረታታት አብረው ሲሠሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
መምህርቷ ከማስተማር ሥራቸው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያደርጉትን መልካም ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነግረውናል። የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማሕበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤትም አብሮ እንደሚሠራ እና የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ኃላፊዋ ወ/ሮ የሺወርቅ ሞላ ተናግረዋል::
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


