ጤናማ አመጋገብ ለሕጻናት

0
133

ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ 39 በመቶ ያህል ሕፃናት የመቀንጨር ወይም  የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው፤ አማራ ክልልም ችግሩ አሳሳቢ ከሆነባቸው አካባቢዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው፡፡

ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ33 በመቶ በላይ የምርት ድርሻ እንዳለው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፤ ይሁን እንጂ የመቀንጨር ችግር በከፍተኛ ደረጃ ከሚታይባቸው አንዱ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

ችግሩ ደግሞ በዋናነት በግንዛቤ እጥረት የሚከሰት መሆኑን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ከዚህ ችግር ጋር በተገናኘ በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኘው የደብረ ታቦር ጤና ጣቢያ እያከናወነ ያለው ተግባር በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን በተቋሙ ተገኝተን ታዝበናል። በጤና ጣቢያው እንደተመለከትነው ተቋሙ ለወላጆች የተመጣጠነ የሕጻናት አመጋገብ ግንዛቤን ይፈጥራል፤ ከዚህ በተጨማሪም በየሦስት ወሩ የተመጣጠነ ምግብን ለሕጻናት ይመግባል። ይህን ማድረጉ ደግሞ ወላጆች የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀትን በተግባር እንዲመለከቱና እንዲተገብሩት ያስችላል።

ወ/ሮ ፋሲካ ደገፋው ግንዛቤውን በማግኘት በተግባር እየተረጎሙ ከሚገኙ ወላጆች መካከል አንዷ ናቸው፤ የአንድ ልጅ እናት ሲሆኑ በጤና ጣቢያው የተመጣጠነ የሕጻናት ምግብ ዝግጅት እና ምገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት አግኝተናቸው ሐሳባቸውን አካፍለውናል። “ከስድስት ወር በኋላ የእናት ጡት ብቻ በቂ አለመሆኑን ከዚህ ቀደም ግንዛቤ ተፈጥሮልኛል” ሲሉ ነው ሐሳባቸው የጀመሩልን፤ ወ/ሮዋ ልጃቸውን አቅማቸው በፈቀደ መጠን፣ ቤት ያፈራውን የተመጣጠነ ምግብ በማዘጋጀት እንደሚመግቡም ነው ያጫወቱን።

ወይዘሮዋ እንደነገሩን ከእናት ጡት በተጨማሪ ከምጥን ዱቄት የተዘጋጀ ገንፎ ልጃቸውን ይመግባሉ። ይህም ከጥራጥሬ እና ከእህል (አንድ እጅ ጥራጥሬ ሦስት እጅ ደግሞ ከእህል አይነት) የሚዘጋጅ ነው። ገብስ፣ ጤፍ፣ አጃ፣ ክክና የመሳሰሉት ደግሞ ምጥን የገንፎ ዱቄት የሚያዘጋጁባቸው የእህል አይነቶች ናቸው። ይህን ሁሉ አመጣጥኖ፣ በአግባቡ አዘጋጅቶ ልጅን መመገብ “ለልጆች ጤና እንዲሁም ለተስተካከለ ዕድገት በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉም ነው ተሞክሯቸውን ያካፈሉን።

“የሁለት ልጆች እናት ነኝ፤ የመጀመሪያው ልጄ አመጋገብ ብዙ አስተምሮኛል” ያሉን ደግሞ መቅደስ ለገሰ የተባሉ ሌላዋ ወላጅ ናቸው። ወ/ሮ መቅደስ እንደነገሩን ሕጻናት ስድስት ወር ከሆናቸው በኋላ የእናት ጡት ብቻ በቂ አይሆንም፤ በመሆኑም ቀስ በቀስ በአትክልት የበለፀገ ሾርባ እና ከተመጠነ ዱቄት የተዘጋጀ ገንፎ መመገብ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ሕጻናት ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ነው ተሞክሯቸውን ያካፈሉን።

የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ መቅደስ ከስድስት ወር በኋላ ከእህል እና ጥራጥሬ ተመጥኖ የተዘጋጀ ገንፎ በመመገብ ልጃቸውን እንደሚንከባከቡ ይናገራሉ። ይህን በማድረጋቸውም “ልጄ ጤናው የተጠበቀ ብቻ ሳይሆን ዕድገቱም የተስተካከለ ነው” ብለዋል፤ በዚህ መንገድ ያደጉ ልጆች በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ስለመሆኑም ነግረውናል። በመሆኑም ቤት ያፈራውን አመጣጥኖ በማዘጋጀት መመገብ እንደሚገባ ያገኙትን ተሞክሮ አካፍለውናል።

በጤና ጣቢያው ተገኝተን እንደታዘብነው ስለ ሕጻናት ዕድገት ለወላጆች ትምህርት ይሰጣል፤ ስለ ተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት እና አመጋገብም ግንዛቤ ይፈጠራል። የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀትን በተግባር እንዲመለከቱም ይደረጋል፤ ከዚህ ባለፈም የተዘጋጀውን የተመጣጠነ ምግብ በየሦስት ወሩ ለሕጻናት ምገባ ይካሄዳል።

ያነጋገርናቸው እናቶች ጤና ጣቢያው ለሚያደርግላቸው ግንዛቤ እና መሰል ደጋፍ አመስግነዋል፤ ከእርግዝና ክትትል ባለፈ ከወለዱ በኋላ ስለ ልጃቸው ዕድገት በየጊዜው ግንዛቤ እንደሚያስጨብጧቸው ተናግረዋል፤ የተመጣጠነ የሕጻናት ምግብ አዘገጃጀትን በተግባር በማየታቸውም ቤት ያፈራውን  መጥኖ ለማዘጋጀት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡት ከጽንሰት ጀምሮ ያሉት  አንድ ሺህ ቀናት ለሕጻናት በእጅጉ ወሳኝ ጊዜያት ናቸው። በደብረ ታቦር ከተማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የሕፃናት አመጋገብ ክፍል ባለሙያ ሲስተር ያልጋነሽ ያረጋገጡልንም ይህንን ሐሳብ ነው። “ሕፃናት ትክክለኛ ዕድገት አላቸው የሚባለው የአንድ  ሺህ ቀናት ጉዞ ማለትም ከጽንሰት ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ያለው ጊዜ ነው” ሲሉም ነው ሙያዊ ማብራሪያን የሰጡን።

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ እስከ ስድስት ወር ጡትን በሚገባ ማጥባት፣ ከዚያም የተለያዩ የእህል አይነቶችንና ጥራጥሬዎችን በመቀላቀል ምጥን በማዘጋጀት መመገብ (ገንፎ) የተሟላ ጤንነትን እንዲሁም አካላዊ እና አዕምሯዊ ዕድገትን ይሰጣል።

የሕጻናትን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማስተማር ጤና ጣቢያው በየሦስት ወሩ ሠርቶ ማሳያ የምግብ አዘገጃጀትና የአመጋገብ ፕሮግራም ያዘጋጃል፤ በዚህም ለእናቶች ጥሪ በማድረግ በተግባር ልምድ ይወስዳሉ። ተሞክሮውን በመውሰድም እናቶች ቤት ያፈራውን አዘጋጅተው ልጆችን የመመገብ ልምዳቸው እየዳበረ መሆኑን ነው ባለሙያዋ የተናገሩት።

ባለሙያዋ አክለውም ጤናማ አመጋገብ የመቀንጨር፣ የመቀጨጭ እና በሽታን ያለመቋቋም ችግርን ያስቀራል። ይህም የተሟላ ጤንነትን ይሰጣል። “ይህ ሲባል ደግሞ ክትባትን በወቅቱ ተከታትሎ ማስከተብ እንደሚገባም ሳይዘነጋ ነው” ብለዋል።

(ዓለምነሽ ንጉሴ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here