ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢዎቻችን! በዚህ ዕትም ጤናማ እርግዝናን በተመለከተ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማሕጸን እና ጽንስ ትምህርት ክፍል ባልደረባ እንዲሁም የልዩ አማራጭ ሕክምና ዳይሬክተር ዶ/ር መሠረት ከፋለ ማብራሪያ ሰጥተውናል:: ዶ/ር መሠረት እንደሚሉት አንዲት እናት ጤናማ እርግዝና አላት የሚባለው ቀኑ ደርሶ በመውለጃ ጊዜው ልጁ ሲወለድ፣ የተወሳሰበ የእርግዝና ሁኔታ የሌላት ማለትም ደም መፍሰስ፣ የዐይን ብዥታ እና የራስምታታ ሳይኖራት ሲቀር ነው:: እንደ ዶ/ር መሠረት ማብራሪያ የጤናማ እርግዝና ምልክቶች እነዚህ ብቻ አደሉም እናት ለተለያዩ በሽዎች ያልተጋለጠች ሲሆን፣ መደበኛ ቀላል የሰውነት እንቅስቃሴ ስታደርግ (የእግር ጉዞ ወይም ዋና የምትዋኝ)፣ አደገኛ እጽ የማትወስድ (ለምሳሌ ሲጋራ የማታጨስ፣ መጠጥ የማትጠጣ) ከሆነች፣ እስክትወልድ ድረስ ከደም ግፊት፣ ከኩላሊት እና ከስኳር በሽታዎች ነጻ ከሆነች፣ መደበኛ የቅድመ ወሊድ ክትትል የምታደርግ እና አደገኛ የእርግዝና ምልክቶችን የምታውቅ ቢፈጠርም እርዳታ የምትሻ ከሆነች ነው::
ባለሙያው እንደገለጹት አንድ ጨቅላ ሕጻን ቀኑን ጠብቆ ተወለደ ሲባል ከ37 ሳምንት እስከ 41 ሳምንት ባለው የእርግዝና ጊዜ ሲወለድ ነው:: ነገር ግን የተሻለ የሚባለው ከ39 ሳምንት እስከ 40 ሳምንት ከስድስት ቀን ያለው ጊዜ ነው:: ከ37 ሳምንት በፊት ሲወለድ ግን የሕጻኑ ሳምባ ስለማይጠነክር የአተነፋፈስ ችግር ይገጥመዋል:: የስኳር እጥረት እና የሙቀት አለመቋቋም እንዲሁም ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ አጋጣሚው ሰፊ ይሆናል:: ከ37 እስከ 38 ከስድስት ቀን ባለው ጊዜም የተወሰነ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ:: ይሁንና ሳይንሱ ስለሚፈቅድ ከ37 ሳምንት ጀምሮ መውለድ ይቻላል:: ብዙ ጊዜ ነፍሰ ጡሮች የእንሽርት ውኃ ከፈሰሰ እና የደም ግፊት ችግር ካለባቸው ከ37 ሳምንት በፊት እንዲወልዱ ይመከራል::
ጽንሱ ከ41 ሳምንት ከስድስት ቀን በላይ ሲቆይ ደግሞ የመውለጃ ጊዜው አለፈ ይባላል:: የሚወለድበት ጊዜ ሲያልፍም የእርግዝና ችግሮች እንደሚከሰቱ ነው ባለሙያው የገለጹት:: ችግሮቹም እናት ላይ ወይም ልጅ ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ:: የእንሽርት ውኃ ሊወፍር ወይም ሊያንስ ይችላል:: የእንግዴ ልጅ እያረጄ ይሄዳል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ከእናት ወደ ልጅ የሚደርሰው የደም መጠን እየቀነሰ ስለሚሄድ በምጥ ጊዜ የሕጻኑ የልብ ምት ከፍ ወይም ዝቅ (ላይ ታች) ሊል ይችላል:: በዚህ ጊዜም ሕጻኑ እክል ሊያጋጥመው ይችላል::
ጽንሱ 34ሳምንት ከስድስት ቀን ሲሞላው ባደጉት ሀገራት የሕጻናት ማሞቂያ ስላላቸው እርግዝና ላይ ችግር ሲከሰት እንድትወለድ ያደርጋሉ:: እናት እና ልጅ ጤናማ እስከሆኑ ድረስ ግን እስከ 37 ሳምንት እንዲጠብቁ ይመከራል::
ዶ/ር መሰረት እንደሚሉት ቅድመ ወሊድ ክትትል ለእናትም ለልጅም በጣም ጠቃሚ ነው፤ ጤናማ እርግዝና እንዲኖር ከሚያደርጉ መሠረታዊ ነገሮች መካከልም አንዱ ነው:: ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጡ አደገኛ ምልክቶችን ለማወቅ ማስቻሉ ነው:: ለአብነትም ደም እና ውኃ መሳይ መፍሰስ፣ የልጁ እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ብዥታ እና ከባድ የራስ ምታት ናቸው:: ነፍሰጡሯ እነዚህን ምልክቶች ቀድማ ካወቀች ወደ ሕክምና መምጣት እንዳለባት እሷም ቤተሰቧም ማወቅ አለባቸዉ ::
በእርግዝና ውስጥ የሕጻናት ክብደትን በተመለከተ መቀንጨር፣በቂ እና ከበቂ በላይ ውፍረት ሊከሰት ይችላል:: ታዲያ በዚህ ጊዜ ትክክለኛ ክብደት እንዲኖረው ለማድረግ በቅድመ ወሊድ ክትትል ሊታወቅ ይገባል:: የእናቲቱ አወላለድ በምጥ ነው? ወይስ በቀዶ ሕክምና? የሚለው የሚለየው እናት በቅድመ ወሊድ በምታደርገው ክትትል ነው::
በቅድመ ወሊድ ጊዜ በሚደረግ የአልትራሳውንድ ምርመራ የጽንሱ ክብደት ይታወቃል፣ የእንግዴ ልጅ አቀማመጥን፣ የእንሽርት ውኃ መጠንን እና የልጁ አፈጣጠርም ይታወቃል:: እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ጭንቅላቱ ትልቅ ከሆነ ውኃ ቋጥሮ ሊሆን ይችላል:: በአጠቃላይ ጽንሱ ጤነኛ ነው የሚለው የሚታወቅበት በመሆኑ ቅድመ ወሊድ ክትትል አስፈላጊ ነው::
ባለሙያው አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት ማሕበረሰቡ ማወቅ ያለበት ነገር የጽንሱን አፈጣጠር በደንብ ለማወቅ ነፍሰጡሯ ቢያንስ ስምንት ጊዜ የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ (መታየት) ይኖርባታል:: አካላዊ አፈጣጣር ላይ ችግር አለው? ወይስ የለውም? የሚለው የሚታወቀው ደግሞ በሦስት እና በአምስት ወር ላይ በሚደረግ ደረጃውን የጠበቀ አልትራሳውንድ ምርመራ ነው:: አንዲት ነፍሰጡር በነዚህ የእርግዝና ወራቶቿ በአልትራሳውንድ መታየቷ ግዴታ ነው::
የአፈጣጠር ችግር ካለበት በመጀመሪያ ባለሙያው ከሥራ አጋሮቹ ጋር ቁጭ ብሎ በመመካከር ምናልባት እርግዝናው ቢቀጥል እና ያለበት የአፈጣጠር ችግር በሕይዎት ያኖረዋል ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ ይወያያል:: በሌላ በኩል እርግዝናው ቢቀጥል ጽንሱ በመሃል ሕይወቱ ካለፈ፣ ከተወለደ በኋላም በሕይወት የመቆየቱ ጉዳይ ያን ያህል ካልሆነ ደግሞ ከወላጆች ጋር በመወያየት ጽንሱ እንዲወርድ ይደረጋል:: ታዲያ ይህ የሚሆነው እስከ አምስት ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ ነው:: አምስት ወር ላይ ሙሉ በሙሉ ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎች የሚወጡበት ጊዜ ነው፤ሌላው በአምስት ወር ላይ በመድሃኒት ጽንስን ማስወረድ ስለሚቻል ነው:: ከአምስት ወር በኋላ ግን በጣም አስቸጋሪ ካልሆነ በስተቀር ጽንስን ለማስወጣት መሞከር እናቲቱ ላይ ለሕይዎት አስጊ የሆነ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል እንደማይመከር ነው ያስገነዘቡት::
ባለሙያው እንደሚሉት ከሰባት ወር በኋላ ችግሩ እንዳለ ቢታወቅ በጣም አስጊ ነው:: ሕክምናው ለእናቲቱም ለባለሙያውም አስቸጋሪ ያደርገዋል:: አልትራሳውንዱን ከተቻለ በማሕጸን እና ጽንስ ባለሙያ ብትታይ ተመራጭ እንደሚሆንም ይመክራሉ::
እንደ ዶ/ር መሠረት ገለጻ ሌላው የቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያስገኘው ጠቀሜታ የነበሩ ሕመሞች ካሉ እነሱን ተከታትሎ ለማከም ማስቻሉ ነው:: ለአብነትም አንዲት እናት ስታረግዝ የደም ግፊት፣ የስኳር እና የኩላሊት በሽታ እንዲሁም የደም መርጋት ሊኖርባት ይችላል:: ከማርገዟ በፊት እነዚህን ችግሮች ለመቆጣጠር ያስችላል::
ሌላው ለእናቲቱ ተመጣጣኝ ምግብ እንድትመገብ ምክር ይሰጣል:: ቫይታሚኖችን እና ሚኒራሎችን የያዙ ምግቦች ያስፈልጓታል:: አይረን ከምግብ በተጨማሪ መድሃኒት እንድትወስድ ያስችላታል:: ክትባቶችን እንድትወስድ ያስችላል:: ሌላው ኤች አይ ቪ በደሟ መኖር አለመኖሩ ምርመራ ታደርጋለች፤ ምክንያቱም ኤች አይ ቪ ካለባት ስትወልድ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ ነው:: በገንዘብ /ፋይናንስ/ በኩልም ቀድማ እንድትዘጋጅ ያደርጋታል:: ምናልባት ችግር ቢያጋጥማት የሚሰጣት ደም የትኛው እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችለውን የደም አይነቷን እንድታውቅ ያድርጋል:: የቤተሰብ ድጋፍ እንድታገኝም ያስችላል:: ከዚህ ባለፈ ሕክምና ተቋም ላይ እንድትወልድ ያስችላታል:: ቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረጓ የእናትን እና የሕጻናትን ሞትም ይቀንሳል::
በተያያዘም በእርግዝና ጊዜ ስለሚፈጠሩ ሕመሞች ማብራሪያ የሰጡት ባለሙያው አብዛኛውን ጊዜ በእርግዝና ወቅት የሚሰሙ ሕመሞች ተፈጥሯዊ እንደሆኑ እና ማከም ማስቀረትም እንደማይቻል ነው የጠቆሙት:: እንደባለሙያው ማብራሪያ አብዛኛዎቹ እናቶች የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት አካባቢ ጥሩ ስሜት አይሰማቸውም:: ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ይኖራቸዋል:: ምርመራ ተደርጎ በእርግዝናው ምክንያት የመጣ መሆኑ ከታወቀ መድኃኒቶች ይሰጣሉ:: ነገር ግን ተፈጥሯዊ ስለሆነ ማስቀረት አይቻልም:: በሕጻኑም ሆነ በእናቲቱ ላይ ጉዳት አያደርስም:: ነገር ግን አንዳንድ እናቶች ላይ ማስታወኩ እና ማቅለሽለሹ እስከ ዘጠኝ ወራት ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል አስገንዝበዋል::
ተጓዳኝ ችግሮች ካሉ፣ በፊት ያልነበሩ እና ስታረግዝ የተከሰቱ ካሉ፣ የስኳር በሽታ ሲኖር እናቲቱ ጥሩ ስሜት አይሰማትም:: ሌላው የደም ግፊት ካለ አብረው የሚመጡ ስሜቶች አሉ:: የዐይን ብዥታ እና ከፍተኛ የራስምታት ይኖራል:: የደም መፍሰስ ካለ ጥሩ ስሜት አይኖርም:: ከእርግዝና በፊት የነበሩ ነገር ግን በእርግዝናው የተባባሱ ካሉ በእርግዝና ወቅት ጥሩ ስሜት እንዳይኖራት ያደርጋል::
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ማስታወክን መቀነስ ወይም ማቆም የሚያስችሉ መድኃኒቶች አሉ:: የሚሰጡ መድኃኒቶችም ለጽንሱ በተቻለ መጠን ጉዳት እንደማያደርሱ በመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተረጋግጦ የሚሰጥ ነው:: በጥቅሉ በእርግዝና ወቅት መድኃኒት ባይሰጥ ይመከራል:: ካልሆነ ግን በእርግዝና ወቅት የሚሰጡ በሕጻኑም ሆነ በእናቲቱ ላይ ጉዳት የማያደርሱ መድኃኒቶች ይሰጣሉ:: መድኃኒት መውሰዱ ካለመውሰዱ የሚሻል ከሆነ ብትወስድ ጥሩ ይሆናል:: ከሀኪም ትዛዝ ውጪ መድኃኒት መግዛት እና መዉሰድ አይመከርም::
አንድ እናት ስታረግዝ የቤተሰብ ማለትም የባል፣ የእህት፣ የወንድም እና የእናት የአባት ከፍተኛ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋት ባለሙያዉ ጠቁመዉ ጤናማ እርግዝና እንዲኖር፣ ጤናማ ልጅ እንዲወለድ፣ የእናት እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ እንደባለሙያ የምመክረው ቀጣይነት ያለው ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ ወሊድ ክትትል ማስፈለጉን ነው:: ችግሮች ካሉ ቀድሞ በማወቅ መፍትሔ ለማግኘት ወሳኝ ነውና:: ማንኛዋም ነፍሰጡር ስትወልድ በጤና ተቋማት መሆን አለበት” በማለት ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም