ጤናማ እናትነት

0
141

እናትነት እንቁ የሆነ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ውድ የተፈጥሮ ሥጦታ በጤና እክል እና ድንገት በሚፈጠር አደጋ የሐዘን ምንጭ ሲሆን ይታያል፡፡ ጤናማ እናትነት እንዲከበር የተወሰነውም ሕይወት በመስጠት ሂደት ሕይወት እንዳይቀጠፍ በሚል  ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ እናቶች በተለይ በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ ተገቢውን የጤና እንክብካቤ ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች ለማድረግ ታስቦ  ነው፡፡

ጤናማ እናትነት በእርግዝና ብቻ ሳይሆን ከእርግዝናም በፊት፣ በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ወቅት እና በኋላ የተሟላ አገልግሎት እንድታገኝ ማስቻል ነው፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል  ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ የጤናማ እናትነት ወር ፕሮግራምን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  የጤናማ እናትነት ቀን በጥር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ20ኛ  እንዲሁም በክልላችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ ታዲያ ዘንድሮ “ፈጠራ እና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል በጥር ወር ሲከበር ወሩን ሙሉ  ስለጤናማ እናትነት ግንዛቤ በመፍጠር እና ሥራዎችን በመሥራት  ነው፡፡

ኃላፊው ሲያስረዱ በዚህ ወር የጤናው ባለድርሻ አካላት ስለጤናማ እናትነት ትኩረት እንዲሰጡበት ትብብርና ቅንጅትን ለማጠናከር ታሳቢ ተደርጎ የሚዘጋጅ ኹነት ይካሄድበታል፡፡  ይህ ኹነት ለአንድ ወር የሚቆይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ጥር ወር ተመራጭ የሚሆንበት  የክልሉ አብዛኛው ማሕበረሰብ የአርሶ አደር ማሕበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ከብዙ ልፋት በኋላ ሥራዎችን አጠናቆ በቤቱ የሚሆንበት፤ ሚዲያዎችን ክትትል የሚያደርግበት እና በቀላሉ የማሕበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክርበት ስለሆነ ነው፡፡

በዚህ ወር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ለመፍጠርም እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ትልቅ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡  ስለዚህ እናት የሀገር ተረካቢ እና ትውልድን አስቀጣይ በመሆኗ  ስለእናቶች ጤና ሰፋ ያሉ ግንዛቤዎችን መፍጠር እና የነገን  ትውልድ ማስቀጠል  ለነገ የሚተው ሥራ እንዳልሆነ ነው ያብራሩት፡፡  ጥርን ወር ጤናማ የእናትነት ወር በሚል ሲከበርም ከዚህ በፊት የተከናወኑ ሥራዎች ዓመቱን ሙሉ ተጠናክረው የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን በተከናወኑ  ሥራዎችም እናቶችን ከሞት ከመታደግ አኳያ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡ እናቶች ባሉበት አካባቢ ለእናቶች እና ለሕፃናት የሚሆኑ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

ትልቅ ለውጥ የመጣበትም በየአካባቢው ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ምናልባትም ሕመም ሲያጋጥም ሕክምና በመስጠት፣ ከነሱ አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ሪፈር በመላክ  የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ የተሄደበት መንገድ ጥሩ ነበር፡፡

ሁለተኛ አቅርቦትን ከማሻሻል አኳያ በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የግብአት አቅርቦትን በማሳለጥ እና የሰው ኃይልን በማሟላት በተለይ የሚድዋይፈሪዎች ቅጥር ተከናውነዋል፡፡

የተለያዩ አዳዲስ አሠራሮች በመነደፋቸው በጤና ጣቢያ ደረጃም የአልትራሰውንድ  አገልግሎት ማስጀመር ተችሏል፡፡ ይህም ችግርን በወቅቱ የመለየት እና በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት እድል ይሰጣል፡፡  ሁለተኛ ከወትሮ በተለየ በአዲስ የተጀመረው አንድ እናት ከእርግዝና  በፊት ዝግጅት ማድረግ አለባት፣ እርግዝና  መውለድ  እና ልጅ ማሳደግ በእቅድ መመራት አለበት የሚለው ነው፡፡

እናት ከማርገዟ በፊት ሰውነቷ፣ አዕምሮዋ እና ቤተሰቧ መዘጋጀት አለበት፡፡   የፋይናንስ እጥርት እንዳያጋጥማትም መዘጋጀት አለባት፡፡ ይህን ለማድረግም እንደተሞከረ ነው የገለጹት፡፡

እናቶች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ስለሚያስፈልጋቸው አገልግሎቱን በሆስፒታል ደረጃ ብቻ መሰጠት የለበትም በሚልም ክልሉ ካሉት መቶ ሆስፒታሎች በተጨማሪ  አሁን ላይ 36 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የጤናማ እናትነትን መርህ ለማሳካት የባለሙያዎችን አቅም እና  ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡ በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ ማድረግ፣ አንዲሁም ከጤና ተቋማት ለመድረስ ዘመናዊ እና ባሕላዊ አምቡላንስ አቅርቦት ያስፈልጋል፡፡ የእናቶች ማቆያም አስፈላጊ  ነው፡፡ ማሕበረሰቡም  የእናቶችን ሞት ለመከላከል በገንዘብ ማገዝ እንዳለበት ነው የጠቆሙት፡፡

አቶ አበበ እንዳብራሩት እንደ መንግሥት የሚመደብ በጀት እንዳለ ሆኖ ከማሕበረሰቡ እና አጋራ አካላት ለእናቶች ሀብት የማሰባሰብ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ለጨቅላ ሕጻናት ደግሞ የክትባት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቤተሰብ ዕቅድ እስከ ድህረ ወሊድ ድረስ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት አጋር አካላት፣ መንግሥት እና አመራሩ በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡

ትልቁ ሥራ መሻሻል ያለበት ብለው አጽንኦት ያደረጉበት ጉዳይ በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎትን የበለጠ እንዲሳለጥ ማድረግ ላይ ነው፡፡ በዚህ ስድስት ወርም ከ305ሺህ በላይ እናቶች በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት 75   በመቶ ናቸው በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎት የሚያገኙት፡፡  ቀሪዎቹ 25 በመቶ የሚሆኑትን እናቶች በጤና ጣቢያዎች እንዲወልዱ ለማድረግም የሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ወሳኝ  መሆኑን እና በተለይም አጋር አካላት አሁንም ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው  አቶ አበበ  ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው እንዳብራሩት የእናቶች ጤና የበለጠ የሚሻሻለው የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ሲጎለብት ነው፡፡ በሌላ መንገድ ከማሕበረሰቡ የሚጠበቀው የደም ልገሳ ነው፡፡ በመሆኑም ሕብረተሰቡ ያለመሰልቸት ደም በመለገስ የእናቶችን እና የሕጻናትን ሕይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በስድስት ወሩም ወደ 40 ሺህ ዩኒት ደም መሰብስቡን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ ያለውን ችግር ሲያብራሩም የተደራሽነት ችግር፣ ተደራሽነቱ ቢኖር እንኳ ሙሉ አገልግሎት አለመስጠት፣ ለተሻለ ሕክምና ከሚላኩ ሕሙማን ጋር ተያይዞ ክልሉ ካለበት ተጨባጭ ሁኔታ የአምቡላንስ እጥረት፣ የመንገድ ምቹ አለመሆን (የመንገድ መዘጋት) ያጋጥማል፡፡ ይህንን ለመፍታትም እናቶች መንገድ ከመዘጋቱ በፊት አስቀድመው ወደ ጤና ተቋም እንዲመጡ እና በተዘጋጀላቸው ማቆያ እንዲቆዩ የማድረግ ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በክልሉም ከስድስት መቶ በላይ በሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች የእናቶች ማቆያ መዘጋጀቱን ልብ ይሏል፡፡ 318 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ የአልትራሳውንድ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

እናቶች ጤናማ ሲሆኑ ጤናማ ሕጻን ይወለዳል፣ ጤናማ ቤተሰብ ይኖራል፣ ጤናማ ቤተሰብ ደግሞ ሀገር ያቆማል፡፡፡

ጤና አዳም

ጤናማ እናት ለመሆን መደረግ ያለበት…

ከእርግዝና በፊት፡-

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ከአልኮል፣ ከሲጋራ እና ከአደንዛዥ ዕጾች(መድኃኒቶች) መራቅ፣ ሙሉ የጤና ምርመራ ማድረግ…ያስፈልጋል፡፡

በእርግዝና ጊዜ፡-

የእርግዝና ክትትል ማድረግ፣ አይረን እና ፎሊክ አሲድ መውሰድ፣ ጤናማ ምግብ መመገብ፣  ከጭንቀት መራቅ ተገቢ ነው፡፡

በወሊድ ጊዜ፡-

የሰለጠኑ ባለሙያዎች ባሉበት የሕክምና ቦታዎች መውለድ ይገባል፡፡ ይህም በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር የደም መፍሰስን እና ኢንፌክሽኖችን ወዲያው ለማከም ይረዳል፡፡

ከወሊድ በኋላ፡-

የእናትን ጤናን መመርመር፣ ሕጻኑን ስድስት ወር እስኪሞላው ከጡት ውጭ ሌላ ነገር አለመመገብ ይመከራል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here