“ጤናማ ውድድርን እናሰፋለን!”

0
154

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

ከባለፈው ሣምንት የቀጠለ

በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች ብቅ እያሉ በሚያስተላልፏቸው አስተማሪና አነቃቂ ንግግሮቻቸው፣ ተስፋ በሚሰጡ ትልሞቻቸው እና ለወጣቶች በሚያቀርቧቸው የማበረታቻ ስጦታዎች ይታወቃሉ፡፡

‹‹እጄ ሰፊ›› ናቸው የሚባልላቸው ኢንጅነር ቢጃይ ናይከር አዋጭ የንግድ ሐሳብ ለሚያቀርቡ ወጣቶች ለፕሮጀክቶቻቸው ማስጀመሪያ ይሆናቸው ዘንድ ያለምንም ማስያዣ ከአንድ መቶ  ሽህ ብር ጀምሮ ሲለግሱ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ከኢንጂነር ቢጄይ ጋር የተደረገው ማራኪ ቆይታ የመጨረሻ ክፍል እንሆ፡፡

 

ቢሮ ሁልጊዜ ሲገቡ መጀመሪያ የሚያደርጉት ምንድን ነው?

ሁልጊዜ ቢሮ ስመጣ አስቸኳይ ነገር ከሌለኝ ልጆቹን አያለሁ፤ በየቢሮው እየገባሁ ሰላም እላቸዋለሁ:: ፊታቸው ላይ ደስታ ካለ ደስታውን እጋራለሁ፤ ፊታቸው ላይ ሀዘን ካለ ሀዘናቸውን እጋራለሁ፤ አጽናናቸዋለሁ:: ይህን አድርጌ ወደ ቢሮየ እገባለሁ:: ከዚያ በበየነ መረብ እና በአካል የመጡ እንዲሁም ያቀድኳቸውን ጉዳዮች መፍትሔ እሰጣለሁ:: ምሳ ከበላሁ በኋላ ሌሎች ሥራዎችን እከውናለሁ::

ፋብሪካዎቹ ብዙ ስለሆኑ የሠራተኞቼን ቁጥር አላውቀውም:: እኔ ከጅምሩ የጠነሰስኳቸው 87 ፋብሪካዎች አሉ:: በየሃገራት እነዚህ ፋብሪካዎች ይገኛሉ:: በሽርክና ያለሁባቸው አሉ:: አንዱ የማደርገው ምንድን ነው- ለምሳሌ ጎጃም ውስጥ አንድ ሰው የመስሪያ ቦታ (ሼድ) እና መሠረተ ልማት ኖሮት የሥራ ሀሳብ ከሌለው ፈልጌ አገኘዋለሁ፤ ባሕሪውን እና ሌሎች ነገሮችን እፈትሻለሁ:: ከዚያ ማሽን እሰጠውና  ሽርካ ሆነን አብረን እንሠራለን::   ይህን መሰል ሥራዎች በጣም ብዙ አሉኝ::

 

ከወጣቶች ጋር እንዴት ነው የምትሠሩት?

በብዙ መንገዶች ከወጣቶች ጋር እንሠራለን:: በተለይ አንዱ እና ዋነኛው ሀሳብ ያላቸውን፤ ነገር ግን ገንዘብ የሌላቸው ወጣቶችን ፈልፍለን፣ አብቅተን ወደ ሥራ የምናስገባበት ነው:: ይህን የምናደርግበት ማዕከል አለን::  ወጣቶቹ በማዕከሉ አንድ ላይ ሆነው ይሠራሉ:: መዋለ ንዋይ ይፈስላቸዋል፣ ብር መስጠት ብቻ ሳይሆን ድጋፍ እና ክትትል እናደርግላቸዋለን፤ በዚህ ሂደት ራሳቸውን ችለው ይወጣሉ:: እኛ የሽርካ ባለቤት እንሆናለን:: ሥራ ከጀመሩ  በኋላ በግብር እና የተለያዩ ወጪዎች ድጋፍ እናረግላቸዋለን:: ለምሳሌ አምስት ወጣቶች ከአደይ አበባ ሻምፖ፤ ኮንዲሽነር እና ሌሎች የመዋቢያ እና ንጽህና መጠበቂያ   ምርቶችን አምርቶ ወደ ውጪ መላክ የሚል ሀሳብ እና እውቀት ነበራቸው:: ሀሳቡን ይዘው መጡ፤ መዋለ ንዋይ አፈሰስን አካሄዱንም መራናቸው:: አደይ አበባ ከምናመጣባቸው አካባቢዎች አንዱ አማራ ክልል ነው፤ ደብረ ብርሀን እና ዙሪያው አረርቲ ዋና ዋናዎቹ ናቸው:: አሁን ምርት ጀምረን የገበያ ሥርዓት ዘርግተን ወደ ሥራ ልንገባ ነው:: ይሄኛው ቡድን እስከ ህዳር ያጠናቅቃል:: ሌላ በወተት ዱቄት ምርት ሀሳብ ያለው ቡድን ደግሞ ወደ ማዕከሉ ገብቶ፤ በቅቶ መዋለ ንዋይ አግኝቶ ምርቱን እውን አርጎ ይወጣል:: ወደ ንግዱ ይገባል እኛም ሽርካ እንሆናለን::

እኛ ጋር ተቀጣሪ የነበሩ ብዙ ልጆች አሉ:: አደራጀናቸው ከዚያ ክህሎት እና መሠረተ ልማት አሟላንላቸው::  እኛ ጋር ያመርቱት የነበረውን እቃ ራሳቸው አምርተው እኛ ጋር ያቀርባሉ:: ማሺን አምርተው ለእኛ የሚያቀርቡ 24 ልጆች አሉ::

አብረውኝ የሚሠሩት ወጣቶች ከሁሉም የሀገራችን ክፍል የተወጣጡ ናቸው:: ዋነኛ መሥፈርታችን እውቀት ነው እንጂ አካባቢ አይደለም:: ለምሳሌ የዲዛይን ክፍላችን ውስጥ ከሀረር፣ ከጋሞ፤ ከወለጋ፣ ከባሕር ዳር እና ሌሎች ከተሰባጠሩ ቦታዎች የመጡ ልጆች ናቸው::

 

 

የበጎ ሰውነት ሽልማት ተሸልመዋል፤ ስለዚህ ቢነግገሩን?

ብዙ የማላስታውሳቸው ሽማቶች አሉ፤ የበጎ ሰው ሽልማት ተበርክቶልኛል፤ ግን እኔ በጎ ነኝ ብየ አላስብም፤ ሽውልማቱ የሚገባቸው ብዙ በጎ ሰዎች አሉ::

 

እማማ እርጎየ ማን ናቸው?

እማማ እርጎየ ጓደኛየ ናት፤ ጓደኛየ ስለሆነች አንቺ ነው የምላት:: ከጎንደር ነው የመጣችው የነገረችኝን ሳሰላው 78 አካባቢ ይሆናል እድሜዋ:: በልመና ነው የምትተዳደረው፤ የምትቀበለው የእለት ጉርሷን ብቻ ነው:: ከዛ የዘለለ ቢሰጣት አትቀበልም:: ቤተክርስቲያን በር ላይ ነው የምትኖረው:: ከዛ ውጪ መኖርም አትፈልግም:: ፍላጎቷን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ ሌላው አሁን ቆርባለች፤ ብዙ ሰው እሷን አገናኘን ይላል፤ ስለቆረበች ሰዎችን ማግኘት አትፈልግም::

የተለያዩ የሕይወት ፍልስፍናዎችን ትነግረኛለች:: ለምሳሌ በጎ ሰው ማለት ምን ማለት ነው? ብየ አንዳንዴ ጠየቅኋት፤ “በጎ ሰው ማለት ካለው ግዙፍ ነገር ቆንጥሮ የሚሰጥ ሳይሆን ከሌለው ነገር ላይ ዘግኖ የሚሰጥ ነው” ትለኛለች:: ትንሽ ነገር ኖሮህ ዘግነኸው ያለህን ነገር ነው የምትሰጠው እንደማለት ነው:: ካለህ ግዙፍ ነገር ላይ ቆንጥረህ መስጠት ስሜቱም አይኖረውም፤ መስጠትም አይባልም::  ካለህ ነገር ማለት ደግሞ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ፍቅር እና ሌላም ሊሆን ይችላል በሰፊው ዘግነህ መስጠት ነው:: “በጎዎች ራሳቸውን የሚፈትኑ ናቸው” ትላለች:: እማማ እርጎየ እንደዚህ አይነት ሰው ነች::

ሀሳብ ላላቸው ሰዎች በማኅበራዊ መገናኛ አወዳድረው የ100, 000 ብር ሽልማት ያበረክታሉ? ሀሳቡ እንዴት መጣ? ዓላማውስ ምንድን ነው?

ከኮሮና በኋላ የተማርናቸው ብዙ የሕይወት ዘይቤዎች አሉ:: ለምሳሌ ለአራት ወራት ታምሜ ነው የተነሳሁት:: ከህመሙ በኋላ እንዴት ነው ወጣቱን መርዳት የምችለው ብየ ፕሮግራም አወጣሁ:: የመጀመሪያው ምንድን ነው ነጻ ሀሳብ ማካፈል ነው:: አዕምሮን እምቅ አቅም የመክፈት ሥራ ነው:: ለምሳሌ ይህን ብትሠሩ ያዋጣል፤ ይህን ብታደርጉ እንደዚህ ይሆናል እያሉ የማማከር እና የመቀስቀስ ሥራ ለሁለት ዓመት ሠራን::

የመጀመሪያው ደረጃ ካለቀ በኋላ ወደ ገንዘብ ነው የሚኬደው:: ይህ ነገር በተለይ እኛ ሀገር ላይ አስቸጋሪ ነው:: ለምሳሌ ባንኮች ለወጣቶች የሚሆን የሀሳብ ገንዘብ ያለ ማስያዣ አይሰጡም:: ስለሆነም የማኅበረሰብ ማስያዣ (community collateral) የሚለው ጽንሰ ሀሳብ እንዲመጣ እፈልጋለሁ:: ለምሳሌ አቆልቋይ፣ መሶብ፣ ቅንጃ፣ ደቦ፣ እቁብ እና እድር የመሳሰሉ ማኅበራዊ እሴቶች ለወጣቱ ጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ውስጥ ገባን:: እሱን ለማለማመድ ያህል ለማላውቃቸው ሀሳብ ላላቸው ሰዎች እድል ሰጠሁ:: ይህንንም በ32 ቃላት ሀሳቡን የገለጸ እና ብዙ ሰው የወደደው ተመራጭ ይሆናል::

“ይህን ልጅ አውቀዋለሁ፣ ጎበዝ ነው፣ ብትሰጠው” የሚለው ድምጽ የማኅበረሰብ ማስያዣ ሆነ ማለት ነው:: በዚህ መሠረት የተመረጡ ልጆች 100,000 ያገኙበት ነው፤ ሽልማት ሳይሆን የሠሩበት ነው:: ይህ እንግዲህ ቅድም ያነሳኋቸውን ለማኅበረሰቡ ለማስተማር የተጠቀምኩበት ነው:: በምርጫው ወቅት ከ87 ሺህ በላይ አስተያየት ሰጪ በማኅበራዊ መገናኛው የምናገኝበት ነበር:: በዚህ ሀገር እንግዲህ ትልቁ ቁጥር ነው ማለት ነው:: ይህ ብዙ የማኀበረሰብ መነቃቃትን ፈጠሯል::

በሦስተኛ ደረጃ የሚመጣው ስልጠና ነው:: አንድ ሰው ሀሳቡን ማፍለቅ ከቻለ፤ ይህን ወደ ተግባር ለመቀየር ያጣውን ገንዘብ ካገኘ በኋላ እንዴት ፕሮጀክቱን ይመራዋል፤ ያስፈጽመዋል የሚለው ነገር ይመጣል:: በውድድሩ ያሸነፉ ልጆችን የስትራቴጂ እና ፕሮጀክት አስተዳደር ስልጠናዎችን እሰጣቸዋለን:: የእስካሁኑ እንደ ሙከራ ነው የተጠቀምንበት:: ሙከራው ጥሩ ተሳክቷል::

 

በእርስዎ መንገድ ምን መማር ይቻላል?

አንደኛው እርዳታን እዳ ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ አንድ ሰው በሀሳቡ እና በእውቀቱ ተወዳድሮ ገንዘብ ማግኘት እንደሚችል የምንማርበት መድረክ ነው:: የመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎችን የሚፈትን ነው:: ለወጣቶች የብድር አገልግሎት ያለ ማስያዣ የሚሰጥበት ፖሊሲ ባለመኖሩ መድረኩ ወጣቶች ከፖሊሲው ውጪ ታምነው መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው:: ሌላው የገንዘብ ተቋማት ወጣቶችን በሀሳባቸው አምነው ገንዘብ እንዲያቀርቡ እና ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ እና ማኅበረሰብ እንዲጠቅሙ ያመላከተ ነው:: በተጨማሪ ጤናማ ውድድሮች እንዳሉ ወጣቶችን ማስተማር ተችሏል:: በቀጣይ በሁሉም ክልሎቻችን ጤናማ ውድድርን እናሰፋለን!

 

ለወጣቱ ምን ያስተላልፋሉ?

ሁሉም ወጣት በውስጡ የተቀበረ ሀሳብ አለው፤ ይህን የላቀ ሀሳብ  ቆፍሮ ማውጣት ካልቻለ የሀሳቡ ሬሳ ሳጥን ነው የሚሆነው:: ወጣቶች ሀብት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን መንገድ መከተል አለባቸው::

የአንድ ማኅበረሰብ  አራት የኑሮ ማገሮች አሉት:: እነዚህ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የቴክኖሎጂ ናቸው:: አንዱ ከረዘመ ወይም ካጠረ ልክ አይመጣም፤ ለምሳሌ አንድ ወንበር ሦስቱ አጥሮ አንዱ ከረዘመ እሱን መቁረጥ ነው የሚያስፈልገው:: ስለዚህም የተመጣጠነ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖር ሁሉንም ማገሮች እኩል ማድረግ ያስፈልጋል፡ ወጣቶች ከሁሉም የተመጣጠነ ነገር ሊኖራቸው ይገባል፤ በአንዱ ወይም በሁለቱ ላይ ብቻ አብዝተው መያዝ አያስፈልጋቸውም፤ ማመጣጠን እጅግ አስፈላጊ ነው:: ለምሳሌ አብዝቶ ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልግም፣ አብዝቶ ገንዘብ መሰብሰብም እንዲሁ::

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

 

እኔም አመሰግናለሁ!

 

 

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here