የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ መንገዶች በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። የቅሪተ አካል ነዳጅን በማውጣት እና በማቃጠል የሚከሰቱ በካይ ጋዝ (የግሪን ሃውስ) ልቀቶች ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለአየር ብክለት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። በዓለማችን ላይ በከሰል እና በእንጨት የሚሠሩ የጭስ ማስዎጫ የሌላቸውን ምድጃዎች በመጠቀማቸው ሳቢያ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ የቤት ውስጥ የአየር ብክለት ተጋልጠዋል፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከዋነኞቹ የሞት መንስኤዎች መካከል ሲሆኑ ብዙዎቹ ከአየር ብክለት ጋር የተያያዙ ናቸው። በዓለማችን ካሉ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች ወይም የሞት መንስኤዎች መካከል በገዳይነታቸው በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል፡፡ በዋናነት በመተንፈሻ አካላት፣ በልብ እና በደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በዓመት ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም በአየር ብክለት ይሞታሉ፡፡
ባለፈው ዓመት (2024) በወጣ የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ ባንግላዴሽ፣ ፓኪስታን እና ህንድ በዓለማችን ከፍተኛ የአየር ብክለት ካለባቸው ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት አማካኝ የአየር ብክለት ብሎ ካስቀመጠው መስፈርት እነዚህ ሀገራት 10 እጥፍ የባሱ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተያያዘም ግሪን ፒስ ኦርግ //www.greenpeace.org/ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በአፍሪካ ለአየር ብክለት መጋለጥ ሁለተኛው የሞት መንስኤ ነው፡፡ በካይ ልቀት በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞትን እያስከተለ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
ግብፅ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያለማቋረጥ ትልቅ ችግር ውስጥ እንዳሉም መረጃው አመላክቷል፡፡ ሀገራቱ ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር እያስተናገዱ የሚገኙት ከቅሪተ አካል በሚወጣ የነዳጅ አየር ብክለት ጋር በተያያዘ ነው። የነዳጅ ኢንዱስትሪ የአፍሪካ ከፍተኛ የአየር ብክለት ምንጭ እንደሆነ ነው አዲሱ የግሪንፒስ ዘገባ የሚያሳየው፡፡
ዘገባው እንደሚያመላክተው በዓለም ላይ ካሉት አስር ትላልቅ የናይትሮጅን ኦክሳይድ (NO2) ልቀት ቦታዎች መካከል ስድስቱ በደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ። በዓለም ላይ ካሉት አስር ግዙፍ የሰልፈር ዳይኦክሳይድ (SO2) ልቀት ቦታዎች ደግሞ ሁለቱ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በአፍሪካ ውስጥ ከተለዩት አስር ትላልቅ የሰልፈር ዳይኦክሳይድ (SO2) ምንጮች ዘጠኙ የሙቀት ኀይል ማመንጫዎች ሲሆኑ አንደኛው በማሊ ውስጥ ካለው የጭስ ማውጫ ኮምፕሌክስ ጋር የተያያዘ ነው። ከኀይል ማመንጫዎቹ ውስጥ አራቱ በደቡብ አፍሪካ፣ ሁለቱ በሞሮኮ፣ በግብፅ እና አንደኛው በዚምባብዌ ይገኛል።
በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ብክለትን ካስወገዱ እና የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎችን ካሟሉ በሕይወት የመቆያ ዕድሜ እስከ ሦስት ዓመት ሊሻሻል እንደሚችል የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተሠሩ ጥናቶች አመላክተዋል።
ለጥሩ ጤና ንፁህ አየር፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መጠለያ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጅ የአየር ንብረት ለውጥ እነዚህን ነገሮች ያበላሻል፡፡ በዓለም አቀፍ ጤና ውስጥ የአስር ዓመታት እድገትን የመቀነስ አቅም እንዳለውም ነው የዓለም ጤና ድርጅት የገለጸው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው እ.አ.አ. በ2030 እና 2050 መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በወባ፣ በተቅማጥ እና በሙቀት መጨመር ብቻ ወደ 250 ሺህ የሚጠጋ ተጨማሪ ሞት ያስከትላል ተብሎ ይጠበቃል። በ2030 በጤና ላይ የሚደርሰው ቀጥተኛ ጉዳት በዓመት ከሁለት እሰከ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም የዓለም ጤና ድርጅት ጠቁሟል።
በአብዛኛው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትልባቸውን ጉዳት ለመቆጣጠርና ለመቀልበስ እርዳታ ካልተደረገላቸው በራሳቸው ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ነው የተነገረው።
በአየር ንብርት ላይ የሚወጡ ፖሊሲዎች እና በግለሰብ ደረጃ የሚወሰዱ ርምጃዎች የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን የመቀነስ አቅም አላቸው።
ይህ በእንዲህ እዳለ ከሰሞኑ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከ47 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ ታካሚዎች፣ ተሟጋቾች፣ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ግለሰቦች የአየር ብክለትን ለመቀነስ እና በሰዎች ጤና ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ተጽዕኖዎችን ለማስወገድ አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድ ጠንከር ያለ ጥሪ በማድረግ ተፈራርመዋል።
ፊርማቸውን ያሳረፉ አካላት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ “ድምጻቸው ሊሰማ ይገባል!” ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም ጤና ድርጅት የአየር ብክለትን ለማስወገድ እና የሚያስከትለውን በሽታ ለመከላከል በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ መሳሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሀገራትን እየደገፈ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው ።
በከተሞችም ሆነ በገጠር ያለው የአየር ብክለት ጥቃቅን ቁስ አካላትን ይፈጥራል፡፡ ይህም እንደ ስትሮክ፣ የልብ ሕመም፣ የሳንባ ካንሰር፣ ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት እና እንደ የሳንባ ምች ያሉ አጣዳፊ በሽታዎችን ያስከትላል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ እና ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር ማሪያ ኔይራ “ንፁህ አየር ልዩ መብት አይደለም፤ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና የተሰጠው ሰብአዊ መብት ነው። ከድንጋይ ከሰል ኀይል ወደ ታዳሽ ኀይል የሚደረገውን ሽግግር ለማሳደግ በከተሞች ውስጥ ዝቅተኛ ልቀትን በመተግበር እንዲሁም በጤና ተቋማት ውስጥ ለምግብ ማብሰያ የፀሐይ ኀይልን ለማስፋፋት በጋራ መሥራት አለብን” በማለት አስገንዝቧል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች፡፡ ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ይመክራሉ፡፡ ጉባኤው በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ይህ ኮንፈረንስ በአየር ንብረት ሳይንስ ዕውቀት ላይ በየጊዜው ሁሉን አቀፍ እና ሥልጣናዊ ሳይንሳዊ ግምገማዎችን ለፖሊሲ አውጪዎች ያቀርባል፡፡
እ.አ.አ. ከ1995 ጀምሮ የመጀመሪያው የአየር ንብርት ጉባኤ(COP1) በበርሊን (ጀርመን) ሲካሄድ ሀገራት በየዓመቱ የሚያስመዘግቡትን መሻሻል ለመለካት እና ርምጃ ለመውሰድ ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡
በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በታኀሳስ 2015 የፓሪስ ስምምነት ተብሎ በሚጠራው ስምምነት እያንዳንዱ የ195 ግዛት ፈራሚዎች በ2025 ወይም በ2030 የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ወይም ለመገደብ በተናጠል እንቅስቃሴ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ስምምነቱን በፌርማቸው በማተም የዓለም ሀገራት የዓለም ሙቀት መጨመርን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለመገደብ ወስነዋል፡፡ በዚህ ስምምነት ያደጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ለታዳጊ ሀገራት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ስምምነቱን በመፈረም ሀገራቱ የግሪን ሀውስ ልቀትን እንዴት እንደሚቀንሱ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መላመድ እንደሚችሉ የሚገልፅ የየራሳቸውን የውዴታ ቃል ኪዳን ለማቅረብ እና ለማስረከብ ቁርጠኞች ሆነዋል። ቃል ኪዳኖቹ በስምምነቱ ግቦች ላይ የጋራ እድገትን በሚገመግም ዓለም አቀፍ ዘዴ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ስምምነቱ የተለያዩ ሀገራት የገቡትን ቃል በግልፅ በማሳየት ቃላቸውን መፈጸም ካልቻሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያስችላል።
ሀጋራቱ ይህንን ስምምነት ያድርጉ እንጂ ከተወሰኑ ሀገራት ውጪ አሁን ያለው ሁኔታ የዓለም ሙቀት መጨመርን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለመገደብ በቂ እንዳልሆነ ነው በአየር ንብረት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት የገለጹት፡፡
የካርቦን ዳይኦክሳይድ (co2) እና ሌሎች የሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ንፁህ ዜሮ ልቀት ላይ ለመድረስ ግብ ካወጡ ጥቂት ሀገራት መካከል ስዊድን ፣ ኖርዌይ፣ ፊላንድ እና ኦስትሪያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህም በሕጋዊ መንገድ የተጣራ ዜሮ ዒላማዎችን ከፈጸሙት ሀገራት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው::
እንግሊዝ በ2050 የተጣራ ዜሮ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ላይ ለመድረስ ቁርጠኝነት በማሳየት ከቡድን ሰባት (G7) ወይም ፈርጣማ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች።
ሀገራቱ የግሪን ሀውስ ልቀትን በመቀነስ የልቀት ቅነሳ ዒላማዎችን እየተገበሩ ነው፡፡ በታዳሽ ኀይል ላይ ኢንቨስትመንቶችን እና ዓለም አቀፍ የፓሪስን ስምምነት መተግበር፣ የግሪንሀውስ ጋዝ ታክስን መጨመር፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስተዋወቅ እና በንጹህ ቴክኖሎጂዎች ላይ ምርምር እና ልማትን የመደገፍን ተግባር እያከናዎኑ ናቸው፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም