ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣቶች በምግብ፣ በውኃ እንዲሁም ለመተንፈስ ከሚያገለግለው አየር ጋር ተቀላቅለው ወደ ሰውነት በመግባት በአንጐል፣ ጉበት፣ አንጀት እና ኩላሊት ላይ ተጽእኖ በማድረስ ለጤና ጠንቅ መሆናቸው መረጋገጡን ፎክስ ኒውስ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
ድረ ገጹ በቅርቡ የተካሄዱ ሁለት የጥናት እና ምርምር ውጤቶችን ለህትመት አብቅቷል:: ሂደቱን በተመለከተ በመጀመሪያዉ ከሰዎች በፊት ለምርምር በሚመረጡት አይጦች- ለስምንት ሳምንት የፕላስቲክ ቅንጣቶች እንዲበሉ አድርገዋል:: ከዚያም የበሉት የፕላስቲክ ቅንጣት በተለያዩ የአካል ክፍሎች መድረሱን እና ያስከተለውን ለውጥ ገምግመዋል::
በተመሳሳይ በሁለተኛው ምርምር ደግሞ በቀጥታ በችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከምን? በምን? እንዴት? የጤና እክሉ ሊከሰትባቸው እንደቻለ ትኩረት አድርገዋል::
የጥናት እና ምርምር ቡድኑ መሪ ዶክተር ጃኒት ኔሽዋት ለፎክስ ኒውስ የፕላስቲክ ቅንጣቶች በሁሉም ቦታ እንደሚገኙ እና ለጤና ስጋት መሆናቸውን አስረድተዋል::
እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በሚበሉ፣ በሚጠጡ እና ለመተንፈስ ከሚሳብ ከባቢ አየር ጋር ተቀላቅሎ በመግባት እብጠትን ያስከትላሉ::
ማንኛውም ከውጪ ወደ አካል ውስጥ የሚገባ የፕላስቲክ ቅንጣት ከጉሮሮ ጀምሮ በሚደርስበት የአካል ክፍል የጤና ጉዳት እንደሚያስከትልም አስምረውበታል- ተመራማሪዎቹ::
እንደየአካሉ ዓይነት የሚያደርሱትን ጉዳት በተመለከተ በአንጐል ውስጥ የመልዕክት ሞገድ መቆረጥ እና መዛባት፣ በኩላሊት ውስጥ የተስተካከለ የፈሳሽ እንቅስቃሴን በመግታት እብጠት እንደሚያስከትሉ ነው የደረሱበት:: በተጨማሪም በጉበት ላይ ውጥረትን እና እብጠትን በመፍጠር የተስተካከለ ሂደትና ውጤት እንዳይከወን ጫና ያሳድራሉ::
በመጨረሻም ማናቸውም ከውጪ ወደ አካል የሚገቡ የፕላስቲክ ቅንጣቶች ብዛቱ ከፍ ባለ ቁጥር የሚያደርሱት የጤና እክል ስር የሰደደ ሊሆን እንደሚችል አስምረውበታል::
በመሆኑም የፕላስቲክ ቅንጣቶች የሚያደርሱትን የጤና እክል ለመቀነስ የፕላስቲክ መገልገያዎችን በመተው ጠርሙስና ሊበሰብሱ የሚችሉ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም