ጥላሁን ገሠሠ በሌላ መልኩ

0
298

ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ለሃምሳ ዓመታት በሃገራችን ሙዚቃ ግንባር ቀደም ሆኖ አልፏል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ የሚል መጠሪያ ያገኘው። በድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ የህይወት ታሪክ ዙሪያ ዘከሪያ መሃመድ በፃፈው መጽሃፍ ላይ በመመስረትም ባለፈው ሳምንት እትም “ጥላሁን ገሠሠ በሌላ መልኩ” በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል። ቀጣዩ እና የመጨረሻ ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው ቀርቧል።

“ጥላሁን አሳማሚውን እውነት ካደው፣ አሳማሚው እውነት ሲካድ ከተፈጠረው ክፍት ቦታ ሌላ እውነት ያልሆነ መረጃ ተካበት። ይህንን መረጃም ለጋዜጠኞች ነገራቸው። እነርሱም ጽፈው በጋዜጣ እና መጽሔት አተሙት” ይላል ዘከሪያ በመጽሐፉ። ጥላሁን የእናቱን ስም ሲናገር ጌጤነሽ ግርሙ በማለት ነው። ነገር ግን ዘከሪያ ዋቢ አድርጎ በጻፈው የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ውስጥ የተጻፈው  የዘር ሐረግ ጌጤነሽ ኢተአ የሚል ነው። ጌጤነሽ በ1938 አዲስ አበባ ስትመጣ፤ ያመጣት አጎቷ ስም ነው። ጉርሜሳ የሚለውን ግርሙ በማለት ነው። እሷም በመኮብለሏ ነው እንዳትታወቅ ስትል የአባቷን ስም የቀየረችው። ጥላሁንም ይህንን ስም ትክክል አድርጎ ወስዶት ሲናገረው ኖሯል።

ጥላሁን ደብረ ብርሃን በሚከርምባቸው አጋጣሚዎች የአቶ ፈይሳ ኀይሌን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ  ያነብብ ነበር። ዘከሪያ መሐመድ የፈይሳ ኀይሌን ልጅ ሳምሶንን አንድ ጥያቄ  አቀረበለት። ጥያቄውም ጥላሁን አባባ ፈይሳ ስለ ራሱ የጻፉትን ታሪኩን አንብቦ አስተያየት ሲሰጥ ሰምተኸው ታውቃለህ የሚል ነበር።

ሳምሶንም አሰብ አደረገና ጥላሁን እንዴት እንደተቀመጠ፣ ምን እንደለበሰ፣ ፊቱ እና ገጽታው ምን ይመስል እንደነበር በማስታወስ ጥላሁን የነገረውን ለዘከሪያ አጫወተው። “አሁን እኔ ይኽን ታሪክ ባወጣው፣ በቀሪ የሕይወት ዘምኔ ከጋዜጠኞች ጋር ስዳረቅ ነው የምኖረው…” ብሎ ጥላሁን አጫወተኝ ይላል ለዘከሪያ ሲናገር። በመቀጠልም ጥላሁን ለሳምሶን “እኔ ስሞት ግን ይኼን ታሪክ አትተኙበትም” በማለት የጥላሁን እውነተኛ ታሪክ  እሱ በብዙኀን መገናኛ የሚናገረው እንዳልሆነ፣ ይልቁንስ እሱ ከሞተ በኋላ ታሪኩን እንዲያሳትሙት እና ለሕዝብ እንዲደርስ ፍላጎት እንዳለው ነገረው። ጥላሁን ከዚህ ቀደም ከእውነት ሽሽት በማድረግ ታሪክ ፈጥሮ ለሚዲያ አውርቷል። ስለ እድገቱ፣ ውልደቱ እና ቤተሰቡ። ብዙውን በማድበስበስ አልፎታል። የታሪክ ማስታወሻውን የእኔ ታሪክ ነው ብሎ ቢናገር ደግሞ ‘ቀድሞ እንዲህ ብለህ አልነበር ፣ እሁን ከየት አመጣኸው፣ ድሮውንስ ለምን ዋሽተህ ተናገርክ’  የሚል ወቀሳን ያመጣበታል። ለዚያም ነው ስሞት ታሪኬን እንዳትተኙበት ያለው። ምስጋና ለዘከሪያ መሐመድ ይሁን ሌላኛውን ጥላሁንን ልናየው በቅተናል።

ኅዳር 12 ቀን 1962 ዓ.ም ጌጤነሽ /የጥላሁን እናት/ በአዲስ አበባ  ጨርቆስ አካባቢ በጠጅ ንግድ ሥራ ተሠማርታ ስትኖር  በአንድ ክንፈ በሚባል ሰው በሽጉጥ ተመትታ ተገደለች። ክንፈ እና የሺ ባልና ሚስት ነበሩ። የሺ የወሊሶ አካባቢ ሴት  እና በጠጅ ንግድ የምትተዳደር ሴት ነበረች። ጌጤነሽ ደግሞ ባል የላትም። ክንፈ እና ጌጤነሽ የአንድ አካባቢ ሰዎች ነን በሚል ወዳጅነታቸውን አጠናከሩት። ጌጤነሽ ቤት በጉርብትና  የምትመላለሰው የሺ “ጎልማሳ እና ወጣት ወንዶች ከሚመላለሱበት የጊዜ ማሰለፊያ  ጠጅ ቤት” አትመላለሽ ብሎ ክንፈ ሚስቱን አስጠነቀቀ። ጌጤነሽ ቤት አትሂጂ በማለት ይከለክላት ነበር። ሚስቴን  ሌላ ወንድ ያውቅብኛል  በሚል ነበር ስጋቱ። የሺ ግን አሻፈረኝ አለች። ጌጤነሽንም እባክሽን ይህች ልጅ አንቺ ቤት አትምጣ ብሎ ጠየቃት። “ምነው የአንድ ሀገር ልጆችም አይደለንም እንዴ” ብላ ቀለል አደረገችው። የሺ ጌጤነሽ ቤት መሆኗን የተረዳው ክንፈ ሽጉጡን መዝዞ ወደ ጌጤነሽ ቤት ተጓዘ። የሺንም፥ ጌጤነሽንም ገድዬ  ልገላገል ብሎ አስቦ ነበር። ሽጉጡን በሁለቱም ላይ አከታትሎ ከተኮሰ በኋላ አመለጠ። ጌጤነሽ ሞተች፤ የሺ ቆስላ ተረፈች። ገዳዩ ክንፈ  ተሰወረ።

መሳቁን ይስቃል እና ሐርካፉኔ ዘፈኖችን ጥላሁን ሲዘፍን እናቱን እያስታወሰ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ገብቶ ስለሚዘፍናቸው እንባው ይፈስ ነበር ይላል ዘከሪያ በመጽሐፉ። ጌታቸው ደስታ የጥላሁን የቅርብ ወዳጅ ነበር። ጥላሁን በሠርግ እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲጋበዝ የሚያቀርበው ዘፈን በለቅሶ እና እንባ የታጀበ ሆነ። ጌታቸውም አንድ ቀን ጥላሁንን ተቆጣው። “ምንድን ነው አንተ እንዲህ የሚያደርግህ? በዘፈን እንግዶቻቸውን ሊያዝናኑ ገንዘብ በከፈሉ ሰዎች ላይ  ነው እንዴ የምታለቅሰው?” አለው። ጥላሁንም ይመልሳል። “ወድጆ’ኮ አይደለም ጌታቸው። እኔ እዚህ ቆሜ እዘፍናለሁ፤ ይኼኔ የእናቴ ገዳይ አንድ ስፍራ ላይ በነጻነት ይፏልላል። …እያልኩ ማሰቤን ፍርድ ሳላገኝ   እንዴት ላቆም እችላለሁ?!” ብሎ ለጌታቸው ሲመልስለት ልቡ ተነካ።

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጥላሁንን ቃለመጠይቅ አድርጋው ነበር። ”ከሙዚቃ ለሰከንድ መለየት አልፈልግም፣ የሙዚቃ መሣሪያ ጋጋታው እንኳ ቢቀር ቤቴ ውስጥ አንጎራጉራለሁ። እኔ የእናቴን ሕይወት የለወጥሁት በሙዚቃ ነው” ሲል ተናግሮ ነበር። ከብዙ ማፈላለግ በኋላ የጥላሁን እናት ገዳይ ወሊሶ ከተማ ውስጥ እንደሚኖር አወቀ ። ይቅር ብየዋለሁም አለ።

መስከረም ወር 1977 ዓ.ም ጥላሁን አሜሪካን ሀገር ኮንሰርት እንዲያቀርብ ግብዣ መጣለት። በጣም ተደስቶ ለመሄድ ሲሰናዳም ከሀገር ሊጠፋ ይችላል ብለው የአብዮቱ ጠባቂዎች ከለከሉት። እንዲያውም ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ለስራ እንዲዘጋጅ ተነገረው። ጥላሁን አልሄድም ብሎ ራሱን ሰውሮ ተደበቀ። የማዕከላዊ እዝ ባንድ አባላት ጉዟቸውን አደረጉ። ባንዱ ሥራውን ሲያቀርብ “ጥላሁን ጥላሁን” የሚል የመድረክ ድምጽ አስተጋባ። ጥላሁን ባለመኖሩ ዝግጅቱ እንከን ገጠመው። ጥላሁንን ከአዲስ አበባ አስገድደው ወሰዱት። በግዴታ አዘፈኑት። አፈሙዝ ተደግኖበት ዝግጅቱ ላይ ይዘፍን ጀመር። ሲያቅተው ራሱን ስቶ ወደቀ። በኋላም አማኑኤል የአእምሮ ሕሙማን ሆስፒታል ገባ።

እሑድ ሚያዝያ 10 ቀን 1985 ዓ.ም የትንሳኤ ዕለት ደግሞ እንዲህ ሆነ። ሆዱን፣ ጉሮሮውን እና እጁን መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ተወግቶ ዘውዲቱ ሄስፒታል መግባቱ ተሰማ። ቀጥሎም ወደ እንግሊዝ ሀገር ለተሻለ ሕክምና ሚያዝያ 16 ቀን 1985 ዓ.ም ጉዞ አደረገ። ጥላሁን ራሱን የማጥፋት ሙከራ አደረገ ወይስ ሌላ  ሰው ጉዳት አደረሰበት የሚለው ዛሬም ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሄኖ ቀጥሏል። ጥላሁን አደጋውን ያደረሰብህ ማን ነው ተብሎ ሲጠየቅ “ሆድ ይፍጀው” ከማለት ውጪ ምንም አላለም። ለጓደኛው ጌታቸው ደስታ ደግሞ ራሴ ነኝ የሚል ምላሽ ሰጥቶታል ጥላሁን።

ዘከሪያ መሐመድ ጥላሁን ፈለቀች ማሞ የምትባል ልጅን  ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳገባ ይተርካል። ጋብቻውም በሠርግ ነበር። ፈለቀች ደግሞ 13 ዓመቷ ነበር። እሱ ደግሞ 17 ዓመት ከአራት ወራት ዕድሜም ነበረው። ጥላሁን ያገባትን ሚስት እናቱም፥ አያቱም አልወደዱለትም።

ሙሽሮች አንድ ልጅ ወልደው በጨቅላ ዕድሜው አረፈ። መጀመሪያ ቤተሰቦች አዝማሪ አታገቢም ብለውት የነበረችው ፈለቀች የጥላሁን ዝና እየጨመረ ሲመጣ “እኔ ችላ ተባልሁ” ብላ ለጥላሁን ሳትነግረው ጥላው ወደ ወላጆች ቤት ሄደች። ክፉኛ የተበሳጨው ጥላሁን እስከ መጨረሻው ረሳት።

ይህ ጋብቻ ፈርሶ ጥላሁን ሌላ ልጅ ተዋወቀ። አስራት ዓለሙ ትባላለች። ጥላሁን የመጀመሪያ ሚስቴ ይህቺ ነች ሲል ነው ያለፈው። ፈለቀች የምትባል ሴት አላውቅም ነው ይል የነበረው። ለሦስት ዓመታት አብራው የኖረችውን ፈለቀችን እንደማያውቃት በተደጋጋሚ ተናግሯል። አስራት ዓለሙን በ1953 ዓ.ም ቀለበት አሰረላት፤ በ54 ዓ.ም ደግሞ ጋብቻቸው ተፈጽሟል። የሙዚቃውን ወርቃማ ዘመን ያሳለፈውም አምስት ልጆች ከወለደችለት አስራት ዓለሙ ጋር በመሆን ነበር።

ከአስራት ጋር ጥሩ ፍቅር ቢኖራቸውም ፌሪያል የምትባል ሴት ወደደ። እሷም ጋር ቤቱን ትቶ መኖር ጀመረ፤ ፌሪያልም አስራትን እየደወለች ታበሽቃት ነበር። አስራትም በጋብቻ ላይ ጋብቻ ለምን ፈጸመብኝ ብላ ከሰሰችው። ጥላሁን ራሱን ለመከላከል ወሰነ። ፍርድ ቤትም ቀርቦ “በጋብቻ ላይ ጋብቻን ሀይማኖቴ ይፈቅዳል” ሲል ተከላከለ። ጥላሁን የክርስትና እምነት ተከታይ እንደነበር ሀገር ያውቃል። “ርግጥ ነው ክርስቲያን ነበርሁ። ነገር ግን ወደ እናቴ ሀይማኖት ተመልሻለሁ። ትዳሬን ሳልፈታ ሁለተኛ ሚስት ያገባሁት ሙስሊም ከሆንኩ በኋላ እንጂ በክርስትና ስር ሳለሁ አይደለም። በእስልምና እስከ አራት ሚስት ማግባት የተፈቀደ ነው” በማለት መልስ ሰጠ። ጥላሁን አስራትን ፈትቶ ፣ ሀብት ንብረቱን ለአስራት ትቶ   ፌሪያል መሐመድን አግብቶ መኖር ጀመሩ። ዘግይቶም ነሐሴ 13 ቀን 1976 ዓ.ም የጥላሁን እና አስራት ሰማንያ ተቀደደ።

ጥላሁን እስልምናን ተቀብያለሁ ቢልም እንኳን በሀይማኖት በኩል ብዙም ለውጥ አልታየበትም ነበር ይላል ዘከሪያ በመጽሐፉ። በአካል እና ዳንኤልን ከፌሪያል ወልዶ ተለያዩ።

ጥላሁን አሁንም ልቡ ወደ ሌላ ሴት ሸፈተ። ፌሪያል የበረራ አስተናጋጅ በመሆኗ ከአገር አገር ስትዘዋወር ቤት የማትኖርባቸው አጋጣሚዎች ይበዙ ነበር። ይህም ጥላሁን ወይዘሮ ብርሃኔ ዘለቀ ከምትባል ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲጀምር አድርጎታል። ልጆች ነበሯት፣ የ40 ዓመት ሴት ነበረች። ትንከባከበውም ነበር። ከስድስት ዓመት በላይ የኖረበትን የፌሪያልን ቤት “እዚህ ቦታ ሄጃለሁ” ሳይል  ሻንጣውን ይዞ ወጣ፤ ብርሀኔ ዘለቀ ቤትም መኖር ጀመረ ይላል ዘከሪያ።

ጥላሁንን ድሮ ገና አፍላ ወጣት ሆኖ ሲዘፍን የምታውቀል ሒሩት ምትባል ልጅ ነበረች። ልታገባው ፈልጋ  ባለትዳር እና የልጆች አባት መሆኑን ስታውቅ በልቧ ወዳው ቀረች። ውጪ ሀገር ለትምህርት ደርሳ ስትመለስ በ1967ቱ የመንግሥት ለውጥ ከቤተሰቦቿ ጋር ለሰባት ዓመታት ታስራለች። ልጅቱ የራስ መስፍን ስለሽ ልጅ ሒሩት ነበረች። ራስ መስፍን ስለሺ በደርግ ከተረሸኑት ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው። ጥላሁን ሕዝብ ለሕዝብ ጉዞ ሲያደርግ የቤቱን ቁልፍ ሰጥቷት ሄደ። በ1980 ዓ.ም ሒሩት መስፍን እና ጥላሁን ጋብቻ ፈፀሙ። ቀድሞም ታፈቅረው ስለነበር ፍቅራቸው መልካም ነበር። ይሁን እንጂ ይህም ትዳር ፈተናዎች ነበሩበት።

ጥላሁን መርሰዲስ መኪና በተሸለመበት ሰሞን ጋብቻው በመፈጸሙ ሒሩት  ገንዘብ ፈልጋ እንደ መጣች ተደርጎ ይናፈስ ጀመር። ሌሎች ቅናተኞች ትዳራቸውን ለመበጥበጥ ብዙ የሚታገሉበት ዘመን ነበር። ሒሩት ከጥላሁን ናኦሚ የምትባል ሴት ልጅ ወለደች።

በ1982 ጥላሁን ለመስክ ሥራ በማለት ለቀናት ከቤት መጥፋት ጀመረ። ለካ ጥላሁን እየተደበቀ ወይዘሮ ቀለሟ ማሞ የምትባል ሴት ጋ  መኪናውን እያቆመ ይሄድ ነበር። ጥላሁን ቀለሟ ጋር ወዳጅነት መስርቷል። ሒሩት ደግሞ ሁለተኛ ልጇን ርጉዝ ነበረች። ናታን ጥላሁንም የሒሩት ልጅ ነው። ቀለሟ ጋር አሁንም መኖር ጀመረ። ጥላሁን አንድ ቀን ጥሎኝ ይሄዳል ስትል ቀለሟ  ትናገርም ነበር። ጥላሁን ከቀለሟ ቃልኪዳን የምትባል ልጅ ወልዷል። ጥላሁን የገዛውን ቤትም አልሰጥህም አለችው፣ መኪናውንም ጭምር ትቶ ሄደ።

ጥላሁን የድሮ ዘፈኖቹን ድጋሚ በመጫዎት በአሜሪካ በሲዲ ለማስቀረጽ ያቀናል። በዚያም ቆይታው ሮማን የምትባል ሴት ተዋወቀ። ነሐሴ 1984 ዓ.ም ጥላሁን እና ሮማን ለአንድ ሳምንት  በለንደን ተገናኝተው ጊዜ አሳለፉ። ሚያዝያ ወር 1985 የመጀመሪያ ልጇን ሄለንን ተገላገለች። ሁለተኛ ልጇንም ዮናታን ጥላሁንን ወለደች።

ጥላሁን ጉሮሮው ላይ በደረሰበት አደጋ ወደ ጀርመን ሄዶ  ሲታከም አንዲት የበረራ አስተናጅጋጅ  ይተዋወቃል። ይህቺ ሴት ማርታ ሲማቶስ ትባላለች። በሒልተን ሆቴልም አብረው ኖረዋል። ማርታ ስድስት ወር ጀርመን ስድስት ወር አዲስ አበባ በመዘዋወር ነው የምትሰራው። ሸህ አላሙዲን ቤት ገዝተውላቸው ይኖሩ ነበር። በዚህ ወቅት ሮማን ውጪ ነበረች። ማርታም የሦስት ወር ርጉዝ ነበረች። ሮማን ከአሜሪካ መጥታ ጥላሁን ጋር መኖር ጀመረች።

እሱ ደግሞ ወደ አሜሪካ ሄዶ ማርታ ጋር እንደሚኖር ለሮማን ነገራት። በ1992 ዓ.ም ጥላሁን አሜሪካ እያለ በተለያዩ ግዛቶች ኮንሰርት   ለማቅረብ ኮንትራት ተፈራረሟል። ማርታም ከጥላሁን ከወለደቻት ልጇ ናኦሚ ጋር ትኖር ነበር። በዚህም ማርታ  ጥላሁን የስኳር በሽታን ተከትሎ የሚመጣ የጋንግሪን በሽታ እንዳያጠቃው በሐኪሞች አስመክራዋለች። እግርህ እንዳይቆረጥ ተጠንቀቅ ብለውም ነገሩት። ትንባሆ እንዳያጨስ አስጠነቀቁት። በቄስ ሲጃራ እንዳያጨስም አስገዘተችው። ጥላሁን ባድመ በሄደበት ወቅት ማርታ  ከጥላሁን ልጅ ወለደች፣ ስሟም ቪክቶሪያ ይባላል። ማርታ ጥላሁንን ድክመቱን አውቃ እለውጠዋለሁ፣ አግዘዋለሁ ያለች ሴት ናት። ጠንካራ ስነ ልቦና ያላት ሴትም ናት። የጥላሁን ትልልቅ ልጆቹ ሳይቀሩ ማርታ ጋር ከሆነ በኋላ ጤናው መስተካከሉን መስክረዋል። ግን ጥላሁን አሁንም ወደ ድሮው መስመር ሾልኮ ተመለሰ። ማርታ ጤናውን እንደሚጎዳው በማመን ተው ትለው ነበር። አንድ ቀን ልብሱን ጥቅልሎ “ሲጃራ አታጭስ” የሚለውን የማርታን ንግግር ላለመስማት ወስኖ ከቤት ጥሎ ወጣ። በዚህ ሳቢያ 1997 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ እግሩን ተቆረጠ። እስከ ሞተበት  ሚያዝያ 2001 ዓ.ም ድረስ ሮማን ጋር ኖሮ አለፈ። ጥላሁን በትዳር እና በፍቅር 16 ልጆች ወልዷል። ከሀገር ፍቅሯ አርቲስት አልማዝ ቢሆን ጽዮን የምትባል ልጅ ወልዷል። ጊዜውም በ1950 ዎቹ አጋማሽ ነበር።

ይህን ታሪክ የሚያነብ ሰው በጥላሁን ይፈርድ ይሆናል፤ ነገር ግን ጥላሁን በቤተሰቡ በልጅነት ዕድሜው የገጠመው የቤተሰብ መፍረስ እና መበታተን እስከ መቃብር ሲከተለው ነው የኖረው። ጥላሁን ለራሱ የማያውቅ፣ ያዝ ለቀቅ የሚያደርግ፣ መወሰን የማይችል፣ ስነልቦናው ደካማ ፣ በተቀደደለት ቦይ የሚፈስ ነው በማለት የሚያውቁት ይናገራሉ። የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን እንኳን አያውቅም ነበር ይባላል። ይህንን ስነልቦናዊ ስብራት የፈጠረበት ደግሞ ልጅነቱ ላይ የተቋጠረበት ውስብስብ ታሪክ ነው በማለት ዘከሪያ መሐመድ ልንፈርድበት እና ልንሳለቅበት አይገባም ይላል። ጥላሁን ዝነኛ በመሆኑ ታሪኩ ተጻፈ እንጂ ይህ በብዙዎች ቤት ያለ መቃወስ ነው። ጥላሁን ይህንን ሁሉ ችግር ችሎ ያንን ያህል  ሙዚቃ ለአድማጭ እንዴት አደረሰ? “ከሙዚቃ ለሰከንድ አልለይም” የሚለው ውስጡ ያለው ጠባሳ እንዳይሰማው ይሆን? አበቃሁ።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here