ጥልን በእግር ኳስ ያከሸፈዉ

0
167
ኮትዲቯር በምዕራቡ የአህጉራችን ክፍል የምትገኝ ሀገር ናት። ሀገሪቱ ልክ እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በአንድ ወቅት በእርስ በእርስ ጦርነት ትታመስ የነበረች ሀገር መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ሕዝቦቿ በጎሳ ተከፋፍለው እርስ በእርሳቸው ተፋጅተዋል። የመጀመሪያው ዙር ጦርነት ከ2002 እስከ 2007 እ.አ.አ ነበር። በኋላ ደግሞ ከ2009 እስከ 2011 እ.አ.አ የኮትዲቯር ምድር እና ሕዝቦቿ አለመረጋጋት ውስጥ ገብተው እንደነበረው በታሪክ መዝገብ ተጽፏል። የጦርነቱ መነሻም በሰሜኑ እና በደቡቡ ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦች የብሄራዊ የማንነት ልዩነቶች እንደነበሩ ይነገራል። በዚህ ምክንያትም ኮትዲቯር ለዜጎቿ ምድራዊ ሲኦል ሆና ስትረገም እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።
በሺህ የሚቆጠሩት ሙተዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ከሞት ለማምለጥ ሽሽት የጀመሩትም የባህር እና የአውሬ ሲሳይ ሆነዋል። በመጨረሻ ግን ከደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል የተገኝው ዲዲየር የቭስ ድሮግባ ተፋላሚዎቹን እጅ ለእጅ አያይዞ ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ አድርጓል።
የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በፕሪሚየር ሊጉም ከታዩ የተዋጣላቸው ጥቂት ግብ አነፍናፊዎች ውስጥ ስሙ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል። ድሮግባ ከአቢጃን ተነስቶ በፈረንሳይ ማርሴ ጎልብቶ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቸልሲ ያንጸባረቀ ተጫዋች ነው።
በስታንፎርድ ብሪጅ በቆየባቸው አጠቃላይ ዘጠኝ ዓመታት የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የፕሪሚየር ሊግ ፣ የኢሮፓ ሊግ እና ሌሎችንም ዋንጫዎችን አሳክቷል። ይህ የቀድሞ እግር ኳሰኛ በሜዳ ውስጥ ከሠራው ገድል ባለፈ በሀገሩ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ እና ሰላም እንዲሰፍን ያስቻለ ጀግና ስፖርተኛ ነው። በ2002 እ.አ.አ በገዥው መንግስት እና በታጠቁ ኃይሎች ያገረሸው ጦርነት ምህዳሩ ስፈቶ በሰሜን እና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ሆኗል። እ.አ.አ በ2002 መስከረም ወር በተፈጠረው ግጭት በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። ከዚህ ጥቃት ለመሸሽ ከኮትዲቯር የተሰደደው የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ሰባስቲያን ግናሆር እነዚያን ጊዜያት ሲያስታውስ “አሳዛኝ ነበር” ይላል።
‘‘በየ ማለዳው ለእህቴ ስደውል ከቤት ውጪ ያለውን የጦር መሳሪያ ድምጽ እሰማ ነበር። ሁሉም ቤተሰቦቼ ለአራት ቀናት አልጋ ስር ተደብቀው አሳልፈዋል፣ የወጡትም ምግብ ፍለጋ ነበር። ሁሌም ሲነጋ የሚያስጨንቀኝ ነገር ቢኖር ቤተሰቦቼ ደህና አድረው ይሆን? የሚለው ብቻ ነበር” ሲል ሰባስቴያን ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
አንዴ ረገብ ሲል ሌላ ጊዜ ድጋሚ እያገረሸ ሕዝቦቿን በሰቀቀን የጨረሰው የእርስ በእርስ ጦርነቱ፣ በ2004 እ.አ.አ አበቃ ቢባልም ከአንድ ዓመት በኋላ ድጋሚ አገርሽቶ ውጥረቱ ተባብሷል። በዚህ ሳቢያ የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዕጣ ፋንታም የጨለመ ይመስላል። ሕዝቦቿ ከተስፋ ብርሐን ወደ ድቅድቁ ጨለማ እየተጓዙ መሆኑ ገብቷቸው ግራ ተጋብተዋል።
በዚህ ጭንቅ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ግን የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን በ2006 እ.አ.አ ጀርመን ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን እያከናወነ መሆኑ ብዙዎቹን አስገርሟል። ዝሆኖቹ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍም ቆርጠው ተነስተዋል።
ምድብ ሦስት ላይም ከካሜሮን ፣ ከግብጽ ፣ ከሊቢያ ፣ ከሱዳን እና ከቤኒን ተደልድለዋል። በምድቡ ከካሜሮን ብሄራዊ ቡድን በአንድ ነጥብ አንሰው በ19 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የዓለም ዋንጫ ትኬቱን ለመቁረጥም በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ የግድ ሱዳንን ማሸነፍ ሲኖርበት የካሜሮንን ነጥብ መጣልንም ይጠብቃል። አሊያ ግን ልፋታቸው ክንቱ ይሆናል። እ.አ.አ በጥቅምት ወር 2005 ወደ ሱዳን ተጉዞ በኦምዱርማን አል ሜሪክ ስቴዲየም ሱዳንን የገጠመው የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ተሳክቶለት 3ለ1 ያሸንፋል። ዕድል ያልቀናቸው ካሜሮናውያን ግን በሜዳቸው ከግብጽ ጋር አንድ አቻ መለያየታቸው ተሰማ። ይህ ዜናም በመላው ኮትዲቯራውያን ዘንድ ደስታ እና ፌሽታ ሆነ።
ቀድመው ለሕዝባቸው ይህን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋልና ዝሆኖቹ ቃላቸውን አከበሩ። ጨዋታው እንደ ተጠናቀቀ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሳይባክኑ የዝሆኑ ስብስብ በዲዲየር ድሮግባ መሪነት በቀጥታ ወደ መልበሻ ቤት በማምራት ካሜራ ፊት ተሰባሰበ። ተጫዋቾቹ ተንበርክከው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ቆሞ እርቀ ሰላም እንዲወርድ በመልዕክታቸው ተፋላሚ ኃይሎችን መማጸን ጀመሩ። መነጋገሪያውን (ማይኩን) የያዘው ዲዲየር ድሮግባም እንዲህ አለ።
“የኮትዲቯር ወንዶች እና ሴቶች ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅ፣ ከምዕራብ እና ከመሐል ሀገር ያላችሁ ሁሉም ኮትዲቯራውያን በአንድነት መኖር እንደሚችሉ ዛሬ አረጋግጠናል፤ ይሄው ለዓለም ዋንጫው አለፈናል። ይህ በዓልም ሕዝባችንን አንድ እንደሚያደርግ ቃል ገብተንላችሁ ነበር፤ ዛሬ ተንበርክከን እንማጽናችኋለን። በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ሃብት ያላት አንድ ሀገር ወደ ጦርነት መግባት የለባትም። እባካችሁ መሳሪያችሁን አውርዳችሁ ምርጫ አድርጉ በማለት ድሮግባ አሳስቧል። ሌሎች ተጫዋቾችም “አሁን መዝናናት እና መደሰት እንፈልጋለን፡፡
ስለዚህ መሳሪያችሁን አስቀምጡ” የሚል መልዕክት አስተላለፉ። ከዚህ አስደናቂ የመልዕክት ትዕይንት በኋላ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ምሽቱ በጦር መሳሪያ እና በጩኸት ድምጽ ሲናጥ አምሽቷል፣ የጦር መሳሪያው ድምጽ የደስታ መግለጫ ሲሆን ጭኸቱም የፌሽታ እንደነበር የዋና ከተማዋ አቢጃን ነዋሪ የሆነው ሀሰን ኦማር ተናግሯል። ቀኑን ሲያስታውስም “ያ ቀን ሁላችንም ሀገራችን የተከፋፈለች መሆኗን የረሳንበት ቀን ነው” ብሏል። በዚያ ምሽት ትንፋሽን የሚያስውጡ፣ ልብን የሚያሞቁ፣ ድራማዊ ክስተቶች የተፈጠረው በእግር ኳስ ሜዳ አልነበረም። ይልቁንም በአል ሜሪክ ስቴዲየም ጠባቡ የመልበሻ ክፍል ውስጥ ነበር።
ምሽቱን ያደመቀውም ከሱዳን ያውንዴ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ማይል ርቆ ያስተጋባው በድሮግባ የሚመራው የተለየው የተማጽኖ ቃል ነው። የብሄራዊ ቡድኑን የተማጽኖ ቃል የሰሙት ተፋላሚ ኃይሎችም ሳይውሉ ሳያድሩ የመሳሪያቸውን አፈሙዝ ወደ ሰገባው በማስገባት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ችግራቸውን በንግግር እና በድርድር በመፍታት ተስማምተዋል።
እ.አ.አ በ2006 ኮትዲቯር በጀርመኑ የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ድግስ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፈች። በዚህ ዓመትም ኮከቧ ዲዲየር ድሮግባ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ክብርን ተጎናጸፈ። ከዚህ ክብር በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ ያቀናው ድሮግባ ሰኔ 3 2007 እ.አ.አ በኮትዲቯር እና ማዳጋስካር መካከል የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በአቢጃን እንደማይደረግ ይፋ አደረገ።
ይልቁንም ሁለቱን ጥል ሕዝቦች የሰሜኑን እና የደቡቡን ክፍል ለማቀራረብ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኝው እና የአማጽያኑ ማዕከል በሆነችው ቡዋኬ ከተማ ጨዋታው እንደሚደረግ ድሮግባ ገለፀ። ጉዳዩ በሀገሪቱ ፕሬዝደንት ፈቃድ አግኝቷል ወይ የሚለው ጥያቄ በወቅቱ መነጋገሪያ ቢሆንም አስገራሚው ነገር ይህ ጉዳይ እስካሁንም አልታወቀም። ቀኑ ደረሶ የኮትዲቯር እና የማዳጋስካር ጨዋታ በቡዋኬ ከተማ ሲከናወን ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በመጣው ተመልካች ስቴዲየሙ በደስታ መናጥ ጀመረ። ስቴዲያም መግባት ያልቻለው ደጋፊም በመኪናዎች አናት ላይ ተቀምጦ ደስታውን ይገልጻል።
በሁለቱ የስቴዲየም ጫፍ የተቀመጡት የመንግስት እና የአማጺያን ወታደሮች የጋራ ዝማሬ ያስተጋባል። እጅግ የተለየ ድባብም ፈጥሯል። ይህ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ተስፋ እና የመኖር ጉጉትን ፈጥሯል። ትዕይንቱን አጢኖ ለተመለከተው የእግር ኳስ ጨዋታ ሳይሆን የተበታተነው ሕዝብ አንድ ሲሆን እና ሲዋህድ ነበር የሚያሳየው።
ኮትዲቯር ይህንን ጨዋታ 5ለ0 ስታሸንፍ የመጨረሻውን ግብ ያስቆጠረው የሰላም ምልክቱ ድሮግባ ነበር። ይህቺ ግብ ከመረብ ስትገናኝም በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ሲዋደቁ የነበሩትን እና በስቴዲየሙ በተለያየ ቦታ የተቀመጡትን ኃይሎች ያስተቃቀፈች እንደነበረች ቅጽበቱን አስታውሶ ሀሰን ኦማር ያስረዳል። ምንም እንኳ ከአምስት ዓመታት በኋላ በምርጫ ምክንያት በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገሪቱ ድጋሚ መከፋፈሎች እና ልዩነቶች በዝተው ኮትዲቯር የደም ምድር ብትሆንም ከሁለት ዓመታት በኋላ ሰላም ወርዷል። ስፖርት የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት መሆኑን የተረዳው ሰው እግር ኳስን ይዞ ሀገሩን ከአስከፊ ችግር እና መከራ ታድጓል።
እኛም እንደ ድሮግባ ያለ ልበ ሙሉ ፣ ደፍሮ ይበቃል የሚል ስፖርተኛ ድንገት ከመኝታችን ስንነቃ እንዲሰጠን እንመኛለን፤ ፀሎትም እናደርጋለን።
ቢቢሲ ሰፖርትን፣ ፌስ ቱ ፌስ አፍሪካን እና አልጀዚራን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here