ጥልን ያከሸፉ የኦሎምፒክ ክስተቶች

0
147

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን የመስፋፋት እና የቅኝ ግዛት አባዜ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካዊ ኢፍትሐዊነት ምድራችንን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በጦርነት አዙሪት እንድትናወጥ አድርጓት ነበር ይላል የናሽናል ጆግራፊ መረጃ። ይህንን ጥቁር ታሪክ ከምድራችን ለመሰረዝ፣ በፕላኔታችን ስላም እና ልማት ለማምጣት ኦሎምፒክን እንደ መሳሪያ መጠቀም የተጀመረም በዚያ ወቅት ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 70ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ሰላምን በማስፈን የተሻለ ዓለምን መገንባት በኦሎምፒክ ስፖርት ሀሳብ ቀርቧል። ሀሳቡ የመነጨውም በፈረንሳያዊው ባሮን ፔየር ዲ ኩበርቲን አማካኝነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ሰው በወቅቱ በአውሮፓ እየጨመረ የመጣውን የብሄርተኝነት ማዕበል በኦሎምፒክ ለመታገል በማሰብ ነው።

በወቅቱ የነጮች የዘር የበላይነት እና ሴቶች በሕዝባዊ ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳይሳተፉ የሚከለክሉ አክራሪ ቅኝ ገዥዎች እንደነበሩ ይነገራል። ታዲያ ኦሎምክ ለሰላም የሚለው መርህ አሸንፎ በ1928 እ.አ.አ አምስተርዳም በተደረገው ዘጠነኛው ኦሎምፒያድ ሴቶች በኦሎምፒኩ እንዲሳተፉ ፈቅዷል። በቆዳ ቀለም ልዩነት የሚደርሰው አድሏዊ አሰራርም እንዲቀር ተደርጓል።

በየ አራት ዓመቱ በሚደረገው የኦሎምፒክ መድረክ ሀገራት ባህል እና እሴቶቻቸውን ያስተዋውቁበታል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በዘመናዊ መልክ መጀመራቸውን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያስነብቡናል። የኦሎምፒክ መሰረት የሆኑትን አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገትን ማሳደግ፣ የተሻለ ሰላም የሰፈነባት ዓለምን መገንባት እና የአብሮነት መንፈስን ማሳደግ የኦሎምፒክ ጽንሰ ሀሳቦች ናቸው።

ዓላማውም ስፖርትን ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት በማስተዋወቅ ሰላማዊ ማህበረሰብ እና ዜጋ መፍጠር ነው። ይህ የአብሮነት የወንድማማችነት እና የሰላም ጽንሰ ሀሳብም ጥልን አክሽፏል፤ የተለያዩትን አንድ አድርጓል፤ የተጣሉትን አስታርቆ አስተቃቅፏል። የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከሌላው የስፖርት ሁነት በተሻለ የሰው ልጆች ስለ ሰላም የሚሰብኩበት፣ ጥላቻን እና መድሎንም የሚኮንኑበት የስፖርት ሁነት ነው።

በዚህ የበኵር ዕትማችን በኦሎምፒክ ታሪክ ጥልን ያከሸፉ፣ ኢፍትሐዊነትን እና መድሎን የተቃወሙ፣ ዘረኝነትን፣ ብሄርተኝነትም በአደባባይ ያወገዙ እና የሰው ልጆችን ሰላም የሰበኩ ሁነቶችን እንዳስሳለን።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የፖለቲካ ርዕዮት ዓለምን ለማስተዋወቅ እና ለማስፋፋት እንደ ትልቅ መድረክ አገልግሏል። በተለይ በ1936ቱ 11ኛው የበርሊን ኦሎምፒያድ የጀርመኑ ናዚ ያንን ክፉ ርዕዮታለሙን አቀንቅኖበታል። አትሌቶችም ቢሆኑ የኦሎምፒክ መድረክን ተጠቅመው የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስተዋወቅ ሞክረዋል።

ታዲያ በዚህ ወቅትም ነበር ኦሎምፒክ ለሰላም የሚለው መርህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው፡፡ በወቅቱ ናዚ አዶልፍ ሂትለር አይሁዶችን በማሳደድ ድፍን የአውሮፓ ምድርን ያስጨነቀበት ነበር። ዘረኝነት በደም ስራቸው ሰርፆ ያሰከራቸው ጀርመናውያንም ራሳቸውን የተለዩ የሰው ልጅ ፍጡር አድርገው የሚመለከቱበት ወቅት ነበር።

የጀርመኗ ከተማ በርሊን አዶልፍ ሂትለር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ነበር ኦሎምፒክን እንድታስተናግድ የተመረጠችው። በዚህ ኦሎምፒያድ የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገውን ልዩነት እስከ ወዲያኛው የቀየረ ሁነት የተፈጠረበት እንደነበር መረጃው ያሳያል።

አሜሪካዊው የአጭር ርቀት እና የርዝመት ዝላይ ጀሲ ኦውንስ እና ጀርመናዊው ሉዝ ሎንግ በእርዝመት ዝላይ ውድድር እየተፎካከሩ ነው። አሜሪካዊው ጀሲ ኦውንስ  ምንም እንኳ በመም ውድድሮች ሦስት ሜዳሊያዎችን ቢያሳካም በርዝመት ዝላይ ግን የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም። በፍጻሜው በተደጋጋሚ ቢዘልም ከጀርመናዊው ሉዝ ሎንግ የተሻለ መዝለል አልቻለም።

እናም አሁን አንድ እድል ብቻ ይቀረዋል። በዚህ ወቅት ነበር ጀርመናዊው ሉዝ ሎንግ፤ ለጥቁር አሜሪካዊው ጀሲ ኦውንስ እንዴት መዝለል እንዳለበት ምክር እና አስተያየት ሲሰጠው የታየው። አሜሪካዊው ጀሲ ኦውንስም ከጀርመናዊው ተፎካካሪው የተለገሰውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የመጨረሻውን ዕድል ተጠቅሟል፤ 26 ሜትር ከአምስት ሴንቲሜትር በመዝለል። በዚህም ቀደም ብሎ ጀርመናዊው ወጣት ሉዝ ሎንግ  ከዘለለው ጋር እኩል መሆን ችሏል። በመጨረሻም አሜሪካዊው ጀሲ ኦውንስ 26 ሜትር ከ44 ሴንቲ ሜትር በመዝለል የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል።

ከዚህ አስገራሚ ሁነት በኋላ ጀርመናውያንን ጨምሮ አምባገነኑ አዶልፍ ሂትለር በሎንግ መልካም ሥራ መበሳጨታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። ጀርመናዊው ሉዝ ሎንግ ግን መተሳሰብን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እና እኩልነትን የሚሰብክ ጠንካራ መልዕክት በመልካም ሥራው አስተላልፏል። በውድድር መድረክ እና በህይወት ዘመናቸው ይህን የሚያደርጉ ጥቂት መሆናቸውን በመግለጽ መገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል። ሁለቱ ስፖርተኞች ሜዳ ውስጥ ተፎካካሪ ከመሆናቸውም ባለፈ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ወዳጆች ሆነው ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል።

ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ ከ1964 እስከ 1988 ባሉት ጊዜያት በኦሎምፒክ መድረክ አልተሳተፈችም። ሀገሪቱ በወቅቱ በአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ ስለነበረች በውድድሮች እንዳትካፈል ተከልክላ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ኔልሰን ማንዴላ በ1992 እ.አ.አ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በስፖርቱ ዘርፍም የነበረውን የነጮችን የበላይነት በመስበር ጥቁሮቹ እንዲካፈሉ አድርጓል። ጥቁሮች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ብቻ ሳይሆን በስፖርት ተጠቃሚ መሆን የጀመሩበት ጊዜ ነበር የባርሴሎናው ኦሎምፒክ።

እ.አ.አ በ1945 ኮሪያ ከጃፓን ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበት ጊዜ ነው። የኮሪያ ልሳነ ምድር ከጃፓን ቅኝ ግዛት ከተላቀቀ በኋላ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በሚል ለሁለት ተከፍሏል። ከዚያን ጊዜ ወዲህም ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በጥርጣሬ ሲተያዩ ድፍን 80 ዓመታት ሊቆጠር ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ተደርገው ንጹሀን አልቀዋል።

በፈረንጆች ሚሊኒየም በአወስትራሊያ ሲዲኒ በተደረገው 27ኛው ኦሎምፒያድ ግን የዓለምን ትኩረት የሳበ ክስተት ተፈጥሯል። ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ተቀራርበው በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ አንድነታቸውን የሚያሳይ “ኮሪያ” የሚል ነጭ ሰንደቅ አላማ በመያዝ ታይተዋል። የሰላም አየር መተንፈስ የናፈቃቸው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በእንባ በመታጀብ አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል። ለዓመታት የተጠራቀመ ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል በኦሎምፒክ መድረክ ከሽፏል። የእርቅ መንገድም ከፍቷል። አሁን ላይ ግን ሁለቱ ሀገራት ድጋሚ የተካረረ ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

የ2004ቱ የአቴንስ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ለተተኪው አልጋ ወራሹ ዙፋኑን ያስረከበበት በመሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያስታውሱታል። ቀሪው ዓለም ደግሞ ከዚህ ደምን ከሚያሞቅ ፉክክር በተጨማሪ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ በኦሎምፒክ የተሳተፉበት ወቅት በመሆኑ ጭምር ያስታውሰዋል። ሁለቱ ሀገራት ከ2003 እስከ 2011 እ.አ.አ ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ላይ እንደነበሩ ታሪክ ያወሳል። አፍጋኒስታውያን እና ኢራቃውያን ሰፖርተኞች ከአስፈሪው የጦርነት ድባብ ወጥተው ሀገራቸውን ወክለው ወደ ግሪክ ማቅናታቸው አጃኢብ አሰኝቷል፡፡

በአቴንስ ኦሎምፒክ አፍጋኒስታን ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ስፖርተኞችን ያሳተፈችበት ወቅት እንደነበረ አይዘነጋም። በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ኮፊ አናን ለሰላም የስፖርትን ኃይል አወድሰው፤ ሌሎችም ከእነርሱ መማር እንዳለባቸው በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ባሉት ዓመታትም እስከ 2021 እ.አ.አ ጊዜ ድረስ አልፎ አልፎ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ አይዘነጋም። እ.አ.አ በቻይና ቤጂንግ በተደረገው 29ኛው ኦሎምፒያድ ዓለም የቀነኒሳን እና የጥሩነሽ ዲባባን ብቃት የተመለከተበት ወቅት ነው። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትር ርቀቶች ድርብ ድል ያስመዘገቡበት በመሆኑ አጋጣሚውን ለየት ያደርገዋል።

የቤጂንግ ኦሎምፒክ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ሁለቱ ጎረቤታሞቹ ሀገራት ሩሲያ እና ጆርጂያ ቅልጥ ያለ ጦርነት ውስጥ ነበሩ። 16 ቀናት በቆየው ጦርነት በርካታ ንጹሀን ሞተዋል፤ በሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል። በወቅቱ ከፖለቲካው ይልቅ የስፖርቱ መንፈስ የጠነከረ በመሆኑ የሩሲያ እና የጆርጂያ ስፖርተኞች በቤጂንጉ ድግስ እየተካፈሉ ነበር።

በአስር ሜትር የተኩስ ውድድር ሩሲያዊቷ ናታሊያ ፓደሪና እና ጆርጂያዊቷ ኒና ሳሉክቫዜ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል። በዚያች ቅጽበት ምንም እንኳ የሁለቱ ስፖርኞች ሀገራት ጦርነት ውስጥ ቢሆኑም በሜዳሊያ ስነ ስርዓቱ ወቅት እነርሱ በመተቃቃፍ ሀገራቸው እርቅ እንዲያወርዱ ተማጽነዋል፤ ሰብከዋል። እኛም በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አተሌቶቻችን በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ይቆም ዘንድ በዓለም አደባባይ እንዲጠይቁ ምኞታችን ነው፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here