ጥረቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥል፤ ለውጤትም እንብቃ!

0
88

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ  ይዞ ነበር፡፡ ይህን  ዕቅድ ለማሳካትም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 በሦሥት ዙሮች የተማሪ ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ በዚህም ወደ ሦሥት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ከተመዘገቡት ሦሥት ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉት ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ  ባካሄደው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እንደተገለጸው ደግሞ በክልሉ አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በዋነኛነት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ነው፡፡

ይህም ሆኖ የተመዘገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ፣ ተመዝግበው ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ይገኛሉ፡፡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ በጦርነቱ የተጎዱትን መጠገን፣ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል ከተደረጉት ጥረቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተደርገው የተመዘገቡትን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ባይቻልም ወደ ትምህርት ቤት የመጡትን ውጤታማ በማድረግ በተማሪ ምዝገባ ማሳካት ያልተቻለውን ውጤት ማካካስ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ሲማሩ የከረሙ ተማሪዎችን በማብቃት ሁሉንም ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ማሸጋገር፣ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ውጤት ያመጡ ዘንድ መሥራት ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

በተጨማሪም የእያንዳንዱን የትምህርት ይዘት በአግባቡ ለመሸፈን እንዲሁም ያልተሸፈኑት በወቅቱ እንዲሸፈኑ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ የማጠናከሪያ ትምህርትም በተጠናከረ መንገድ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ ያለፉ ይዘቶችን መከለስ፣ ያለፉ ዓመታትን የፈተና ጥያቄዎች መሥራት፣ መምህራንም ለተማሪዎቻቸው ጥያቄዎችን እያዘጋጁ በመሥጠት ይበልጥ እንዲዘጋጁ እያደረጉ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የሳምንቱን የእረፍት ቀናት እና የምሳ ሰዓትን ጨምሮ የአዳር ጥናት  እያካሄዱ ተማሪዎቻቸውን በሚገባው ልክ እያበቁ ይገኛሉ፡፡ መጻሕፍት ቤቶችን በአጋዥ መጻሕፍት ማሟላት እና የመማሪያ መጻሕፍትን አንድ ለአንድ ተደራሽ ማድረግ ላይም ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ ለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናው ከስንተኛ ክፍል ጀምሮ እንደሚወጣ የማሳወቅ ሥራም ተከናውኗል፡፡ ሥነ ልቦና ግንባታም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች በእስካሁን ጉዟቸው ስጋት ውስጥ ናቸው፤ የሚሰሙት እና የሚያዩት የተረጋጋ ሥነ ልቦና እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ስለሆነም በትምህርታቸው እና  በሚወስዱት ፈተና ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሥነ ልቦና ግንባታ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል፡፡

ባጠቃላይ በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በዚሁ ከቀጠለ ነጋችን የጨለመ እንደሚሆን  መገመት አይከብድም፤ በተለይም በአማራ ክልል፡፡ ችግሩ ከአማራ ክልልም አልፎ ሀገር አቀፍ ጫና ማሳደሩን መተንበይ  ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዜጎች ባለመማራቸው የተነሳ ባገራዊ ሀብት በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ፣ ቀስ በቀስም ሀገራችንን ወደ አለመረጋጋት የሚመራ በቀላሉ የማይታይ ችግር ነው፡፡

ስለሆነም ነጋችን እንዳይጨልም በምዝገባ ያልተሳካውን የዕቅድ ክንውን እየተማሩ ባሉ ተማሪዎች ውጤት ለማካካስ የተጀመሩ ጥረቶች  ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ የትምህርት መሠረቱ ማህበረሰቡ ነው፡፡ ትምህርት የማህበረሰብን ድጋፍ ሲያገኝ ሽፋኑ እንደሚያድግ፣ ጥራቱም እየተሻሻለ ሄዶ ችግር ፈቺ ትውልድ እንደሚፈጥር፣ ይህም ውጤት በተራው ለሀገራዊ ሰላም እና መግባባት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም የተጀማመሩ ጥረቶቻችን ማህበረሰቡን   በማሳተፍ አጠናክረን ልንቀጥልና ለውጤት ልንበቃ ይገባናል፡፡

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here