ጥቁሩ ባለቅኔ  ወሌ ሶየንካ

0
93

       ከናይጀሪያ ምድር የበቀለ፤ አፍሪካ የምትኮራበት ድንቅ የስነ ፅሁፍ ሰው ነው። አቢኦኩታ በተሰኘች የናይጀሪያ ከተማ እአአ ሐምሌ 13 ቀን 1934 ዓ.ም የተወለደው የተውኔት ፀሀፊ፣ ገጣሚ እና  ሐያሲ ነው፣ አኪንዋንዴ ኦሉወሌ ባባቱንዴ ሶየንካ  /በስፋት የሚታወቅበት ወሌ ሶየንካ/ በተሰኘ ስሙ ነው። ለስነ ፅሁፍ፣ ለቲያትር እንዲሁም በማህበረሰብ ትችት ላደረጋቸው አስተዋፅኦዎቹ ከአፍሪካ እጅግ የተከበሩ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ ይካተታል።

እድገቱ በባህል በታነፀ አካባቢ ሲሆን አባቱ የአንድ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር፤ እናቱ ደግሞ በንግድ እንቅስቃሴው ዘርፍ ወሳኝ የሚባሉ ነበሩ። ይህ አስተዳደጉ ለዮሩባ ትውፊታዊ ባህል እና ለቅኝ ገዥው የእንግሊዝ የትምህርት ስርዓት ቅርበቱን እንዲያገኝ አድርጎታል። በመሆኑም በናይጀሪያ ኢባዳን ውስጥ  በመንግሥት ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን፤ በእንግሊዝ በሊድስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በናይጀሪያ እና በእንግሊዝ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተምሯል።

የስነ ፅሁፍ ስራው ብዕሩን ተጠቅመው ለማህበረሰባቸው የተሻለ ሕይወት፣ ለእድገት፣ ለነፃነት እና ለእኩልነት ሰርቷል። ናይጀሪያ በወሳኝ የታሪኳ ወቅት ካፈራቻቸው ቱባ ፀሀፍት ውስጥ አንዱ የሆነው ወሌ ሶየንካ የስንፅሁፍ የሕይወት ጉዞው የተለየ በሆነ ችሎታው የተሞላ ነው። ናይጀሪያ በታላቅ ለውጥ እና በነውጥ ውስጥ ባለፈችባቸው 1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ወቅት ነበር ሶየንካ ወሳኝ የሀገሪቱ ሰው ሆኖ ብቅ ያለው። ቀደም ካሉት ስራዎቹ መካከል ለአብነት “በ1960 ያበረከተው “ዘ ዳንስ ኦፍ ፎረስትስ”፣ አንዱ ነው። በ1964 ዓ.ም “ዘ ማን ዳይድ” የተሰኘ የእስር ቤት ማስታወሻዎች የተመለከተው ስራው፣ እና “ማድሜን ኤንድ ስፔሻሊስትስ” በሚል ርእስ በ1963 ዓ.ም ያበረከታቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ። የስራዎቹ ጭብጦች በናይጀሪያ ማንነት ላይ የነበረውን ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት፣ የፖለቲካዊ ጭቆና እንዲሁም በናይጀሪያዊያን የማንነት ውስብስብ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።  ወሌ ሶየንካ በእጅጉ ከሚታወቅባቸው   አንዱ “ዴዝ ኤንድ ዘ ኪንግስ ሆርስ ማን” በሚል ርእስ በ1967 ዓ.ም ላይ ያበረከተው ስራው ነው። ይህ ስራው ከየሩባ ማህበረሰብ ስነቃል ወይም ወግ መነሳሳትን የወሰደ እና በትውፊት እና በዘመናዊነት መካከል ያለውን ግጭት የፈተሸበት ድንቅ ስራው መሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  ይህ ተውኔቱ ነበር ዓለማቀፍ እውቅናን ያስገኘለት።

ወሌ ሶየንካ የፖለቲካ አንቂ እንደነበር እና ለእስራትም የመዳረግ ክስተቶችን ያስተናገደ ስለመሆኑ ታሪኩ ያስረዳል። ሶየንካ ለማህበረሰብ ፍትህ ራሱን የሰጠ መሆኑ እና የወጣ የንግግር ችሎታው ወደ ፖለቲካ አንቂነት አቅጣጫ እንዳመራው የሕይወት ታሪኩ ይናገራል። በወቅቱ የነበሩት የናይጀሪያ ወታደራዊ አገዛዞችን እና የሚፈፅሟቸውን ሰብአዊ መብት ጥሰቶች በንግግር የሚነቅፍ እና የሚተች ሰው ነበር። በ1959 ዓ.ም የናይጀሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በተፋላሚ አንጃዎች መካከል በሽምግልና ልዩነታቸውን ለመፍታት ጥረቶችን አድርጓል። ይሁን እንጂ ይህ የአንቂነት ተሳትፎው ከተገናጣዩ የቢያፍራ አንጃ ጋር የሰላም ድርድር በመሞከር የሀሰት ውንጀላ አስከትሎ በቁጥጥር ስር እንዲውል እና እንዲታሰር አድርጎታል።

ወሌ ሶየንካ በ1978 ዓ.ም የስነፅሁፍ የኖቤል ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሎሬት የመባልን ክብር መደረብ የቻለ የናይጀሪያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ፈርጥ ነው። በስነፅሁፍ ላበረከታቸው ስኬቶቹ ፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር የነበረው መሰጠት እና በጨቋኝ መንግሥታት ላይ የነበረው ቆራጥ አቋም ለዓለም የኖቤል ሽልማት እውቅና አስገኝተውለታል። የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ሶየንካን ለባህል ሰፊ እይታው እና ለሰው ልጆች ጥቅም መረጋገጥ ለነበረው የማይታክት ሚና በዓለም መድረክ አወድሶለታል።

ወሌ ሶየንካ የሕይወት ዘመኑን በመፃፍ፣ ማሳተም እና ለማህበራዊ ፍትህ በመቆም የቀጠለ ብርቱ የስነፅሁፍ አርበኛ ነበር።  ስራዎቹ በአብዛኛው የናይጀሪያ ማህበረሰብን ችግሮች እና በሰፊው ደግሞ የሰው ልጆችን ልምምዶች የሚያንፀባርቁ ናቸው። የሶይንካ ትሩፋቶች ከስነፅሁፍ ስኬቶቹ በላይ የተሻገሩ ናቸው። ለዚህም ማሳያዎቹ ሶየንካ በባህል፣ በፖለቲካ እና በሰብአዊ መብቶች ላይ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ወይም ምክክሮች ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው እንደሆነ መቀጠሉ አንዱ ነው። ፅሁፎቹ በትውልዶች ፀሀፍት ዘንድ በአነሳሽነታቸው ቀጥለዋል። ይህን ታላቅ አፍሪካዊ ሰው በዘመን አይሽሬ ስራዎቹ አፍሪካ ስታወሳው ትኖራለች።

ናይጀሪያ እንደወሌ ሶየንካ ያሉ ጉምቱ የስነፅሁፍ አርበኞች ወላጅ ናት። በጥቁር ማንነት ላይ የነጩን ቅኝ አገዛዝ ሴራ በመተቸት ያጋለጠውን እና ለሀገሬው ባህል ትውፊት እና ወግ ዘብ በመቆም የሚታወቀውን ታላቁን ደራሲ ቸወንዋ አቼቤን ያፈራች ናት።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here