ጥቁሩ ተሟጋች

0
244

“ሁሉም ሰዎች እኩል ተፈጥረዋል፣ እና ማንም የማይቀማቸው ከፈጣሪያቸው የተሰጡ መብቶች አሏቸው፤ ከእነዚህም መካከል በሕይወት የመኖር ነፃነት እና ደስታን መሻት ናቸው” የሚል ጭብጥ የነበረው የአሜሪካ የነፃነት ሰነድ በ1768 ዓ.ም በስራ ላይ ዋለ። ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌ በአሜሪካ ባርነትን ማስቀረት አልቻለም።

በ1852 ዓ.ም ፀረ ባርነት አቋም የነበረው አብርሃም ሊንከን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኖ ሲመረጥ አዲስ የተስፋ ጎህ የቀደደ መሰለ።  ነገር ግን ጥቁሮቹ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ለተለያዩ በደል እና ለፍትሕ እጦት የተዳረጉበት ሌላ ፈተና ተጋረጠባቸው፤ ዘረኝነት።

በየዘመናቱ የጥቁሮቹን እኩልነት እና ፍትሕ ለማረጋገጥ ጥቁሮችን በማስተባበር እና በመምራት እንደሻማ ቀልጠው ብርቱ ትግል አድርገው ስማቸውን በወርቃማ ቀለም ከፃፉ ባለታሪኮች መካከል የማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹን ሕይወቱ እና የትግል ትሩፋቶቹን እንካችሁ እንላለን።

በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ውስጥ ጥር 6 ቀን 1920 ዓ.ም ላይ ተወለደ። ከአባቱ መጋቢ ማርቲን ሉተር ኪንግ ትልቁ እና ከእናቱ አልቤርታ ዊሊያምስ ኪንግ የተገኘው ትንሹ ማርቲን ሉተር ኪንግ የመጀመሪያ ስሙ ሚካኤል ኪንግ ነበር። መላ ቤተሰቡ ወደ አውሮፓ በተጓዙበት እና ጀርመንን በጎበኙበት በ1926 ዓ.ም አባቱ ለጀርመናዊው የፕሮቴስታንት መሪ ማርቲን ሉተር ክብር ሲሉ የሁለታቸውንም ስም የቀየሩት እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹ ተብሎ መጠራት እንደቀጠለ ታሪኩ ያሳያል። ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹ ዊሊ ክሪስቲን ኪንግ የተባለች ታላቅ እህት እና አልፍሬድ ዳኔልስ ዊሊያምስ ኪንግ የሚባል ታናሽ ወንድም ነበሩት።

በአትላንታ ከተማ ያደገው ብላቴናው ኪንግ በቡከር ቲ ዋሽንግተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቱን ተከታትሏል። በጣም ጎበዝ ስለነበር ዘጠነኛ እና አስራ ሁለተኛ ክፍሎችን ዘሎ ገና የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ እያለ ሞርሀውስ ኮሌጅን ሊቀላቀል ችሏል። በ1940 ዓ.ም ላይ በሞርሀውስ ኮሌጅ በስነ ጥበብ እና በሶሾሎጂ ተመርቋል። በ1943 ዓ.ም ክሮዘር ቲዮሎጅካዊ ሴሚናር ኮሌጅ ውስጥ በመማር በመለኮታዊ ዲግሪ አገኘ። ከዚያም ፕሮፌሰሮቹ ዶክትሬቱን የመቀጠል አቅም ያለው መሆኑን ስላመኑበት ትምህርቱን ቀጠለ እና ቦስተን ዩኒቨርስቲ ውስጥ  በሲስተሚክ ቲዮሎጂ ፒ ኤች ዲ አግኝቷል፤ በሰኔ ወር 1947 ዓ.ም።.

ኪንግ ኮሬታ ስኮት የተባለች ሚስቱ ጋር በጋብቻ ተጣምሮ አራት ልጆችን አፍርቷል። እነርሱም ዮላንዳ ስኮት፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ 3ኛ፣ ዴክስተር ስኮት ኪንግ እና በርኒስ ኪንግ ይባላሉ። ኪንግ በአላባማ ግዛት ሞንትጎመሪ ከተማ በዴክስተር አቬኑ ቤተክርስቲያን ውስጥ በ1946 ዓ.ም የሀያ አምስት ዓመት እድሜው ላይ ፓስተር ሆኗል።

ማርቲን ሉተር ያደገባት ከተማ አትላንታ በጥቁሮች የከፋ አድልኦ እና መገለል የሚደረግባት ነበረች። እርሱ ልጅ ሳለ በተለይ በጥቁሮቹ ሕይወት አድሎ እና መገለልን የእለት ከእለት እጣ ፋንታ ያደረገው የጅም ክሮው ሕግ በጥብቅ የሚተገበርበት ወቅት ነበር። በመሆኑም ብላቴናው ኪንግ እና ሌሎች ጥቁር ጓደኞቹ በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ ለረጅም ጊዜ ያህል ወደ ተለያዩ ስፍራዎች እንደልባቸው  ለመንቀሳቀስ ጥቁርነታቸው እንቅፋት ነበር። ወደ መዋኛ ስፍራዎች መሄድ፣ በማንኛውም የሕዝብ ፓርኮች መገኘት፣ ለነጮች በተለዩ ትምህርት ቤቶች መማር፣ ከተማ ውስጥ በሚገኙ በርካታ መደብሮች ሄዶ ሀምበርገር ወይም አንድ ስኒ ቡና መግዛት፣ በማንኛውም ቲያትር ቤት ፊልም ማየት ለአንድ ጥቁር አሜሪካዊ ብላቴና ክልክል በሆነበት ሁኔታ ነበር ያደገው በግለ ታሪኩን እንደፃፈው።

ኪንግ በዘር ከፋፋዩ ስርአት ያሳለፋቸው የወጣትነት ልምዶቹ ዘርፈ ብዙ ናቸው። በአንድ ወቅት ትንሹ ኪንግ አውቶቡስ ውስጥ አባቱ ለአንድ ነጭ ጎረምሳ ፖሊስ ወንበራቸውን ለቅቀው ቆመው መሄዳቸውን አይቷል። ኪንግ ትልቁ በእድሜያቸውም  በስራቸውም ሊከበሩ የተገባቸው ጠንካራ ሰው ነበሩ። በሌላ ገጠመኝ ኪንግ ትንሹ ራሱ፣ አትላንታ መሀል ከተማ ውስጥ የዘር ትንኮሳ ደርሶበት ነበር። የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለ ከአስተማሪው ጋር በመሆን በደቡባዊ ጆርጂያ አንድ አነስተኛ ከተማ ውስጥ የንግግር ውድድር አድርጎ ከመምህርቱ ወይዘሮ ብራድሊ ጋር ወደ አትላንታ መንገድ እንደ ጀመሩ ሾፌሩ ኪንግን እና አስተማሪውን ወንበራቸውን ለነጭ ተሳፋሪዎች እንዲለቁ አስገደዳቸው። ኪንግ እና መምህሩ አትላንታ ድረስ ያለውን የሶስት ሰዓታት መንገድ ቆመው መሄድ ነበረባቸው። “ያ ምሽት ከአእምሮዬ በፍፁም አይጠፋም። በጣም አናዳጁ ገጠመኜ ነው። በሕይወቴ ከተናደድኩባቸው ይህ የበለጠው ነው” ሲል ግለ ታሪኩ ላይ እጅግ ካበሳጩት የልጅነት ገጠመኞቹ መካከል ጠቅሷቸዋል።

ኪንግ  የፒ ኤች ዲ መመረቂያ ፁሁፉን ካጠናቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ በሕዳር 11 ቀን 1936 ዓ.ም ላይ ሮዛ ፓርክስ በሞንትጎመሪ የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ለአንድ ነጭ ወንበሬን አልለቅም ያለችበት ጊዜ ነበር። አሻፈረኝ አለች እና በቁጥጥር ስራ ዋለች። የእርሷም መያዝ ለሞንትጎመሪው የአውቶቡስ አድማ መጀመር ምክንያት ሆነ። እርሷ በተያዘችበት እለት ምሽቱን በወቅቱ የሕብረቱ መሪ እና አንቂ ኢ.ዲ ኒክሰን ለኮንግ በመደወል አድማውን እንዲቀላቀል እና የአድማውን ስብሰባዎች በራሱ ቤተክርስቲያን እንዲመራ ነገረው። ኪንግ አመነታ፣ ከመስማማቱ በፊት የጓደኛውን ራልፍ አበርናቲን ምክር ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ያ ስምምነት ኪንግን ወደ ሲቪል መብቶች ንቅናቄ  አመራርነት ደረጃውን ጨመረው።

በሕዳር 25 ቀን 1936 ዓ.ም ላይ ሞንትጎሞሪ ኢምፕሩቭመንት ማህበር የተሰኘው በወቅቱ አድማውን ይመራው የነበረው ድርጅት ኪንግን ፕሬዝደንት አድርጎ መረጠው። የሞንትጎመሪ አፍሪካ አሜሪካውያን ዜጎች ስብሰባዎች የኪንግን አንደበተ ርዕቱነት በግልፅ አይተው ወደውት ነበር። የሞንትጎመሪ ነጮች ለመደራደር ባለመፍቀዳቸው አድማው ማንም ከሚገምተው በላይ ረጅም ጊዜ ቆየ። የሞንትጎመሪ ጥቁር ማህበረሰብ እንደ አስፈላጊነቱ የጋራ ተሽከርካሪዎችን በማደራጀት እና በእግር ወደ ስራ በመሄድ በሚደንቅ ሁኔታ ጫናዎችን ተቋቋመው በትግላቸው ፀንተዋል። አድማው በተደረገበት ዓመት የሰላማዊ ትግል ፍልስፍናውን የፈጠሩለትን ወሳኝ ህሳቤዎቹን አዳብሯል። ይኸውም አንቂዎች በተለሳለሰ እና ሰላማዊ ተቃውሞ፣ የነጮችን ጭካኔ እና ጥላቻ ሊገልጡ እንደሚገባ የሚመክር ነበር። ምንም እንኳ የማህተመ ጋንዲ ተፅዕኖ ቢኖርበትም ከዚያ ቀደምት ብሎ ከክርስትና እምነቱ ውስጥ ነበር የራሱን ህሳቤዎች ያዳበረው።

አድማው በታህሳስ ወር 1948 ዓ.ም ላይ የሞንትጎመሪን አውቶቡሶች በማቀናጀት ስኬታማ  ነበር። ዓመቱ ለኪንግ እጅግ ፈታኝ  ነበር፤ በቁጥጥር ስር የዋለበት እና በቤቱ ፊት ለፊት ተቀጣጣይ ቦምቦች የተቃጠለበት ነበር። ነገር ግን ያ ዓመት በተጨማሪ ኪንግ በሲቪል መብቶች ንቅናቄ ውስጥ ሚናውን የተቀበለበት ነበር።

በ1951 ዓ.ም  ኪንግ ወደ ሕንድ ተጓዘ እና ከጋንዲ የቀድሞ መኮንኖች ጋር ተገናኘ። ሕንድ በ1939 ዓ.ም ከእንግሊዝ ነፃነቷን ተቀዳጅታ ነበር፤ ለዚህ ድል ምክንያት የጋንዲ የሰላማዊ የትግል ንቅናቄ ነበር። ክፉውን አገዛዝ በመቃዎም ነገር ግን ከግጭት ነፃ በሆነ መንገድ የሚል ፍልስፍና ነበር። ኪንግ በሰላማዊ ትግል አማካይነት የሕንድ የነፃነት ንቅናቄ አስደማሚ ስኬታማነት ቀልቡን ገዝቶታል።

ኪንግ ወደ አሜሪካ ሲመለስ ሰላማዊ ትግልን አጠናክሮ በማስቀጠል ውጤታማ ድል ማስመዝገብ እንደቻለ ታሪኩ ያስረዳል። አድማዎችን በሚያስተባብርባቸው በርካታ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ይታሰር ይፈታ ነበር። በ1955 ዓ.ም በርሚንግሃም የዘር አግላይነትን በመቃወም በተቀጣጠለው የተቃውሞ ሰልፍ ኪንግ ለአስራ ሦስተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋለበት ነበር። አድማው ለ382 ቀናት ተከናወነ። በታህሳስ 11 ቀን 1948 ዓ.ም የአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በአውቶቡስ ላይ የሚደረገው የዘር ልዩነት ሕገመንግስታዊ እንዳልሆነ እና ጥቁሮች እና ነጮች እኩል እንደሚገለገሉ መወሰኑን ይፋ አደረገ። በእነዚህ የአድማ ቀናት ኪንግ ለእስር ተዳርጓል፣ ቤቱ በቦምብ ጋይቷል፣ ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት እርሱ የጥቁሮች የመጀመሪያ ደረጃ መሪ ሆኖ ብቅ ያለበት ነበር።

በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው ሆነ። በ1950ዎቹ ወቅት በአላባማ፣ የፍሎሪዳ እና ጆርጂያ በተደረጉ ሰላማዊ የሕዝብ ተቃውሞዎች ላይ ኪንግ ለእስራት ተዳርጓል። ኪንግ በነሐሴ ወር ታዋቂውን “ሕልም አለኝ” ንግግሩን በዋሽንግተን  ናሽናል ሞልቶ ላይ ለተሰበሰቡ 200ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች አቅርቦ ወደ ፊቱን የተነበየው እስኪመስል  ብዙዎችን አስደንቋል። ትግሉ የጥቁሮችን የመምረጥ መብት አስገኝቷል። የተለያዩ ዘረኛ እና ከፋፋይ ህጎች ተሽረው የጥቁሮች መብቶች ተከብረዋል።

ነገር ግን በሰላማዊ የትግል ስልቱ የዘረኝነትን መሰረቶች እየናደ የእኩልነትን ዜማዎች እያስተጋባ በድል ላይ ድልን እያነባበረ መሄዱን የማይፈልጉ አክራሪ ነጮች ቀን ይጠብቁለት እንደነበር ኪንግ ራሱ ያውቅ ነበር። ቢሆንም ከትግል ፈቀቅ አላደረገውም። ለአላማው እስከመሞት  ልቡ የቆረጠ ጀግና ነበር። እናም መጋቢት 24 ቀን 1960 ዓ.ም ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹ በሜምፊስ ተገደለ። እጅግ አስደንጋጭ ክስተት ነበር። መላው አሜሪካ በጀግናዋ ሞት አነባች፣ ነገር ግን ኪንግ በስራዎቹ ሁሌም ህያው ሆኗል። አሜሪካ ሁሌ በየዓመቱ የጥር ወር ሦስተኛው ሰኞ የማርቲን ሉተር ቀን ተብሎ እንዲከበር ተወስኗል።  እኛም አበቃን።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here