ጥቁሯ አልማዝ

0
164

ከፍተኛ የመተጣጠፍ እና ቅልጥፍናን በሚጠይቀው የአርትስቲክ ጅምናስቲክ ስፖርት የምንጊዜም ምርጥ ከሚባሉት ስፖርተኞች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ትሰለፋለች። በዘርፉ በሜዳሊያ የተንቆጠቆጠች ሦስተኛዋ ስፖርተኛ ጭምር ነች። በትውልዷ ካሉ የአርትስቲክ ጅምናስቶች መካከል ቀዳሚዋ ንግስት ናት ይሏታል። ከሁለት ዓመታት በፊት የነፃነት ፕሬዝዳንታዊ ሽልማትን በነጩ ቤተ መንግስት ከአዛውንቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተቀብላለች። አራት ጊዜ የሎሪየስ የዓለም የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ሽልማትን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለአራት ጊዜ ወስዳለች። በአርትስቲክ ጅምናስቲክ እንደ ምልክት የምትቆጠር ጥቁር አሜሪካዊቷ ስፖርተኛ- ሲሞን ባይልስ።

የሲሞን ባይልስ በአሜሪካ ኮሎምበስ ኦህዮ ነው የተወለደችው። የልጅነት ህይወቷ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ገና በልጅነት እድሜዋ ነበር አባቷ ካልቪን ክሌሞንስ ቤተሰቡን ጥሎ የጠፋው። የአልኮል እና የአደንዛዥ እጽ ከፍተኛ ተጠቂ የነበረቸው እናታቸው ሻኖን ባይልስ፤ ልጆቿን ማሳደግ ባለመቻሏ ለማደጎ ተሰጥተዋል።

ከ2003 እ.እ.አ ጀምሮም ከእህት እና ወንድሟ ጋር በአያታቸው ስር አድገዋል። የ27 ዓመቷ ስፖርተኛ ገና የስድስት ዓመት ታዳጊ ልጅ እያለች ነበር የጅምናስቲክ ስፖርትን የጀመረችው። በወቅቱ ያላትን ተሰጥኦ እና ክህሎት የተረዳው የታዳጊዋ መምህር በስፖርቱ እንድትቀጥል ያበረታታት እንደነበር የታሪክ ማህደሯ ያስረዳል።

ስምንት ዓመት ሲሞላት ደግሞ ይሄንን ድንቅ ክህሎት እና ተሰጥኦም ቤተሰቦቿ መረዳት ችለዋል። ታዲያ አሳዳጊዎቿም የታዳጊዋን የወደፊት የስፖርት ህይወት ለማስተካከል በግል አሰልጣኝ እንድትሰለጥን አድርገዋል።

ከ14 ዓመቷ ጀምሮ ደግሞ በሁሉም የአሜሪካ ወጣቶች የጅምናስቲክ ውድድር በመሳተፍ አስደናቂ ብቃቷን ማሳየት ችላለች። ሲሞን ባይልስ የመጪው ዘመን የጅምናስቲክ ኮከብ መሆኗን አስመስክራለች።

በስፖርት ህይወቷ ፈጣን ለውጥ እና እድገት ያሳየችው የጅምናስቲክ ስፖርተኛዋ በ16 ዓመቷ በዓለም ሻምፒዮና፣ በዓለም አርትስቲክ ጅምናስቲክ ሻምፒዮና፣ በአሜሪካ ብሄራዊ የጅምናስቲክ ሻምፒዮና እና በመሳሰሉት ውድድሮች ያሸነፈች ሰባተኛዋ ጥቁር አሜሪካዊት መሆን ችላለች።

በ2015 በፈረንጆች በዘርፉ በአሜሪካ ብሄራዊ ሻምፒዮና በግለሰብ ሁለንተናዊ ዝግጅት ውድድር ያሸነፈች ሁለተኛዋ አሜሪካዊት ሆና ስሟ በክብር መዝገብ ሰፍሯል። በተጨማሪም በዚሁ ዓመት የዓለም የጅምናስቲክ ሻምፒዮናን ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴት የጅምናስቲክ ስፖርተኛ መሆኗን ዘ ጋረዲያን አስነብቧል።

አንድ ሜትር ከ42 ሴንቲ ሜትር ብቻ የምትረዝመው ጅምናስት እስካሁን በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ 14 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከሁሉም ስፖርተኞች ትልቃለች። ከእነዚህ መካከል ዐስሩ የወርቅ ሜዳሊያ ነው። ሲሞን ባይልስ የኦሎምፒክ መድረክን “ሀ” ብላ የጀመረችው በብራዚል ምድር በተደረገው በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ ነው። ከብዙ ፈተናዎች በኋላ ወደ ኦሎምፒክ መድረኩ ማቅናቷን መረጃዎች አመልክተዋል።

ውድድሩ ከመጀመሩ ከወራቶች ቀደም ብሎ ሲሞን ባይልስ አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዷን የሚያረጋግጡ ዘገባዎች ከወደ ሩሲያ ተሰሙ።  ከሩሲያ የመገናኛ አውታሮች ዜናውን የሰሙት በርካታ አሜሪካውያን እና የስፖርቱ አፍቃሪያን ተደናግረው እንደነበር መረጃዎች ወጥተዋል። ይሁን እንጂ ባለተሰጥኦዋ ጅምናስት የትኩረት ማጣት ሀይፐር አዲክቲቭ ችግር እንዳለባት፤ ለዚህ ችግርም በህክምና የታዘዘላትን መድሀኒት እየወሰደች እንደምትገኝ በኤክስ (ቲዊተር) ገጿ አስፍራለች።

አበረታች ንጥረ ነገር ነው የተባለውም ከዚህ መድሀኒት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እና ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ተቋሙም ጉዳዩን እንደሚያውቅ ጭምር በመንገር አብራርታለች። በኋላ ላይ ከህመሟ አገግማ በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ ተሳትፋለች። በቡድን እና በግል አራት የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማስመዝግብ የፕላኔታችን ምርጧ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ መሆኗን አስመስክራለች።

በ31ኛው ኦሎምፒያድ የመዝጊያ ስነ ስርዓት የአሜሪካንን ልዑክ በመወከል ስንደቅ አላማ ይዛ የታየች የመጀመሪያዋ ሴት አሜሪካዊት ጅምናስት ሆናለች። ከአስደናቂው ሪዮ ኦሎምፒክ ውጤት በኋላ ታዳጊዋ ሲሞን ባይልስ በጋዜጠኛ ሚሼል በርፎርድ አማካኝነት የህይወት ታሪኳ ተጽፏል። “Courage to soar, A body in motion, A life in balance,” የተሰኝውን መጽሐፍ የታዳጊዋን ውጣ ውረድ ያሳያል። መጽሐፉም ኒወርክ ታይምስ ባስነበበው ጽሁፍ ቁጥር አንድ ተነባቢ መጽሐፍ እንደነበር ተመዝግቧል።

ምንም እንኳ ውድድሩን እስከ መጨረሻው ባታጠናቅቅም በቶኪዮ ኦሎምፒክ አንድ ብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በወቅቱ ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና መታወክ የደረሰባት ሲሆን ውድድሩን ሳታጠናቅቅ የጃፓንን ምድር ለቃ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች። በ32ኛው ኦሎምፒያድ አንድ ብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፏ አይዘነጋም።

ባለተሰጥኦዋ ጅምናስት ከዚያ በኋላ ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ከውድድር ርቃ ቆይታለች። በ2023 ሰኔ ወር ላይ ግን ወደ ውድድር ተመልሳለች። በ2023 የዓለም ሻምፒዮናም ሁለት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ በማሸነፍ ወደ ፉክክር መድረኩ በድል የተመለሰችው ጥቁር አሜሪካዊት ኮከብ በፓሪስም አስደማሚ ብቃቷን አሳይታለች።

በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ ሦስት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ ለሀገሯ አስገኝታለች። በዘርፉ አስቸጋሪ የሚባሉትን ክህሎቶች በማሳየት የምትታወቅ ስፖርተኛ ነች። ሲሞን ባይልስ በ2021 ታይም መጽሔት ከዓለም 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዷ አድርጎ መርጧታል። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ለታላላቅ ሰዎች የሚበረከተውን የነፃነት ፕሬዝዳንታዊ ሽልማት በኋይት ሀውስ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተበርክቶላታል። ባይልስ ይህንን ሽልማት የተቀበለች በእድሜ ትንሿ ለመሆን በቅታለች። ባለፉት ሦስት የኦሎምፒክ መድረኮች ሰባት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ሁለት የብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችንም አግኝታለች።

በዓለም ሻምፒዮና ደግሞ 23 የወርቅ፣ አራት የብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈች ጀግና አትሌት ነች። እንዲሁም በፓስፊክ ሪም ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 32 ወርቅ፣ ስድስት ብር እና አምስት የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋለች። ብርቱዋ ስፖርተኛ በቀጣይ ዓመታትም በአርትስቲክ ጅምናስቲክ ዘርፍ ንግስነቷን ሊያወርዳት የሚችል ተፎካካሪ እንደሌለ ተዘግቧል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here