በባልካን ባህረ ገብ መሬት ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ግሪክ በሰሜን ምዕራብ ከአልባኒያ፣ በሰሜን ከመቄዶንያ እና ቡልጋሪያ፣ በምሥራቅ ከቱርክ ጋር ድንበር ትጋራለች። 131 ሺህ 957 ኪሎ ሜትር በሚሸፋነው መሬቷ ከ10 ሚሊየን በላይ ህዝብ ይኖርባታል።
የጥንት ግሪክ ሥልጣኔ በ1200 ዓ.ዓ ገደማ ካበቃው ከመይሴኒያ ሥልጣኔ እስከ ታላቁ እስክንድር የስልጣን ዘመን ማብቂያ 323 ዓ.ዓ እንደሚደርስ ይነገራል።
ዓለማችን ዛሬም በዘርፉ የምትጠቀምባቸው በፖለቲካ፣ በፍልስፍና፣ በኪነ ጥበብ እና በሳይንስ የተመዘገቡት ዘመን የማይሽራቸው ውጤቶች የጥንታዊ ግሪክ ሥልጣኔ መለያ ናቸው፡፡ እ.አ.አ በ1896 የመጀመሪያው እና ዘመናዊው የኦሎምፒክ ጨዋታ በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ነበር የተካሄደው፡፡ ግሪኮች በቀደመው የአውሮፓ ታሪክ ላይ በፍልስፍና፣ በሂሳብ፣ በሥነ ፈለግ ጥናት ( አስትሮኖሚ) እና በሕክምና ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።
ሥነ ጽሑፍ እና ቴያትር የግሪክ ባህል የጎላ ገጽታ ሲሆን ለዘመናዊ ድራማ መጀመር ተጽዕኖው የጎላ ነበር፡፡ ግሪኮች በተራቀቁ ሐውልቶቻቸው እና የህንፃ ጥበባቸው ይታወቃሉ። ሶቅራጥስን፣ ፕላቶን እና አርስቶትልን የመሳሰሉ ታዋቂ ፈላስፎች መፍለቂያቸው ግሪክ ነው፡፡ ግሪክ በኦሎምፒክ ጀማሪነቷ እና በጥንት ስልጣኔዋ ለዓለም ካበረከተቻቸው ትሩፋቶቿ ባለፈ ሀገሪቷ ሊጎበኙ በሚችሉ አስደናቂ ታሪካዊ ቦታዎች የተሞላች ናት፡፡
ግሪክ ከ10 ሚሊየን ሕዝቧ 90 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ ሁለት በመቶ ደግሞ የእስልምና እና የተቀሩት የሌሎች አምነት ተከታዮች ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዝዳንቷ ኮንስታቲኒስ ታሶላስ እና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ኪሪያኮስ ሚጾታኪስ ናቸው፡፡
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የግሪክ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ከ436 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው፤ የነብስ ወከፍ ገቢዋም 24 ሺህ ዶላር ሲሆን ይህም በዓለም 46ኛ ደረጃን እድትይዝ አድርጓል፡፡ የመገበያያ ገንዘቧም ዩሮ ነው፡፡
የግሪክ አብዛኛው ግዛቷ ሞቃታማ፣ በጋ እና ዝናባማ (ክረምት) ነው፡፡ ሀገሪቱ በተራራ የተሞላች እና ባሕረ ገብ ናት፡፡ ተረራማ ገጽታዋ ብዛት ካላቸው የባሕር ዳርቻዎቿ ጋር ተዳምረው ግሪክን ምድረ ገነት እንዳስመሰሏት ጎብኝዎች ይመሰክራሉ፡፡
ቱሪዝም ለግሪክ የጀርባ አጥንቷ ነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፉም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ (ጂዲፒ) 21 ከመቶውን ይሸፍናል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2022 ግሪክ በዓለም ላይ እጅግ ከተጎበኙ ሀገራት አንዷ ስትሆን በዘጠነኛ ደረጃ ላይም ተቀምጣለች፤ 28 ሚሊየን ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ ጎራ እንዳሉም የጀርመን ድምጽ ዘግቧል፡፡
ግሪክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ 19 ሀብቶች አሏት፡፡
ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ይተማሉ፡፡ ከመዲናዋ አቴንስ ጀምሮ እስከ 11 ካሬ ማይል ስፋት እስካላት የሃሊኪ ደሴት በርካታ የጎብኚ መዳረሻዎች ይገኛሉ፡፡ ያልተለመደ ስነ-ህንፃ ንድፍ ያለው የቻኒያ ከተማ የግሪክ አንዱ መገለጫ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የሆሊዉድ ፊልሞች እና ተከታታይ የቲቪ ድራማዎች መቼት በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
የግሪክ ዜጎች በፈገግታቸው እና በእንግዳ ተቀባይነታቸው ይታወቃሉ፡፡ የውሸት ፈገግታ ብሎ ነገር የለም፤ እነሱ ዘንድ፡፡ በፈገግታ ሰላምታ ሰጥተዋችሁ ወዲያውኑ ከፊታቸው ፈገግታቸው ታጥቦ የሚጠፋ አስመሳዮች አይደሉም፤ ግሪካዊያን፡፡ ይህን ደግሞ ዓለም አቀፍ ተጓዡ አቤል ብርሃኑ (የወይኗ ልጅ) ግሪክን በጎበኘበት ቪዲዮ አረጋግጦልናል፡፡
አጅግ ብዙ ጎብኝዎች የሚጎርፉበት ማዕከላዊ ሜቄዶኒያ ነው፡፡ ስፍራው በባሕር ዳርቻዎች ያሸበረቀ ነው፡፡ ሳንቶሪኒ የተሰኘው ከተማ ደግሞ በኖራ በተለበጡ ህንፃዎች፣ ለዐይን በሚስቡ ትንንሽ ቀለማት ያሸበረቁ ቤቶች፣ ጠመዝማዛ መንገዶች እና ከፍ ያሉ ጉልላቶች የተገነቡበት ነው፡፡ ስፍራው ያለው እይታ እና ማራኪ ስነ-ህንፃ ዲዛይን የጎብኝን ቀልብ ይስባል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2011 ሳንቶሪኒን ትራቭል ሌዠር የተሰኘ መጽሔት የዓለማችን ምርጡ ደሴት ሲል አንቆለጳጵሶታል፡፡
በግሪክ የሚኖአን ሥልጣኔ መነሻዋ የኖሶስ ከተማ በብዙዎች ዘንድ በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከተማ እንደሆነች ይነገራል፡፡ በውስጧ የያዘቻቸው ታሪካዊ እና ጥንታዊ ስፍራዎች ልዩ ያደርጓታል፡፡ ከተማዋ በሄራክሊዮን ዳርቻ ላይ የምትገኝ ሲሆን ታዋቂ የጎብኚ መዳረሻ ሆና ዓመታትን ተሻግራለች፡፡ የአስደናቂው የኖሶስ ቤተ-መንግሥት ቅሪቶች የዚያን ጊዜ አስደናቂ ስነ-ህንፃ ንድፍን ክህሎት ማስረጃዎች ናቸው። በተጨማሪም በሄራክሊን በሚገኘው የአርኪኦሎጂ ቤተ መዘክር ጥንታዊ ግሪካዊያን ሲገለገሉባቸው የነበሩ የተለያዩ ዕቃዎችን እና ምስሎችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ስፍራን አካቶ የያዘ ነው፡፡
ከላይ ከጎበኘናቸው ከተሞች በተጨማሪ የማይኮኖስ ባህር ዳርቻ፣ በናፍፕሊዮ ያሉ የቬኒስ አርክቴክቸር፣ የኦቶማን አወቃቀሮች፣ የጥንት ግድግዳዎች፣ የመካከለኛው ዘመን ሐውልቶች እንዲሁም የዴልፊ ከተማ ባለው ጥንታዊነት እና ታሪካዊነቱ በዩኔስኮ መዝገብ ላይ ሊሰፍር ችሏል፡፡
በስልጣኔ፣ በፖለቲካ፣ በኪነ ጥበብ፣ በሳይንስ እና በፍልስፍና ፈር ቀዳጅ የሆነችው ግሪክ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በስፋት የሚካሄዱባት ሀገር ጭምር ነበረች፡፡ በጥንቷ የግሪክ ደቡባዊት ክፍል ኦሎምፒያ እ.አ.አ በ776 የተካሄዱ ጨዋታዎች ዓለም አሁንም ድረስ በጉጉት የሚጠብቀውን እና በየአራት ዓመቱ የሚዘጋጀው የኦሎምፒክ ውድድር መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል፡፡
አሁን ድረስ ኦሎምፒክ በመባል የሚታወቀው ስፖርታዊ ውድድር ስሙን ያገኘው ግሪክ ውስጥ ከሚገኝው የኦሎምፒያ ተራራ ነው። የዘመናዊው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መስራች የሆነው ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደ ኩበርቲን ነበር።
ባሮን በ393 ዓ.ም በኦሎምፒያ ግሪክ በተካሄደው እና በርካታ ይዘት ባላቸው ጥንታዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በመማረክ ሀገራት ውድድር ለማዘጋጀት የሚፎካከሩበትን የዛሬውን የኦሎምፒክ ጨዋታ ለዓለም ህዝብ አስተዋውቋል፡፡ ግሪክን በጥቂቱ እንዲህ አስጎበኘናችሁ! ሰላም!::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም