ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ምዕራባዊያንን ከባድ ስጋት ውስጥ ያስገባ ነው፣ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት:: የጦርነቱ ዋነኛ ምክንያቴ ነው ስትል ሩሲያ ያነሳችው ደግሞ ዩክሬን የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) በአባልነት እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነው፤ በዚህ ምክንያትም ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ውስጥ ገብቻለሁ በማለት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻን አውጃለች።
ዳሩ አውሮፓዊያን ሩሲያ ዩክሬንን ወረረች ቢሉም፣ ሩሲያ ግን ለደህንነቴ የተጋረጠብኝን ስጋት ለማስወገድ የተጀመረ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ነው ብላዋለች፤ ስጋቱ ሙሉ ለሙሉ እስኪወገድ ድረስም ጦርነቱ እንደሚቀጥል አስታውቃለች።
በዚህም ምክንያት የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነት ካወጁ ሁለት ዓመታት አለፉ:: የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ታዲያ በሩሲያ ላይ ታይቶ የማይታወቅ የማዕቀብ ናዳ ወረደባት። አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊያን በማንኛውም ነገር አለንልሽ በማለት ዩክሬን በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ የአጸፋ ምላሽ እንድትሰጥ መገፋፋታቸውን አጠናከሩት:: ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ዩክሬንን ከውድመት፣ ዩክሬናዊያንን ደግሞ ከስደት አልታደጋቸውም።
ሁለት ዓመታትን በተሻገረው ጦርነት በርካታ ጉዳዮች ተከስተዋል፤ ሀገራቱ ከዓለማችን ቀዳሚ የስንዴ አምራች በመሆናቸውም ጦርነቱ የዓለማችንን የንግድ ሚዛን አዛብቷል፤ የኑሮ ውድነቱን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል:: በአጠቃላይ የጦርነቱ ዳፋ የዓለም ሀገራትን አካልሏል:: በተለይ አውሮፓዊያንን አይተውት የማያውቅ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንዲገጥማቸው አድርጓል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ድረገጽ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ጦርነቱ አራት ሚሊዮን ገደማ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ አድርጓል፤ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፤ ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃንን ሕይወት ቀጥፏል፤ 20 ሺህ የሚጠጉትን ደግሞ አቁስሏል:: የጦርነቱ ዳፋ “በቀጣዩ ትውልድ ጭምር የሚታይ ነው”ም ብሏል።
እንደ ኤን ቢ ሲ ኒውስ (NBC News) ዘገባ ሩሲያ ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን ይዞታዎችን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋለች፤ አራት የዩክሬን ክልሎችን (ዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፓሮዢያ እና ኬርሰን) ወደ ግዛቷ ጠቅልላ ማስገባቷን ደግሞ የሩሲያው የዜና አውታር አር ቲ (RT) አስታውቋል። ለአብነትም በዶኔስክና ሉሃንስክ ግዛቶች ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ የራስገዝ ዕውቅና በመስጠት ሕጋዊ የሩሲያ አካል ማድረጓን ነው ሩሲያ ያስታወቀችው:: ወደ ፊት ግስጋሴዋን በማጠናከርም የዩክሬን ዋና ከተማ ወደሆነችው ኬቭ ድረስ ዘልቃ እንደምትገባ አስጠንቅቃለች።
በጦርነቱ ዋግነር የተሰኘው ቅጥረኛ ተዋጊ በሩሲያ ወገን ስሙ ከፍ ብሎ ይነሳል፤ ዩክሬን ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባትም በጦርነቱ ሩሲያ የበላይነቱን እንድትቀዳጅ ጉልህ ሚናን ተጫውቷል:: ይሁን እንጂ ኋላ ኋላ ቡድኑ ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ፀብ ውስጥ በመግባቱ ጦሩን ወደ ሩሲያ እንደሚያዞር አስጠንቅቆ ነበር። ምስጋና ለሩሲያ ጎረቤት ሀገር ይግባና ውጥረቱ በሽምግልና እንዲረግብ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቅጥረኛ ተዋጊ ቡድኑ መሪ ፕሪጎዥን በአውሮፕላን መከስከስ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል፤ ለዚህ ደግሞ የሩሲያ እጅ አለበት በሚል በርካቶች እየተናገሩ ነው።
የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ፕሬዚደንት ፑቲን ለተጠባባቂ ጦራቸው ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፤ በዚህም ሦስት መቶ ሺህ ያህል ተጠባባቂ ጦር እንዲመዘገብ ነው ፑቲን ጥሪ ያደረጉት:: ይህ ቁጥር ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግዙፉ ወታደራዊ ቁጥር ነው ተብሏል።
ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ዓለም አቀፋዊ ስጋትን ያሳደረው ጦርነቱ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፤ በአሁኑ ወቅት የዓለም ትኩረት የእስራኤል – ሃማስ ጦርነት ላይ ቢሆንም ዩክሬናዊያን ግን የመከራ ኑሮን እየገፉ ነው:: ዩክሬን የተያዙባትን ግዛቶቿን ለማስመለስ መጠነ ሰፊ መልሶ ማጥቃት መጀመሯን ብታስታውቅም የረባ ውጤት አላስገኘላትም፤ ይባስ ብሎም በዩክሬናዊያን ዘንድ በእጅጉ ተወዳጁን እና ስመጥሩውን የጦር ጄኔራሏ ቫለሪ ዛሉዥኒን ማባረሯን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አስታውቀዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዚደንት ፑቲን አስታውቀዋል፤ ምዕራባዊያንንም አስጠንቅቀዋል። ፕሬዚደንት ፑትን ከሰሞኑ ምዕራባዊያን ሩሲያ የኒውክሌር ጦርነት እንድትጀምር እየገፋፏት ነው ማለታቸው ይታወሳል። ይህ የፑቲን ማስጠንቀቂያ ታዲያ የኒውክሌር ባለቤቷ ሩሲያ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።
ዩክሬን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ቁሳዊ ድጋፍ ስታገኝ ቆይታለች፤ ፕሬዚደንት ዘለንስኪ ከሰሞኑ ደግሞ ከቁሳዊ ድጋፍ ባሻገር የወታደር ድጋፍ ያስፈልገኛል ስትል ምዕራባዊያንን ተማፅናለች፤ ይህን ተከትሎም የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተያየት ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ የኔቶ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ስምምነት ላይ አልደረሱም፤ ኔቶ በበኩሉ ወደ ዩክሬን ወታደሮችን የመላክ ዕቅድ እንደሌለው አስታውቋል:: የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ማክሮን በበኩላቸው “የሩሲያ መሸነፍ የመላው አውሮፓ ድል በመሆኑ እንደ መጨረሻ አማራጭ ሊታይ ይገባል” በማለት ለዩክሬን ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ ሐሳብ መስተጋባት ማግሥት ታዲያ ፕሬዚደንት ፑቲን ለሀገሪቱ ሕግ አውጪዎች ንግግር አድርገዋል፤ በንግግራቸውም ከባድ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ተደምጠዋል:: ምዕራባውያን ሩሲያ የኒዩክሌር ጦርነት እንድትጀምር እየገፋፏት ነው ብለዋል:: ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በማዝመት ሩሲያን የሚዋጉ ከሆነም ሞስኮ ሀገራቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝተዋል።
ፕሬዚደንት ፑቲን ቁጣ በተቀላቀለበት ንግግራቸው “የምዕራባዊያን ሀገራት መሪዎች በሩሲያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ምን ያህል አደገኛ መሆኑን በሚገባ የተረዱት አይመስልም” ስለማለታቸው የዘገበው ሬውተርስ ነው። ፑቲን አክለውም ምዕራባውያን በግዛታቸው ውስጥ ዘልቀው ገብተው ጥቃት የሚፈጽሙ የጦር መሣሪያዎች እንዳላቸው መገንዘብ እንዳለባቸውም ነው ያስጠነቀቁት።
ፑቲን ሀገራቸው በዓለማችን ቀዳሚ ያደረጋትን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እያዘመነች መሆኑን የተናሩት ፕሬዚደንቱ፣ የሀገሪቱ ስትራቴጂክ ሃይፐርሶኒክ ኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ለየትኛውም ጥቃት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“ምዕራባውያን ጦርነት የካርቱን ፊልም ይመስላቸዋል” ሲሉ የተሳለቁት ፑቲን፣ ፀብ ማጫሩን ከቀጠሉና ወደ ዩክሬንም ወታደሮችን ከላኩ ከአዶልፍ ሂትለርም ሆነ ከናፖሊዮን ቦናፓርቴ የከፋ እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል የሚል ማስጠንቀቂያ ነው የሰጡት።
ለወትሮው ግፊ፣ ከጎንሽ ነን ሲሉ የነበሩት ምዕራባዊያን ታዲያ በአሁኑ ወቅት ዩክሬንን በራስሽ ተወጪው ያሉ ነው የሚመስሉት፤ ምዕራባዊያን የሚተማመኑበት የጦር ቃልኪዳናቸው ኔቶ፣ ወታደር እንደማይልክ በግልጽ አስታውቋል:: ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ወታደር መላክ ይቅርና ወታደራዊ ቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፋቸውን እንደሚያቆሙ እያስታወቁ ነው።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም