ጦርነት የሚደገፈው፣ ሚዛናዊም የሚሆነው የሀገርን ተፈጥሯዊ ዳር ድንበር አልፎ ለመውረር የመጣን የጠላት ኀይል ለመመከት ሲሆን ብቻ ነው:: በዚህም ኢትዮጵያ ትልቅ ስም እና አኩሪ ታሪክ አላት:: ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ ተከባ እንደ ቅርጫ ሊቀራመቷት በነበረበት ዘመን አሸናፊ ሆና የወጣችበት ታሪኳ ዛሬም ልብ የሚያሞቅ ነው:: “ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ማግስት አውሮፓ ውስጥ የምትገኝ ሀገር መስላ ነበር:: ምክንያቱም ሁሉም የአሁኖቹ የኢትዮጵያ አዋሳኞች የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው ስለነበርና በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ አዋሳኝ የነበሩት ሀገራት በሰሜን ጣሊያን፣ በደቡብ እና በምዕራብ እንግሊዝ፣ በምሥራቅ ፈረንሳይ፣ በደቡብ ምሥራቅ በኩል ደግሞ ጣሊያን፣ ከምሥራቅ ወደ ደቡብ አቅጣጫም (ሶማሊ ላንድ) እንግሊዝ ነበሩና ነው። በዓድዋ ድል ማግስት ኢትዮጵያ እንደ ደሴት በአውሮፓ ሀገራት ተከባ የኖረችው በቅኝ ገዥ ሀገራት አዘኔታ ሳይሆን ክንደ ብርቱ ልጆቿ እና መሪዎቿ ያሳዩት ያልደፈርም ባይነት እሳት ሆኖባቸው እንጂ::” ይህንን ዘመን አይሽሬ ጀብድ ያስታወሱን በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከበኩር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው::
ኢትዮጵያ ጠላትን አሳፍሮ በመመለስ ድሏ ውስጥ ውስጣዊ መቆራቆዞች ነበሩባት፤ ይህንንም እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የበቀል በትራቸውን በኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ ሲጥሩ የነበሩ ሀገራት ነበሩ፤ ዛሬም ያጋጠማትን ውስጣዊ ችግር እንደ መልካም ዕድል ያዩ ታሪካዊ የሀገሪቱ ጠላቶች ጎምጅተው እየተመለከቷት፤ ዝግጅትም እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ::
በጦርነት ውስጥ ያለፉ ግን ደግሞ የጠፉ፣ ሉዓላዊነታቸውም ተዳክሞ ዜጎቻቸው የተሰደዱባቸው የበርካታ ሀገራት ታሪክ ያጋጠሟቸውን ውስጣዊ ችግሮች በንግግር ከመፍታት ይልቅ ኀይልን ብቸኛ አማራጭ በማድረጋቸው ነው:: ይህም የኅይል ሚዛንን አይተው አሰላለፍ ለሚያደርጉ የውጭ ኅይላት በር በመክፈት መጨረሻው የሀገር ፍርሰትን ያመጣል:: እንደ ዩጎዝላቪያ እና ሶሪያ ያሉ ሀገራት ለዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው::
በሂስቶሪያን ዶት ስቴት ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ እንደሚያትተው ዩጎዝላቪያ ሰባት ክልላዊ መንግሥታት እና ሁለት ራስ ገዝ አስተዳደር ኖሯት የተመሰረተችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር:: ሀገሪቷ ለ27 ዓመታት በአምባገነን መንግሥት ተመርታለች:: መሪዉ ማርሻል ጆሲፕ ቲቶ እ.ኤ.አ በ1980 ሲሞቱ ሀገሪቷን የማስተዳደር ሃላፊነት የወደቀው በምርጫ በመጣ መንግሥት ሳይሆን “የእኔ ዘር ቢያስተዳድር ሀገሪቷን ያሻግራል…” በሚል አመለካከት በተፈጠረ አለመተማመን ሀገሪቷን ለ10 ዓመታት ያስተዳደሯት የሀገሪቱ ፌዴሬሽን አባላት እየተፈራረቁ ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በወቅቱ ሰርቦች እና ክሮአቶች (Croato) ብሔርተኝነትን መሠረት ባደረገ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል:: ይህም በፌደሬሽኑ መካከል የነበረውን ብሔርተኝነት በማስፋት ሀገሪቷን ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳስገባት ጽሑፉ ይጠቅሳል:: በዚህም የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፤ ሀገሪቷም ፈርሳ ሰባት ሉዓላዊ ሀገር ሆናለች:: ይህ ታሪክ የሚያሳየው ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ውስጣዊ ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ ነው::
ዛሬ ላይ በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድታልፍ፣ ሕዝቧም በስደት መከራውን እያየባት ያለቸችው ሶሪያ ልዩነትን በኅይል ለመፍታት በተደረገ ሙከራ ለፍርሰት መዳረጓን ታሪክ ያትታል:: የበሽር አል አሳድ መንግሥት የተነሳበትን ተቃውሞ በኀይል ለመመከት ጥረት በማድረግ ፋንታ በለው! በለው! በሚል ይስተጋባ የነበረው እብሪት ከ350 ሺህ በላይ ዜጎቿ ሕይወታቸው እንዲያጡ አድርጓል፤ ከተሞች ፈርሰዋል፤ ሚሊዮን ሕዝቧ የነገን የተሻለ መሆን ናፍቆ በተለያዩ ሀገራት ተሰዷል፤ መተዳደሪያውንም ልመና ያደረገው ውስን አይደለም::
ታዲያ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት የምትማረው ምንድን ነው? ልዩነትን እስከ መጨረሻው በኅይል ለመፍታት መሞከር ወይስ ብቸኛ አማራጭን ድርድር በማድረግ? የሚለው ብዙዎቻችን የሚያከራክር አይሆንም:: ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ከጥንት እስከ ቅርብ ጊዜው የሰሜኑ ጦርነት ማብቂያ ድረስ ጠንቅቆ ስለሚገነዘበው ነው። በመሆኑም አሁናዊ ግጭቶችም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ፍላጎት አለው:: የሰሜኑ ጦርነት ምንም እንኳ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ አግኝቶ ለሁለት ዓመታት ከአገልግሎት ውጭ ሆነው የቆዩት ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴዎች እና የልማት ሥራዎች ወደነበሩበት መመለስ ቢችሉም ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የአማራ ክልል በትጥቅ የታገዘ ግጭት ውስጥ ይገኛል:: አንድ ዓመትን የተሻገረው ይህ ግጭት በክልሉ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴ፣ ስነ ልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው:: ለዚህም የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት የሰጧቸው መግለጫዎች ዋቢ ናቸው::
በ2016 ዓ.ም ብቻ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችም ሳይከፈቱ ቀርተዋል። አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ማምረት አልቻለም፣ ያመረተውንም ወደ ገበያ ማቅረብ ያልቻለበት ነው:: መንገዶች በተደጋጋሚ ሲዘጉ ከርመዋል፤ አሁንም እየተዘጉ ነው:: ይህም ምርት ወደ ገበያ እንዳይገባ በማድረግ የምርቶች እና የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጓል::
የጤና አገልግሎቱ እጅጉን ተፈትኗል:: የክልሉ ጤና ቢሮ በተለያዩ ጊዜያት እንዳስታወቀው ግጭቱ እና የመንገዶች በተደጋጋሚ መዘጋት የሕክምና ግብዓትን በወቅት ለማድረስ እንዳይቻል አድርጓል:: ይህም ታዲያ ሕዝቡ የሚፈልገውን የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል:: የጤና ተቋማት የማስፋፊያ እና አዳዲስ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ እክል መፍጠሩም ተመላክቷል::
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጥቅምት 05 ቀን 2017 ዓ.ም የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ውይይት ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው እልባት ያልተሰጠው ግጭት በክልሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና መምህር እና ተማራማሪ እንዲሁም በኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ማኅበር የአማራ ቻፕተር ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው ቀድሞውንም ደካማ የነበረው የጤና ሥርዓት እልባት ባልተሰጠው በትጥቅ የታገዘ ግጭት እጅጉን እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል:: በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሙያዎች እየተፈናቀሉ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል::
የጤና ሥራ ከየትኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ነው። በመሆኑም የታጠቁ ወገኖችን የምንለምናቸው የጤና አገልግሎቱን የሚጠብቁ ሕጎችን እንዲያከብሩ ነው ብለዋል:: ሕጻናት እና እናቶች እንዳይሞቱ፣ መድኃኒት እንዲደርስ፣ በማንኛውም ሁኔታ መንገድ እንዳይዘጋ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: የጤና ተቋማት ባለሙያዎችም ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ጠይቀዋል::
በክልሉ የተፈጠረውን እና ከአንድ ዓመት በላይ የተሻገረውን በትጥቅ የታገዘ ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮችን ሲያደርግ ቆይቷል:: ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል:: ይህም ሕዝቡን የሰላም አርበኛ በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማስረጽ ያለመ ነው:: የታጣቂ ኅይሉ አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪዎችም ተደርገዋል:: በዚህም በርካታ የታጣቂ ኅይሉ አባላት እጃቸውን ለመንግሥት በመስጠት እና የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን የክልሉ መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም:: እነዚህ ሁሉ ሥራዎች የክልሉ ሰላም ወደ አንጻራዊነት እንዲመለስ በማድረግ ክልሉ ወደተሻለ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል:: የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ መንገሻ ፈንታው በበኩላቸው በ2016 ዓ.ም የተደረጉ የሰላም አማራጭ ጥረቶች ለውጥ ባለመማምጣታቸው በአሁኑ ወቅት የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም አስታውቀዋል::
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለማስቆም ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን እና ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል:: መንግሥት በሕዝብ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን በተደጋጋሚ ማስታወቁ አይዘነጋም:: የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችም ውስጣዊ ግጭቱ መፍትሄ እንዳገኘ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስታውቀዋል:: የህገ መንግስቱ ማሻሻል ጥያቄውን ለመመለስ መንግሥት እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ከወራት በፊት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች ጋር በተደረገ ሕዝባዊ ውይይት ወቅት ማስታወቃቸው ይታወሳል::
የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ባይሳ ዋቅወያ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ለአውስትራሊያው ኤስ ቢ ኤስ የበይነ መረብ ሚዲያ ጥር 2021 ዓ.ም ባጋሩት ጽሑፍ የኢትዮጵያን የግጭት ምንጭ በማድረቅ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል:: በፌዴራል ሥርዓቱ ራስን በራስ የማስተዳደር መርህ መሠረት በተፈጠሩት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ክልሉን እንደ አንድ ነጻ ሀገር በመመልከት ለዘመናት በመልካም ጉርብትና ይኖር የነበረውን የሌላ ብሔር ተወላጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ማፈናቀል እና መግደል መጀመሩ ኢትዮጵያ በቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን ገልጸዋል:: አሁናዊ ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብሩን አላልቶት ሀገሪቷን ወደ ከፋ ደረጃ አሸጋግሯታል። ታዲያ ከወዲሁ ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ላይ ማተኮር ይገባል::
የሥራ ዕድል ፈጠራው ከሕዝብ ቁጥሩ መጨመር ጋር በትይዩ እንዲጓዝ ማድረግም ይገባል:: ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ 65 በመቶ (ወደ 72 ሚሊዮን) የሚጠጋው ሕዝቧ ዕድሜው ከ24 ዓመት በታች እንደሆነ ጸሐፊው ጠቁመዋል:: አሥራ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተምረው ሥራ ያጡ ወጣቶች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል:: ኢትዮጵያ ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት በሰጠችው ትኩረት ልክ ተምሮ ሥራ ላጣው ትውልድ ትኩረት አለመስጠቷ ወጣቱ ትውልድ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት ለሚጥሩ ኅይላት መሳሪያ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቁመዋል::
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለመገንባት ምሑራን ከብሄር ወጥተው በጋራ የሚያሻግሩ ሐሳቦችን እንዲያዋጡ ጠይቀዋል:: ምሁራን ሕዝቡን ወደ አንድነት በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ እንደ መወያየት አንደኛውን ቡድን አወድሶ ሌላውን መኮነኑ ግን ግጭቱ በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንዳያገኝ ከማድረግ ባሻገር ውጤት እንደማያመጣ ያምናሉ:: “አንድ ሰው የራሱን ጎሣ፣ ሃይማኖት ወይም የፖሊቲካ እምነቱን ከፍ አድርጎ እውነት እና ፍትሕን ካሳነሰ ለሰው ልጅ ሸክም ነው” የሚለውን የናይጄሪያ ሴኔት አፈ ጉባዔ ቹባ ኦካዲግቦ (ዶ/ር) ንግግር አጽንኦት ሲሰጡ፣ ምሁራን ሁሉንም ሕዝብ በእኩልነት በማየት የቀውስ መውጫ መንገዶችን እንዲያመላክቱ ጠይቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም