ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ክረምቱስ እንዴት ነው? ጊዜያችሁን በጨዋታ እና ትህርታዊ በሆኑ ነገሮች እያሳለፋችሁ ነው? ልጆች ስለጨዋታ እና ዐይነቶቹ ልንነግራችሁ ወደናል፡፡
ልጆችዬ፣ ከሕፃናት መብቶች ቀዳሚው በቂ የጨዋታ ጊዜ እና የመጫወቻ ዕድል ማግኘት ነው። ጨዋታ ልጆች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም ረገድ ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሠረታዊ እና ወሳኝ ጉዳይ ነው። የሰው ልጆችን ዕድገት የሚተነትነው “ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ” ልጆች በየደረጃቸው መጫወት የሚገባቸው ጨዋታ ካልተጫወቱ ጫናው እስከ እርጅና ባለው የዕሜያቸው ደረጃ እንደሚከሰት እና ፈተና እንደሚሆንባቸው ይተነትናል። “ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ” ከሚዘረዝራቸው ስምንት የሰው ልጆች የዕድገት ደረጃዎች አምስቱ የሕፃናትን ዕድገት የሚመለከቱ መሆኑ ለሕፃናት ዕድገት ምን ያክል ትኩረት መደረግ እንዳለበት ማሳያ ነው።
በትክክለኛ ዕድሜያቸው ትክክለኛውን ጨዋታ የተጫወቱ ልጆች ጠንካራ የአዕምሮ፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና የስሜት ዕድገት ይኖራቸዋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ልጆች ደግሞ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ለሀገር እልፎም ለዓለም የሚጠቅሙ ዜጎች የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው። ይህን አስፈላጊ የዕድገት ደረጃ የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰኔ 4 ቀን (በፈረንጆቹ ጁን 11) በየዓመቱ የጨዋታ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ወስኗል።
“መጫወት ልጆች የደኅንነት፣ እንክብካቤ እና ፍቅር እንደሚሰጣቸው የሚያረጋግጡበት ምልክት ነው፤ በቂ የጨዋታ ጊዜ ካገኙ ከባድ ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜም እንኳ የሚጠብቃቸው እንዳለ እንዲያስቡ ያስችላቸዋል” ይላሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል። የጨዋታ ቀን እንዲኖር የሚያስፈልገው ሁሉም ሰው ልጆች በቂ የጨዋታ ዕድል ሲያገኙ የሚጠበቅባቸውን ፍሬ እንዲያስገኙ በማሰብ ለልጆች በቂ የጨዋታ ዕድል እንዲፈጠር ታስቦ እንደሆነ በድርጅቱ ድረ-ገጽ የወጣው መረጃ ያመላክታል።
ጨዋታ ከመዝናኛ አልፎ ሰዎች የሚግባቡበት ከብሔራዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበረዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ድንበሮች የተሻገረ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ነው። ጨዋታ የሰዎችን ጥንካሬ፣ ችሎታን፣ የፈጠራ ክህሎት እና አዳዲስ ነገሮችን የማሰብ አቅም ያጎለብታል። በተለይ ደግሞ ልጆች ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የስሜት ቀውሶችን እንዲቋቋሙ እንዲሁም ችግሮችን የመፍታት አቅማቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
የልጆችን የመጫወት ዕድል መገደብ ደኅንነታቸው እና ዕድገታቸው ላይ ቀጥታ ተፅዕኖ ያሳድራል። በጨዋታ የተደገፈ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ልጆች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ የሚያደርግ ውጤታማ ዘዴ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። በዚህ መልክ የሚሰጠው ትምህርት ይበልጥ አስደሳች እና ጠቃሚ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አዕምሮአቸው መረጃን በሥርዓት እንዲያደራጅ ይረዳል። በተጨማሪም ጨዋታ መቻቻልን፣ ጥንካሬን፣ ማኅበራዊ አካታችነትን፣ ግጭትን መከላከል እና ሰላምን ማጎልበት ላይ በጎ ተፅዕኖ ያለው ትውልድ እንዲፈጠር ያስችላል።
ናትናኤል ጋሻው በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲሆን 10 ዓመቱ ነው::ናትናኤል መጫወት በጣም እንደሚወድ ነግሮናል::ወላጆቹም በአግባቡ እንዲጫወት እንደሚፈቅዱለት ገልጾልናል::ከሚወዳቸው ጨዋታዎች መካከልም ብይ፣ አባሮሽ፣ ድብብቆሽ፣ እግር ኳስ፣ ነግቶ ነኪ፣ ንጉሥ ንግሥት እና ሌሎችም እንዳሉ አጫውቶናል፡፡
መቅደስ ፋንታሁን ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ስትሆን እድሜዋ 11 ነው::እሷም እቴሜቴ፣ ሱዚ፣ ገመድ ዝላይ፣ እቃቃ፣ መዝሙር መዘመር እና ሌሎች ጨዋታዎችን ትጫወታለች::
ሁለቱም ልጆች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ይዘው ለረጅም ሰዓት እንዲቆዩ ወላጆቻቸው አይፈቅዱም::ይህም በልጆች አጠቃላይ እድገት ላይ ተጽዕኖ ስላለው ነው::እናንትም ልጆች ለአደጋ ሳትጋለጡ ጨዋታዎችን መጫወት አለባችሁ፡፡
ይሞክሩ
- የውኃ ቀለም ምንድን ነው?
- የቻይና ዋና ከተማ ማን ትባላለች?
- ወደላይ ሲወጣ አየር ወደ መሬት ሲወርድ ፈሳሽ?
መልስ
1.ቀለም የለውም
- ቤጂንግ
- ዝናብ (ውኃ)
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም