“ጫናው በሦስት ጊዜ ይበልጣል”

0
189

የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት እ.አ.አ በጥቅምት 2000 ባፀደቀው ውሳኔ ሴቶች እና ሕጻናት በጦርነት ወቅት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል የመብት ከለላ ሰጥቷቸዋል:: 192 ሀገራት ውሳኔውን ተቀብለው ፈርመዋል:: ይሁን እንጂ ስምምነቱን ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሶማሊያ እስከ ሊቢያ፣ ከደቡብ ሱዳን እስከ የመን፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እስከ ሶርያ ባሉ ሀገራት በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጫና እንዳልቆመ የኢትዮጵያ ሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር እ.አ.አ. 2018 በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ አመላክቷል::
ብጥብጥ እና ግጭት ባሉባው ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን መረጃው አመላክቷል:: ይህን ተከትሎም በኤች አይቪ ኤድስ ይጠቃሉ:: በዚህም ሀገራት ያቀዱትን ለማሳካት እንደማይችሉ መረጃው ጠቁሟል::
የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት መረጃ እንደሚለው በአብዛኛው በዓለም ላይ በሚከሰት ጦርነት፣ ግጭት፣ ሰብአዊ ቀውስ፣ ሁከት፣ አመጽ እና አለመረጋጋት በተለይ ትኩረት የሚያሻቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች እና ሕናት ናቸው::
ሴቶች በሰላም እጦት ወቅት የሚገጣማቸውን ችግር አስመልክቶ በጋራካ ማሼል ስተዲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ውመን ሱዛን ማኬይ የተባለች ምሁር ባደረገችው ጥናት ደግሞ በአንድ ሀገር ሰላም ሲጠፋ ሴቶች ለስደት፤ በስተመጨረሻም ለሞት እንደሚዳረጉ አረጋግጣለች::
ሱዛን ማኬይ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ባደረገችው ጥናት በጦርነት ወቅት ሴትች በሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃቶች የተነሳ የሥነ ልቦና እና ማህበራዊ ጫና ይገጥማቸዋል:: በወቅቱ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ስለማያገኙ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል ስትል በጥናቷ ገልጻለች::
የበኲር ጋዜጣ በሀገራችን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተከሰቱ ግጭቶች ሴቶች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት ባለመቻላቸው ለከፋ ድህነት የተዳረጉ ሴቶችን ታሪክ አስነብበናችሁ ነበር።
በዚህ ዕትም ደግሞ ግጭት በሴቶች ላይ ገቢን ከማሳጣት ባለፈ የሚያደርሰውን የሥነ ልቦና እና የአዕምሮ ጤና ችግር በተመለከተ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጥበበ ጊዮን የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህርት እና የሥነ ልቦና ባለሙያ ወ/ሮ አልማዝ ማማሩን አነጋግረናቸዋል::
ባለሙያዋ እንደሚሉት በጦርነት እና ግጭት ወቅት የሚፈጠረው አለመረጋጋት በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከወንዶች በሦስት እጅ ይበልጣል። ምክንያቱ ደግሞ ሴቶች ከሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት ጀምሮ ካለአባት የሚያሳድጓቸውን ልጆች ፍላጎት የሚያሟላ ገቢ አለማምጣታቸው የሚፈጥርባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት(ጫና) ከፍተኛ መሆኑንም ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
ባለሙያዋ እንዳሉት እንደየሁኔታው የሚደርሰው ጫና የተለያየ ቢሆንም በተለይ ሁሉንም የቤተሰብ ጫና ተሸክመው ቤታቸውን የሚመሩ ሴቶች የዕለት ጉርሳቸውን በቀን ተቀን ሥራ ላይ በሚገኝ ገቢ የተመሰረተ ከሆነ ግጭት ሲከሰት ልጆቻቸውን ማብላት፣ ማስተማር…አይችልም:: “እናቴ ራበኝ!” የሚሉ ልጆችን ምግብ ሰጥቶ ርሀባቸውን ማስታገስ አለመቻል አጋዥ ከሌለ የሥነ ልቦና ጫናው ከባድ ነው። ተስፋ መቁረጥ እና በነገሮች ድባቴ ውስጥ መግባት እስከ አዕምሮ መታወክ ያጋልጣል።
የግጭት ሌላው መልክ ስደት ነው:: በሚኖሩበት አካባቢ ሰላም ከሌለ ሰላምን ፍለጋ ፍልሰት ይኖራል:: በዚህም ሴቶች ልጆቻቸውን ይዘው ሲሰደዱ ስደተኛ ጣቢያ የመቆየት እድል አላቸው:: ነገር ግን በዚም የሚደፈሩ ሴቶች ስለመኖራቸው ወ/ሮ አልማዝ ተናግረዋል::
ያደጉበትን አካባቢ መልቀቅ ሳያንስ በልጆቻቸው ወይም በራሳቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ማስተናገዱ፣ አዲስ አካባቢ መላመድ …. የእናቶች ሰቆቃ ነው። ፍልሰት በራሱ የሚያደርሰው የሥነ ልቦና ጫና ከባድ ነው።
በሌላ በኩል ልጇ ወይም የትዳር አጋሯ ወታደር ቢሆን፣ በተለየ ጎራ የተሰለፈ ቢሆን፣ ባለሥልጣን ቢሆን… የሚፈጠረው ጭንቀት ሳያንስ የሚደርስባትን መገለል እና ፍረጃ ማህበረሰቡ በሚፈለገው መንገድ ስለማይረዳት ከባድ ማህበራዊ ቀውስ እንደሚፈጠርባት ባለሙያዋ አብራርተዋል።
መጨነቅ፣ ማልቀስ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድባቴ… ደርሶባቸው አቅማቸው ተሸንፎ ደክሟቸው ከቀን ቀን ከማህበራዊ መስተጋብራቸው እንደሚደናቀፉም ባለሙያዋ አስረድተዋል:: ጭንቀቱ ከዚህ አልፎ ብቻቸውን ማውራት ሲጀምሩ፣ መረጋጋት ሲሳናቸው “ምን ሁነሻል?” ተብለው በራሳቸው ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ወደ ህክምና እንዲወሰዱ ባለሙያዋ ጠቁመዋል። በህክምና መድኃኒት ወስደው ሻል ሲላቸው ያለፉትን መከራ ያወራሉ።
ጦርነት ባለበት አካባቢ ያሉ ሴቶች በተለየ ማህበራዊ ቀውሱ፣ የኑሮ ውድነቱ… እየጨመረ ሲሄድ መኖር ግዴታ ነውና ለአዕምሮ ጤና አስቦ ርዳታ መፈለግ ያስፈልጋል ያሉት ባለሙያዋ፤ ችግሩ እንደየ ሰው እና እንደየ ግዝፈቱ ቢለያይም እንቅልፍ መተኛት አለመቻል፣ የምግብ ፍላጎት እና ክብደት መቀነስ፣ ድባቴ፣ መረጋጋት አለመቻል፣ የስሜት መረበሽ ሲኖር እገዛ መፈለግ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ በቆየ ቁጥር ከበድ ያለ የአዕምሮ ጤና ችግር ይከሰታልና ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባ መክረዋል።
የሥነ ልቦና ቀውሱ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ግን ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን ብቻን ከማብሰልሰል ለሌሎች በማካፈል እና ማህበራዊ መስተጋብርን በማዳበር መፍትሔ ያመላክታል:: በተለይም ለሚቀርቡት ሰው ችግርን ማካፈል ይመከራል። ማውራት በራሱ ችግርን የማቅለል አቅም እንዳለውም ባለሙያዋ አስገንዝበዋል::

(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here