ጳውሎስ ኞኞ

0
342

በጋዜጠኝነት እና በይበልጥም ደግሞ በደራሲነት ሙያ ተሰማርተው ትልልቅ ሥራዎችን አበርክተው ካለፉ ታዋቂ ዜጎች አንዱ ነው -ጳውሎስ ኞኞ::አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ የተወለደው ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም ሀረር ውስጥ በቁልቢ ወረዳ ነው:: ጳውሎስ ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞ እና ከኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ድሬደዋ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደ ቢሆንም ያደገው ግን ድሬደዋ መሆኑን የታሪክ ድርሳኑ ያስረዳል::

በልጅነቱ እጅግ መልከ መልካም ስለነበረ እናቱ ያወጡለት የመጀመሪያ ስሙ “አማረ” የሚል ነበር። በኋላ የበኩር ስሙን በመጽሐፍ ቅዱሱ ጳውሎስ ተኩት። የጳውሎስ አባት በልጅነቱ ስለሞቱበት ያሳደጉት እናቱ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ናቸው::

ጳውሎስ ትምህርቱን የጀመረው ጠላት (ጣሊያን) በተባረረ በሁለተኛው ዓመት ማለትም በ1935 ዓ.ም ድሬደዋ በሚገኘው ክርስቶስ ትምህርት ቤት ነው:: እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ተምሮ የሚረዳው ሰው በማጣቱ ትምህርቱን ቢያቋርጥም በታሪክ እና ሥነ ጽሑፍ ዙሪያ የተጻፉ መጽሐፍትን የማንበብ ፍላጎቱ እጅግ ከፍተኛ ነበር::  ጳውሎስ በተፈጥሮ የታደለውን የማንበብ፣ የመጠየቅ እና የመመራመር ተሰጥኦ በሚገባ በመጠቀም ራሱን በራሱ አስተምሮ በትምህርት ገፍተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱት በላይ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ ማበርከት ችሏል።

ጳውሎስ ወደ መጀመሪያዎቹ እድሜው አዘውትሮ ያነባቸው የነበሩት መጽሐፍት በፍቅር ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ የነበሩ ሲሆን ወደ መጨረሻዎቹ ዘመናት ደግሞ ሙሉ ትኩረት የሰጠው የኢትዮጵያን ታሪክ ከሥረ መሠረቱ በማንበብ እና ጽፎ በማሳተም ተግባር ላይ ነበር::

ጳውሎስ ረጅሙን የሥራ ዘመኑን ያሳለፈው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ውስጥ ልዩ ልዩ አምዶችን በማዘጋጀት ነው::ጳውሎስ በጋዜጠኝነት ሙያ ከተሰማራ ጀምሮ ደብዳቤዎች፣የጥያቄ መልስ እና የሴቶች አምድ የተሰኙትን አምዶችን በቋሚነት አዘጋጅቷል::ብዙ መጣጥፎችንና ሀተታዎችንም ጽፏል::

በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለዓመታት መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት ሕዝብን በማንቃት በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፏል። የመማርን ትርጉም የምስክር ወረቀትና የደመወዝ ጭማሪ ከማግኘት ጋር ብቻ አያይዘው ለሚመለከቱ ሰዎች ጳውሎስ ህያው ወቃሽ ነው። ራስን በማብቃት ህልምን ማሳካት እንደሚቻል ከጳውሎስ ህይወት መማር ይቻላል።

በ1933 ዓ.ም መጨረሻ የተመሰረተው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ በብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እና በኋላም በአቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም ሲዘጋጅ ቆይቶ በሦስተኛ ደረጃ አዘጋጅ ሆኖ የተሰየመው ጳውሎስ ኞኞ ነበረ::ነገር ግን ጳውሎስ በዋና አዘጋጅነት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ውስጥ የሠራው ለሦስት ወራት ብቻ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

ጳውሎስ አብዛኛውን የህይወት ዘመኑን ወዳሳለፈበት ወደ ተወዳጁ ሙያው ወደ ጋዜጠኝነት ዓለም ለመግባት የበቃው በ1953 ዓ.ም ከተገደሉት አንዱ በነበሩት በአቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ግፊት እንደነበረ በ1979 ዓ.ም የጳውሎስን የህይወት ታሪክ ለጻፈው ለአቶ ጌታቸው ታፈሰ በሰጠው ቃለ ምልልስ አስረድቷል::

ጳውሎስ ከጋዜጠኛነቱ ሙያ ጎን ለጎን በጠቅላላው ከ20 በላይ መጽሐፎችን ጽፎ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹን አሳትሟል:: ከነዚህም ውስጥ ፡- የአራዳው ታደሰ (1955 ዓ.ም)፣ የጌታቸው ሚስቶች (1955 ዓ.ም)፣ የሴቶች እምባ (1955 ዓ.ም)፣ የኔዎቹ ገረዶች (1956 ዓ.ም)፣ ድብልቅልቅ (1957 ዓ.ም)፣  ቅይጥ (1957 ዓ.ም)፣ ምስቅልቅል (1958 ዓ.ም)፣ እውቀት (1959 ዓ.ም)፣ እንቆቅልሽ (1960 ዓ.ም) ተጠቃሽ ናቸው:: አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ሦስተኛው፣ አራተኛው እና አምስተኛው አስደናቂ ታሪኮች የሚሉ መጽሐፎችን በ(1966፣ 1969፣ 1973፣ 1975 እና 1976 ዓ.ም) ላይ ለንባብ አብቅቷል ሲሉ ፈንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል::

ሠርጸ ድንግል (በአጼ ገላውዲዎስ ልጅ እና በአጼ ልብነ ድንግል የልጅ ልጅ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ)፣ የሠካራም ሸንጎ (ተውኔት) እና የአጼ ምኒልክ ደብዳቤዎች የሚሉት ሥራዎቻቸው  ደግሞ ያልታተሙ ናቸው ሲሉም ነው ፈንታሁን እንግዳ በመጽሐፋቸው የገለጹት::

ለሕትመት ከበቁት ሥራዎቹ በተጨማሪም የአጤ ዮሐንስ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የአዲስ አበባ ታሪክ፣ የልጅ ኢያሱ ታሪክ፣ አዜብና ሰዎቹ የተሰኙ ያልታተሙ ሥራዎች እንዳሉትም በአዲስ ዘመን ላይ በወጣ የጳውሎስ ታሪክ ተመላክቷል::

ጳውሎስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጸሐፊነት ለረጅም ዓመታት፣ በአዘጋጅነት ደግሞ ለጥቂት ወራት ያገለገለ ሲሆን “ደብዳቤዎቹ” እና“አንድ ጥያቄ አለኝ” የተሰኙ አምዶችን ያዘጋጅ ነበር።

በርካቶች ጳውሎስን የሚያስታውሱት ትልቅ ተወዳጅነትንና ዝናን ባተረፈበት አንድ ጥያቄ አለኝ በሚለው የአዲስ ዘመን የጋዜጣ አምዱ ነው። ጳውሎስ ኞኞ ተወዳጅ በነበረው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የ“አንድ ጥያቄ አለኝ” አምድ የካቲት 1964 ዓ.ም እትም ላይ አንድ አንባቢ “እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በብዛት የሌለው ስም የቱ ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ፣ “ኞኞ” ሲል መልሶ ነበር።

ጳውሎስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እየሠራ ፈለቀች ከተባለች ቆንጆ ጋር ፍቅር ሲይዘው አንድ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ግጥም ይጽፋል። የግጥሙ የመጀመሪያ ፊደሎች ከላይ ወደታች ሲነበቡ ፈለቀች ትወደኛለች፤ እኔም እወዳታለሁ የሚል ዓረፍተ ነገር እንዲሰጡ በማድረግ ፍቅሩን በዘዴ እንደገለጸ ይነገራል። ዐፄ ኃይለ ስላሴ በአንድ ወቅት “ዳንስ ሀገርን አይገነባም” በሚል ርዕስ የጻፈውን ጽሑፍ አንብበው ደስ ስለተሰኙ 300 ብር ሸልመውታል።

ጳውሎስ ስለጸሐፊነት ባህሪው ሲጽፍ “ይምሰል አይምሰል የጠይብ እጅ ከከሰል’ እንደሚባለው እጄ እንደ ልማድ ሆኖበት መሞነጫጨርን ይወዳል:: ያን ሟጫራዬን ደግሜ ካነበብኩ ቀድጄ መጣል ነው፤ ይሰለቸኛል፣ እጠለዋለሁ፣ ስለዚህ አንድ ጊዜ በማርቀቅ የጻፍኳትን እንድትታተም እፈርድባታለሁ። ምናልባት አባጣ ጎባጣ ሆኖ አላስኬድ የሚል ገደላ ገደል ቢያጋጥማችሁ በገደምዳሜ እመር እያላችሁ እለፉት” ብሏል::

እውቁ ጋዜጠኛ እና የታሪክ ተመራማሪ እግሩ ላይ የተከሰተ የአጥንት ካንሰር ህመም ቀስ በቀስ እንዳይንቀሳቀስ አደረገው። ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ሳይነግሩት ገንዘብ አሰባስበው ፓስፖርት አውጥተው ወደ ጀርመን ተጉዞ እንዲታከም አደረጉት። የጀርመን ህክምናውን አጠናቅቆ ከተመለሰ በኋላ ህመሙ አገርሽቶበት አላላውስ ሲለው ሼክ ሙሃመድ አሊ አል-አሙዲ አሜሪካን አገር ወስደው አሳከሙት። ጤናውን ለመመለስ ብዙዎች የደከሙት ድካም ፍሬ ሳያፈራ ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ይህቺን ምድር ተሰናበተ።

አለቃ ተገኝ ታምሩ የጳውሎስን ህልፈት አስመልክተው ተከታዩን ስንኝ ቋጥረውለታል።

… በሺ ዘጠኝ መቶ በሃያ ስድስት

በዘመነ ማርቆስ በጥቢ ወራት

የምስራቁ ኮከብ ያ ጳውሎስ ኞኞ

በህዳር አስራ አንድ ተወለደ ሰኞ

ብሩህ ኮከብ ሆኖ ለሁሉም ሲያበራ

በጥበብ ጎዳና ህዝቡን እየመራ

ታሪክ እየለየ ጣፋጭ ከመራራ

አንድ ቀን ሳይሰለች ለቁም ነገር ስራ

የጳውሎስ አይነት ጸባየ ወላንሳ

ቀድሞም አልነበረ ኋላም አይነሳ

አጣነው በድንገት በግንቦት ሰላሳ

መሬት ምን ቸገራት ብትሰጠን መልሳ።

… ውድ ጳውሎስ ኞኞ የአበሻው ፈረንጅ

የጽሑፍ የቃላት ያ የታሪክ ባለጅ

ሌይት ቀን ረፍት የለው ሁሉን ሲያዘጋጅ

የስንፍና ጠላት የስራ ወዳጅ

የድካሙን ፍሬ ትቶ ለልጅ ልጅ

በስነ ተፈጥሮ በስላሴ አዋጅ

በግንቦት ሰላሳ ፈሰሰ እንደጠጅ

ግን መሞቱ አይደለም ረፍቱ ነው እንጂ።

ጋዜጠኛ እና ደራሲው ጳውሎስ ኞኞ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እና ደራሲዎች በብዙ መልኩ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው:: የጋዜጠኝነት ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ዘግየት ብሎ ቢሆንም እንደ ጳውሎስ ያሉ ስመ ጥር ጋዜጠኞች የተፈጠሩት ግን ከትምህርቱ ቀድመው ነው::ጳውሎስ በጋዜጠኝነቱም ሆነ በደራሲነት ሙያው ላይ ከልቡ ስለሚሰራ በሙያው አንቱታን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀበትም::

የጋዜጠኝነት ትምህርት በሀገራችን መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ስመ ጥር ጋዜጠኞች በሀገራችን ውስጥ ተፈጥረዋል:: ጋዜጠኞቹ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ዘገባዎችን በማቅረብ የራሳቸውን አሻራም አሳርፈዋል::ከእነዚህ ጋዜጠኞች የተለያዩ ልምዶችን በመቅሰም የጋዜጠኝነት ሙያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ ደግሞ ከተተኪ ጋዜጠኞች የሚጠበቅ ነው::ከዚህ አንጻር አርአያ ከምናደርጋቸው ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ ደግሞ ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ  ነው::

መረጃዎቹን በፈንታሁን እንግዳ ከተፃፈው (ታሪካዊ መዝገበ- ሰብ)፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ከሌሎች ዋቢ መጽሐፍት አግኝተናል፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here