ጸጋን ለይቶ ማልማት

0
82

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት “የገጠር ልማት ክላስተር ተቋማት” የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና በቀሪ ወራት ሊተኮርባቸው በሚገቡ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል::

በዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ በዋናነት የግብርና ቢሮ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ቢሮ፣ የአማራ ክልል ግብርና ኢንስቲቲዩት፣ የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ፣ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ቢሮ፣ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት፣ የመንገድ ቢሮ እና በገጠር ክላስተር ዘርፍ የተዋቀሩ ሌሎች ተቋማት ሪፖርት ቀርቧል:: የእያንዳንዳቸው በገጠር ልማት ክላስተር የተዋቀሩ ተቋማት ሪፖርት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን በቀረቡት ሪፖርቶች ላይም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል::

 

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አማራ ክልል እምቅ ፀጋዎች ያሉት፣ ሰፊ የሚታረስ ለም መሬት፣ የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለእንስሳት ሃብት ልማት፣ የማዕድን ሃብት ፀጋዎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እና የደን ሃብት የሚገኝበት ክልል መሆኑን ገልፀዋል:: ባለፉት ዘጠኝ ወራትም እነዚህን ፀጋዎች በማቀናጀት በሙሉ አቅም የጋራ ርብርብ በማድረግ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የክልሉን ምጣኔ ሃብት የሚያነቃቁ  ውጤታማ ሥራ የተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል::

 

የግብርና ቢሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተፈጥሮ ሃብት እና በመስኖ ልማት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን አብራርተዋል:: በዚህም ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተፋሰስ ሥራ ለመሥራት ታቅዶ በሁሉም ተፋሰሶች ላይ ሥራ መጀመሩን ነው የተናገሩት:: እንዲሁም ከ360 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እና ውኃ ዕቀባ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል:: በተመሳሳይ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል፡፡ የክልሉን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ በተለያዩ ደረጃ ያሉ ሙያተኞች በሰብል አመራርት ዘዴ ላይ ልዩ ስልጠና ተሰጥቷል:: የፀጥታው መደፍረስ አርሶ አደሩ በሙሉ አቅሙ ጊዜውን በልማት ላይ እንዳያውል እና በወቅቱ ግብዓት እንዳያገኝ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ  ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌትነት “የገጠር ልማት ክላስተር ተቋማት”ን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል:: በቀሪ ወራት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ሥራዎችንም አመላክተዋል::

 

በሪፖርቱ እንዳመላከቱት በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ ነው:: በመኸር በሰብል ለመሸፈን በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል:: ምርታማነቱን በሄክታር ከ32 ኩንታል ወደ 34 ኩንታል ለማድረስ ታልሞም እየተሠራ ነው:: የታቀደውን ምርት ለማሳካት ለክልሉ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 3 ሚሊዮን 94 ሺህ 372 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ዩኒየኖች ላይ ደርሷል:: 2 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱም ተገልጿል:: ለ2017/18 የምርት ዘመን ለክልሉ በቂ ምርጥ ዘር ተባዝቷል:: እስካሁንም 280 ሺህ 897 ኩንታል የዘር ብዜት እንደተሰበሰበም ተመላክቷል::

ዳይሬክተሩ አክለውም በበልግ እርሻ ልማት በዓመቱ 239 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው:: እስካሁንም 231 ሺህ 978 ሄክታር (የዕቅዱን 97 በመቶ) የሚሆነው በሰብል በመሸፈን የእንክብካቤ ሥራ እየተከናወነ  መሆኑን አቅርበዋል::

 

ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት እንዲሁም ከተረጅነት ለመላቀቅ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 9 ነጥብ 4 ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው:: እስካሁን ባለው መረጃ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ገልፀዋል::

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ በገጠር ክላስተር ተቋማት በዋና ዋና ዘርፎች (በግብርናው ዘርፍ፣ በመስኖ አውታር ግንባታ፣ በውኃና ኢነርጂ፣ በማዕድን ልማት ዘርፍ፣ በመንገድ ፕሮጀክት ሥራዎች እና በአካባቢ ጥበቃ ተግባራት) ለ366 ሺህ 600 ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ለውይይት በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመላክቷል::

 

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ/ር) ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት ተቋሙ ከተቋቋመ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን አውጥቷል:: ኢንስቲቲዩቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሰብል ብቻ 173 የሚሆኑ በምርምር የተገኙ የሰብል ዝርያዎች ላይ ማሻሻያ በማድረግ  ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ገልፀዋል:: ኢንስቲቲዩቱ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ፣ ማላመድ፣ ማስተዋወቅ እና ለተጠቃሚዎች ማድረስ፣ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማቅረብ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ማመንጨት፣ የመነሻ ዘሮችን ለአባዥ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ማድረስ፣ ፈጥነው የሚደርሱ፣ የአፈር አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ፣ በንጥረነገር ይዘታቸው የተሻሉ እና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ እየሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል:: ምርምር ሂደት መሆኑን ያስረዱት ዳይሬክተሩ  በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል:: በዚህም 584 የምርምር አጀንዳዎች ተነድፈው በተለያዩ ሥነ ምህዳሮች ላይ እየተሠራ መሆኑን እና በርካታ ተመራማሪዎችም እየሠሩባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል:: በዚህ ዓመትም ወደ 111 የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች ይፈልቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል::

 

የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ማስፋፊያ ፅሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳዊት ገዳሙ እንዳሉት የአማራ ክልል ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ነው:: ሆኖም በክልሉ ካለው ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር አኳያ በስጋ፣ በወተት እና በእንቁላል ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ አብራርተዋል:: የእንስሳት ሃብቱን ለማዘመን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ከእንስሳት መኖ፣ ጤና፣ ዝርያ ማሻሻል፣ መሠረተ ልማት፣ የገበያ ትስስር፣ ኋላ ቀር እና ልማዳዊ የአረባብ ዘዴ ዘርፉን ከፈተኑት መሠረታዊ ችግሮች መካከል ናቸው:: በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል:: ከእነዚህ ተግባራት መካከልም የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል አንዱ ነው:: አርቢዎች ከአካባቢ ዝርያ እየወጡ የተሻለ ወተት ሊሰጡ የሚችሉ የወተት ላም ዝርያዎችን እንዲያረቡ እየተደረገ ነው:: የተሻለ የእንቁላል ምርት የሚሰጡ ዶሮዎችን በማርባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል::

 

ባለፉት ወራት የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ቴክኖሎጂ (ማሽን) እጥረት ከፍተኛ ችግር መሆኑን አንስተዋል:: በመሆኑም በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ለመሥራት ታቅዷል ብለዋል:: ሌላው በችግር ያነሱት ከዶሮ ሃብት ልማት ጋር በተያያዘ ነው:: የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት አብዛኛው የሚቀርበው ከ “ኢትዮ ቺክን” ሲሆን ከሌላ ቦታ አጓጉዞ ለማምጣት በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ጫና ማሳደሩን አመላክተዋል::

 

በሌላ በኩል የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ/ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 57 ነባር እና 53 አዲስ በድምሩ 110 የመስኖ ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራ ተከናውኗል ብለዋል:: ከእነዚህ ውስጥ በበጀት ዓመቱ 82 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ 114 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን ኢንጂነሩ ተናግረዋል:: አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እና ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማስጀመርም ተችሏል:: የተገነቡ የመስኖ ተቋማት ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ለኅብረተሰቡ ባለቤትነት የማስተላለፍ ሥራ መሠራቱም ተብራርቷል::

አፈፃፀሙ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ቢሆንም በክልሉ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ሳይገቡ መቅረታቸው ተገልጿል:: እነዚህን ግንባታዎች ወደ ሥራ ለማስገባት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል:: በሦስቱ ሩብ ዓመት ሁሉንም የመስኖ ፕሮጀክቶች መገንባት አለመቻሉ በውስንነት ተነስቷል:: የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች በወንዝ እና ሸለቆ ውስጥ በመሆናቸው ከጸጥታ አንጻር አመቺ አለመሆኑ፣ የነዳጅ አቅርቦት ችግር፣ የመንገድ ተደራሽነት ችግር እና በሙያው የተማሩ የሰው ኃይል እጥረት ለሥራው መጓተት እንደ ችግር ተነስቷል:: በቀጣይ በፌደራል መንግሥት የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑትን እንዲሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አመላክተዋል::

 

በውይይት መድረኩ የክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በስፋት በተወያዮች ተነስቷል:: ግጭቱ የሰዎችን ህይወት ከመንጠቅ ባሻገር በተቋማት ሠራተኞች እና በተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱ፣ ዜጎች በሰላም ተንቀሳቅሰው ሰርቶ መብላት  አለመቻል፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሶ መሸጥ አለመቻሉ እና የሚፈልገውን ግብዓት በፈለገው ጊዜ እና መጠን እንዳያገኝ እንቅፋት መሆኑ፣ የነዳጅ እጥረት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተነስተዋል:: ሆኖም ተሳታፊዎቹ እንደገለፁት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት ፈታኝ ቢያደርገውም ፈተናዎችን ተጋፍጦ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን  አመላክተዋል::

 

በውይይት መድረኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሥራዎች ሲከናወኑ የተወሰዱ ትምህርቶች እና ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተቋማት ግንባታ፣ ሠራተኞን በስልጠና፣ በአመለካከት እና በክህሎት ብቁ ማድረግ ላይ ምን እንደተከናወነ እንዲሁም በቀሪ ሁለት ወራት ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር እና በመረባረብ የጎደሉትን በመሙላት የዓመቱን ዕቅድ ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ተደርጓል:: “የቀረበው ሪፖርት መረጃ የተለዋወጥንበት፣ ሥራዎች በምን ሁኔታ እንዳሉ የገመገምንበት፣ ምን እንደተሠራ፣ ምን የቀረ ሥራ እንዳለ የለየንበት ነው” ብለዋል:: በውይይቱ ዝቅተኛ አፈፃፀም የታየባቸው ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አቅጣጫ የተቀመጠበትም ነው:: በውይይቱ በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም  ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ ተጠናቋል::

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here