ከአራት ወራት በፊት ነው፤ ወደ ገበያ እያቀናሁ ባለሁበት ወቅት ታክሲ ውስጥ አብረውኝ ከሚጓዙ ተሳፋሪዎች መካከል በጀርባቸው በኬሻ ቋጠሮ ያዘሉ እድሜያቸው በግምት ከ55 እስከ 60 የሚሆኑ ሴት አርሶ አደር ከጎኔ ተቀምጠዋል:: አርሶ አደር ዘመዶቼን ሳገኝ የማነሳውን ጥያቄ እርሳቸውንም መጠየቅ ጀመርሁ:: የመጡበትን አካባቢ፣ የአዝመራውን እና የሰላሙን ሁኔታ እየጠየቅሁ ጉዟችንን ቀጠልን:: በመሀልም “የዘንድሮ ምርት ተባይ ተጫወተበት እንጂ ጥሩ ነበር!” አሉኝ:: ነገሩን ካነሱት አይቀር በዚህ ጉዳይ ላይ ዘገባ መሥራት ስለምፈልግ በሚልም ስለ ፀረ ተባይ እና ፀረ አረም ኬሚካል አጠቃቀማቸው ጠየቅኋቸው:: እሳቸውም ኬሚካሉን ከአዝርዕት ጀምሮ ለገበያ እስከሚያቀርቡበት ጊዜ ድረስ እንደሚጠቀሙ ነገሩኝ::
በተለይ ምርቱን ሰብስበው በጎተራ ካስቀመጡ በኋላ እስኪሸጥ አይጥ እዳይበላባቸው እና እንዳይነቅዝ የሚወስዱት መፍትሔ ከነከነኝ:: እሳቸው እንዳሉኝ በክኒን መልክ የተዘጋጁ የአይጥ መርዞችን በጎተራ ከገባው እህል ውስጥ እንዲሁም የሚነቅዘውን ደግሞ በኬሚካል አሽተው እንደሚያስቀምጡት ነገሩኝ:: እኔም እንዴት እንደዚህ ታደርጋላችሁ? የሚያደርጉት ነገር ለጤና ጎጂ ስለሆነ እንደዚህ ማድረግ የለብዎትም አልኋቸው:: “የከተሜ ሰው አጥባችሁ አይደል የምትጠቀሙት” የሚል መልስ ሰጡኝ:: ከእሳቸው ያገኘሁትን መልስ እያብሰለሰልሁ ከገበያው ደረስን እና ተሰናብቻቸው ወደ ሸመታዬ ገባሁ::
ፀረ ተባይ እና ፀረ አረም ኬሚካሎች በሰው እና በእንስሳት ጤና እንዲሁም በሥነ ምሕዳር ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት በመገናኛ ብዙኃን፣ በተለያዩ መድረኮች በሚቀርቡ ጥናቶች ይደመጣል:: በዚህ ጉዳይ ላይ በአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አበባው አባይነህ (ዶ/ር) “ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በአካባቢ እና በማኅበረሰብ ላይ የሚያስከትሉት የጤና ጠንቅ” በሚል በፎገራ ወረዳ የተሠራ የጥናት ውጤት ይፋ አድርገዋል:: ዳይሬክተሩ በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች በሰው እና በእንስሳት ጤና እንዲሁም በአካባቢው ሥነ-ምሕዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ነው::
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ፀረ ተባይ ኬሚካል ማለት በእጽዋት፣ በእንስሳት እና በሰብል ላይ የሚፈጠሩ አረሞችን እና ተባዮችን የሚያጠፋ የኬሚካል አይነቶች ናቸው:: ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ምርት እና ምርታማነትን ከሚጨምሩ የግብርና ግብዓቶች ውስጥ ይመደባሉ:: ሆኖም በአጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት በሰው ልጅ ጤና እና በሥነ- ምሕዳር ላይ ያስከትላሉ:: ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ የሚውሉት ሰብሎች (እህል) እንዳይበላሹ ባሉበት ለማቆየት ወይም ረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ነው::
ተመራማሪው በጥናታቸው እንዳረጋገጡት በፎገራ ወረዳ ሰብሎች በፀረ ተባይ ኬሚካል በሁለት ሁኔታ ይረጫሉ፤ የመጀመሪያው ሰብሉ ማሳ ላይ እያለ ሲሆን ሁለተኛው ምርቱ በማከማቻ (ጎተራ) ውስጥ ሲቀመጥ ነው:: በስፋት ግን ኬሚካሉ የሚረጨው ሰብሉ ማሳ ላይ መብቀል ከጀመረበት እስከሚሰበሰብበት ድረስ ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ ነው:: ከዚያም ወደ ማከማቻ ወይም ወደ ጎተራ ለማስቀመጥም በኬሚካል ይታሻል:: በዚህም በአንድ የምርት ዘመን ከአንድ ጊዜ እስከ 26 ጊዜ የሚረጭ ሰብል መኖሩን አረጋግጠዋል:: ለአብነትም ቀይ ሽንኩርት ከተተከለ ጀምሮ ለምግብነት እስኪበቃ ድረስ 11 ጊዜ የኬሚካል ርጭት ይካሄድበታል::
“ጥናቴ ያተኮረው በአብዛኛው በፎገራ ወረዳ ያሉ አርሶ አደሮች እና ምርቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ምን ያህል ስለ ፀረ ተባይ መድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት ያውቃሉ? ምን ያህል የፀረ ተባይ ኬሚካል በአካባቢው እንዳሉስ ያውቃሉ? የሚለውን ያጠቃልላል” የሚሉት ጥናት አድራጊው፤ የአርሶ አደሮቹ የፀረ ተባይ እና አረም የኬሚካል አጠቃቀም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሊጎዳ በሚችል መልኩ እንደሚያከናውኑ ነው በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን የገለጹት:: ለአብነት አርሶ አደሮች የፀረ ተባይ ኬሚካሉን የሚበጠብጡትም ሆነ ማሳቸውን ረጭተው ሲጨርሱም የሚያስወግዱት በዘፈቀደ ነው:: መርጫውን በመስኖ ውኃ ላይ፣ በማሳዎቻቸው እና መሬቱ ላይ እነደሚያስወግዱት ነው የጠቆሙት:: እሳቸው እንደሚሉት አርሶ አደሮቹ ለመጠጥ እና በመስኖ ውኃ ላይ ቀጥታ ግንኙነት ባለው መንገድ ነው የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን እየተጠቀሙ የሚገኙት:: በዘፈቀደ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ሲያስወግዱም ሆነ ሲጠቀመሙም ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በአካባቢው ያለውን ውኃ ሊጠጡ ይችላሉ፤ ምግብም ሊበሰልበት ይችላል:: ይህም በሥነ-ምሕዳር ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል::
“አርሶ አደሮች ማላታይንን እንዲጠቀሙ የተፈቀደላቸው አምስት በመቶ ብቻ ቢሆንም 50 በመቶ ድረስ እንደሚጠቀሙ በጥናት አረጋግጫለሁ:: ለጤና ጎጅ መሆኑን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ቲማቲም እና ጫት ላይ ከአረም እና ተባይ ማጥፊያ ባሻገር ምርትን ያፋፋል፣ እንዲያንጸባርቅ ያደርጋል በሚል በዘፈቀደ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውጪ ይጠቀማሉ” በማለት በግንዛቤ እጥረት እና በግዴለሽነት ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል::
በፎጋራ ወረዳ ሦስት ጊዜ ምርት እንደሚመረት የገለጹት ጥናት አድራጊው በአንድ ማሳ ላይ ከሰኔ ጀምሮ ሩዝ፣ ጓያ ወይም ሽምብራ ይዘራበታል:: በመቀጠል ደግሞ ማሳው በአትክልት ይሸፈናል:: በዚህም በአንድ ዓመት ብቻ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ 28 ኪሎ ግራም ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ይውላል:: ይህ ሁኔታም በሰው ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ነው የገለፁት:: የሚያስከትለው ጉዳትም አጣዳፊ ወይም የዕድሜ ልክ ጠንቅ ሊሆን ይችላል::
በአካባቢው የሚመረቱት ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ እና ጥቅል ጎመን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመርተው ለተጠቃሚዎች የሚደርሱ ናቸው:: ሆኖም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ በተለያዩ ኬሚካሎች በተደጋጋሚ ርጭት እንደሚደረግባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል:: በመሆኑም በውስጣቸው የፀረ ተባይ ኬሚካል ቅሪቶች ስላሏቸው ጉዳታቸው ከፍተኛ ነው::
አርሶ አደሩ የኬሚካል ርጭቱን የሚያከናውነው በባለሙያ እገዛ አይደለም:: የአካባቢው አርሶ አደሮች የተፈቀደውንም የተከለከለውንም ነው ማሳቸውን የሚረጩት:: አበባው አባይነህ ዶ/ር በአካባቢው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችን ጠይቀው አገኘሁት ባሉት መልስም አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያው የሚሰጠውን ሙያዊ ምክር ከመስማት ይልቅ አዋሳኝ የሆነውን አርሶ አደር በመጠየቅ ከእሱ ተሞክሮ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ነው ያረጋገጡት:: የባለሙያ ምክር ባለመቀበላቸውም እንዲሁም መጀመሪያ ላይ የተጠቀሙት ፀረ ተባይ ኬሚካል ውጤት ካላሳያቸው ሌላ ኬሚካል ይጠቀማሉ፣ ሁለተኛውም ተባዩን ካላጠፋላቸው ሦስተኛ ሌላ ኬሚካል ይጠቀማሉ:: ይህም የሰውን ልጅ ጤና ከመጉዳት ባለፈ ሥነ- ምሕዳሩን በከፍተኛ ሁኔታ በመጉዳት ምርት እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ነው ጥናት አድራጊው ያሳወቁት::
እንዲሁም ምን ያህል ኬሚካል ለየትኛው ሰብል ያስፈልጋል የሚለውንም በውል ለይተው አለማወቃቸውም የጉዳቱን መጠን አሳሳቢ ያደርገዋል:: አርሶ አደሮቹ ኬሚካል የሚረጩት በክላስተር ስላልሆነ የጎረቤት ማሳ ላይ ያለ ተባይ ተመልሶ ወደተረጨው ማሳ ሊዛመት ስለሚችል ማሳው በተደጋጋሚ የመረጨት አጋጣሚው ከፍተኛ ነው:: በተጨማሪም የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ፀረ ተባይ እና አረም ኬሚካሎችን እንደሚጠቀሙ ነው የጠቆሙት:: ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት እና ልቅ የሆነ በባለሙያ ያልታገዘ የኬሚካል አጠቃቀም እንደሚተገብሩም ነው በጥናታቸው የደረሱበት:: ይህ በመሆኑም በተጠቃሚው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ነው የተናሩት::
በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ በላይ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ተመዝግበው ፈቃድ አግኝተው ጥቅም ላይ የሚውሉ እንዳሉ የተናገሩት ተመራማሪው ተመዘገቡ ማለት ጉዳት የላቸውም ማለት እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል:: ከእነዚህ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከተፈቀዱ ኬሚካሎች መካከልም 58 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያደርሱ ሆነው እንዳገኟቸው ነው ያስታወቁት::
በኢትዮጵያ የተፈቀዱ በሌሎች ሀገራት የተከለከሉ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ በጥናታቸው አረጋግጠዋል:: ስለዚህ ተፈቀዱ ማለት ጉዳት አያደርሱም ማለት እንዳልሆነ ነው ያስገነዘቡት:: ጥናት ባደረጉበት የፎገራ ወረዳም 78 የሚደርሱ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ ነው በዳሰሳ ጥናታቸው ያረጋገጡት::
የፀረ ተባይ እና ኬሚካል አጠቃቀማችን ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል:: የሚያደርሱት ጉዳቶችም ከፍተኛ በመሆኑ የጤናው ዘርፍ ለሌሎች በሽታዎች ማለትም ለወባ፣ ለኮሌራ፣ ለኤምፖክስ… ለመሳሰሉት ትኩረት እንደሚሰጠው እና ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርገው ሁሉ የፀረ ተባይ ኬሚካሎች የሚያደርሱት የጤና እክል አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት::
“ከምንራብ እየበላን እንሙት“ የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ያብራሩት ተመራማሪው፤ “ሆኖም ይህ አባባል ትክክል አይደለም፤ ጉዳቱ ተፈጥሮንም ጭምር ስለሚያሳጣ ትውልድ ተሻጋሪ ነው፤ በአንድ ትውልድ ብቻ ሊገታ አይችልም:: እስካሁን ያደረሰው ጉዳት ይበቃል! ትኩረት ያሻል” ብለዋል:: ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ፈንገሶችን፣ ነፍሳትን፣ አረሞችን እና ወፎችን የሚያጠፉ ናቸው:: ሆኖም አርሶ አደሮች የትኛው ለየትኛው ይውላል የሚለውን በውል ለይተው ስለማያውቁ አንድ ሰብል ላይ በተደጋጋሚ የተለያዩ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ::
አበባው አባይነህ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በርካታ የጤና እክሎችን የሚያደርሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በብዛት የሚስተዋሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ማስከተል ነው:: ካንሰር፣ መካንነት፣ በመራቢያ አካላት ላይ ጉዳት፣ የጽንስ ማጨናገፍ፣ የአዕምሮ ዘገምተኝነት፣ ቁጡ እና ነጭናጫ መሆን፣ ጤናማ የፅንስ አፈጣጠር አለመኖርም ፀረ ተባይ ኬሚካልን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ በባለመዋሉ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ናቸው::
ሳይንስ ዳይሬክት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው (sciencedirect.com) ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች በሰዎች ጤና ላይ የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት ከፍተኛ ነው:: የአልዛይመር (የመርሳት) እና የፓርኪንሰን (ከነርቭ ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚከሰት) በሽታዎች ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች በነርቭ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የሚመጡ በጣም የተለመዱ በሽታዎች እንደሆኑ በጥናቶች ተረጋግጠዋል:: ለፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ለረጅም ጊዜ መጋለጥ የአንጎል ጉዳት ያስከትላል:: በቅድመ ወሊድ እና በድህረ ወሊድ ጊዜ ለፀረ ተባይ መድኃኒቶች የተጋለጡ ሕጻናት የማገናዘብ ችሎታቸው ያንሳል:: እንዲሁም “ኦቲስቲክ ሲንድሮም” (የአዕምሮ ዝግመት) ያዳብራሉ ሲል ጥናቱ አመላክቷል።
ታዲያ አበባው (ዶ/ር ) በጥናታቸው ላገኙት ችግር ያስቀመጡት መፍትሔ የተሰበሰበው እህል እንዳይበላሽ ተገቢ የሆነ የምግብ ሰብል ማከማቻ ከረጢት ማዘጋጀት፣ ስጋም ይሁን አትክልትን ስንመገብ አብስለን መጠቀም፣ ድንች እና ቲማቲም የመሳሰሉትን ልጦ መመገብን ነው:: አትክልቶችን በደንብ በተደጋጋሚ ማጠብ፣ አርሶ አደሮች ከረጩት በኋላ ወዲያው ለምግብነት አለማዋል፣ እንዲሁም ለተጠቃሚውም አለማድረስ፣ ተጠቃሚዎችም የገዟቸውን አትክልቶች እንዳመጧቸው ባይመገቧቸው በመፍትሔነት ጠቁመዋል::
በተጨማሪም አየር ከሚያገኙበት ቦታ ላይ በማስቀመጥ እንዲናፈሱ ማድረግ፣ ፍሪጅ ውስጥ አለማስቀመጥ፣ ዋል አደር አድርጎ አብስሎ መመገብ፣ ጥራጥሬ እና ሌሎች እህሎችን በመኸር ወቅት መሸመት ለአብነትም አንድ ሰው በቆሎ የሚገዛ ከሆነ ከመጋቢት ወር በፊት መግዛት (ምክንያቱም ከመጋቢት በኋላ እንዳይነቅዝ በሚል በፀረ ተባይ ኬሚካል ስለሚታሽ)፣ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፀረ ተባይ ኬሚካል መፈተሻ መሳሪያ ኖሮት በገበያ ላይ ያሉ ምግቦችን የኬሚካል ይዘታቸውን ቢፈትሽ፣ ኬሚካሎች የሚያደርሱት ጉዳት ከሚሰጡት ጥቅም የሚያንስ ከሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ባይገቡ እንደሚመረጥ አሳስበዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ተባዩን ብቻ ለይተው የሚያጠፉ፣ ሲረጩ በአፈር እና በውኃ ውስጥ ብዙ ጊዜ የማይቆዩ፣ የጉዳት መጠናቸው ከፍተኛ ከሆነ ደግሞ ከአጠቃቀም ሰንሰለታቸው እንዲወገዱ ማድረግ ይገባል:: ፀረ ተባይ ኬሚካሎች የሚያደርሱትን ችግር ለማስቀረት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ተፈትሸው ቢገቡ መልካም መሆኑን አጥኝው አስገንዝበዋል:: እንደ እርሳቸው ገለጻ ፀረ ተባይ እና አረም ኬሚካልን ካደጉት እስከ ታዳጊ ሀገራት ድረስ ይጠቀማሉ:: ልዩነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የአጠቃቀም ችግር መኖሩ ነው:: በቀጣይ በሕጉ መሠረት ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገበት መጠቀም ቢቻል፣ የግንዛቤ ፈጠራ በሰፊው ቢከናወን፣ የኬሚካል አጠቃቀም ሕጎች ተግባራዊ ቢደረጉ እና በአፋጣኝ የማስተካከያ ርምጃ ቢወሰድ ተገቢ እንደሆነም ነው የጠቆሙት::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም