ፅዳት እና ውበትን የመንግሥት እዳ ያደረገው ማነው?

0
16

ፅድት ማለትን የሚጠላ ማነው? መዋብንስ የማይሻ አለን? ፅዳት የጤናማነት መሠረት በመሆኑ ህይወትን ያለመልማል፤ ታዲያ ፅዳትን ማን ይጠላል?

ውበትም ቢያንስ የዓይን ራት ነው፤ አለፍ ሲል ደግሞ ለአእምሮ ርካታን የሚሰጥ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ በእነዚህ እና መሠል ጥቅሞቻቸው ምክንያትም ጤናማ አስተሳሰብ ያለው የሰው ዘር ሁሉ ይፈልጋቸዋል፡፡

ፅዳት እና ውበት ሲሟሉ ከሚያስገኙልን ጥቅም በላይ ሲጓደሉ የሚያስከፍሉን ዋጋ መራራነትም ተግባሩን ከመንግሥት አልፎ የዜጐች ሁሉ ማህበራዊ ሀላፊነት እና ግዴታ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

የግል እና የአካባቢ ውበት እና ንፅህና መጓደል እንደ ወባ፣ ተስቦ እና መሰል ተላላፊ በሽታዎችን በመፍጠር ከግለሰብ አልፎ ለበርካታ ህዝብ እልቂት መንስኤ እየሆነ መገኘቱ ደግሞ ዜጐች መኖሪያ እና መስሪያ ቤቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸውንም  ጭምር የማፅዳት ሀላፊነት እና ግዴታም እንዳለባቸው የሚደነግግ ሕግ ተቀርፆላቸዋል፡፡

በዚህ መንግድ ዜጐች የግል እና የአካባቢያቸውን ውበት እና ፅዳት እንዲጠብቁ ህግ ቢያዝም አሁን አሁን ግን በተለይ በከተሞች የፅዳት እና ውበት ተግባር ለመንግሥት ብቻ የተተወ እስኪመስል የዜጐችን ቸልተኝነት፣ ግዴለሽነት እና ጥፋት ጭምር እያስተዋልን እንገኛለን፡፡

በዛሬው የትዝብት መጣጥፌም በመዲናችን ባሕር ዳር ከተማ የታዘብኳቸውን ጉልህ ህፀፆች እንደ አብነት በማንሳት ችግሮቹን በሦስት ከፍዬ መፍትሔ ከምላቸው ሀሳቦቼ ጋር ለማመላከት እሞክራለሁ፡፡

ከሦስቱ አበይት ችግሮች የመጀመሪያው ከግል እና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ አንፃር እንደማህበረሰብ ከአስተሳሰብ ጀምሮ ለውጥ የሚያስፈልገን መሆኑ ነው፡፡ ከግል ንፅህና ብንነሳ አንዳንዱ ሰው ልብሱን የሚያጥበውም ሆነ ገላውን የሚታጠበው ለራሱ ጤና እና ሰላም ሲል መሆኑ ቀርቶ ሌሎችን እንዳያስቀይም ሲያስመስለው ብዙ ጊዜ ታዝቤአለሁ፣ የቆሸሸ ጃኬቱን ወይም ጋቢውን ገልብጦ የሚለብስ ሁሉ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፤ ሰው እንዳያይበት የደበቀውን ቆሻሻ ይበልጥ ወደገላው አስጠግቶታልና!

“ነጭ ሸሚዝ አልገዛም፤ እድፍ አይችልም፤ ጥቁሩን ስጠኝ” የሚሉስ ገጥመዋችሁ አያቁም? ታዲያ ከእድፍ ጋር ብዙ ቀን አብሮ ለመሰንበት አስቦ እና አቅዶ መኖር የአስተሳሰብ ለውጥ አያስፈልገውም ትላላችሁ?

ከመመገባችን በፊት ጣቶቻችንን እንደነገሩ በውኃ ነካክተን (አንዳንዴ ቀኝ እጅን ብቻ) ከተመገብን በኋላ በሳሙና መታጠብስ ስንነካካ የዋልነውን ጀርም ረስተን የምግቡን ቅባት ለማላቀቅ መጨነቅ ከጥቅም አንፃር አልተገለባበጠም? በፅዳት ጉድለት አስቀያሚ ጠረን የተሸከመ ካልሲ እና ጫማ አድርጐ 15 ሰው በሚታጨቅበት ታክሲ መሳፈርስ በወንጀል ባያስጠይቅ እንኳ ነውርነቱ እንዴት ይረሳል?

የግል ንፅህና ችግር ዋነኛ ክፋቱ ደግሞ በግለሰቡ ላይ የሚያስከትለው እንደ ታይፈስ አይነት በሽታ ለሌሎች ንፁሀንም የሚተላለፍ መሆኑ ነውና በዚህ በሰለጠነው 21ኛው ክፍለ ዘመን እንደሚኖር ዜጋ ለግል ንፅህናችን የምንሰጠው ትኩረት መቀየር እና መዘመን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

ሁለተኛ ችግር ያልኩት ደግሞ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችንን ነው፡፡ በከተማችን ከየአካባቢው የሚሰበሰብን ቆሻሻ ለማስወገድ የከተማ አስተዳደሩ የዘረጋው መዋቅር ተግባሩን በአግባቡ እየተወጣ ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ ግን አብዛኛው ኗሪ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡

ለአነሳሁት ጭብጥ አብነት ለመጥቀስ ያህል አብዛኛው የከተማዋ ነጋዴ ሸቀጥ የጠቀለለበትን ተረፈ ምርት /ቅራቅንቦ/ ሁሉ ጠርጐ የሚጥለው ከድርጅቱ ፊት ለፊት ከሚገኝ አስፋልት ወይም የእግረኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ ልብስ ሰፊው ሁሉ ቁርጥራጭ ጨርቁን የሚበትነው አስፋልት ላይ ነው፤ ለአብነት ያህል የቀድሞው መናኸሪያ ፊት ለፊት በሚገኘው  አስፋልት እሁድ ቀን ብትወጡ አስፋልቱ በጨፌ ሥር ቁራጭ፣ በበቆሎ እሸት ሸልቃቂ፣ በሸንኮራ አገዳ ልጣጭና ልማጭ፣ በቅቅል ድንች ልጣጭ፣ ካርቱን፣ ኘላስቲክ እና መሰል ትርኪ ምርኪ ተሞልቶ ነው የምታገኙት፤ ከእሁድ ውጪ ቆሻሻው የሚቀንሰውም ጧት የከተማ አስተዳደሩ የፅዳት ባለሙያዎች ስለሚያፀዱት ነው፡፡ ግን እስከመቼ? ተጠቅመን የመንጥለውን ቆሻሻ በጆንያ አቆይቶ ከተማ አስተዳደሩ ለዘረጋው መዋቅር ማስረከብ ማንን ገደለ?

ይኼ የቆሻሻ አወጋገድ ችግር የነጋዴው ብቻም አይደል፡፡ ወደየሰፈሩ ጐራ ስንልም የባሰ እንጂ የተሻለ አናይም፡፡ በተለይ በዓመት በዓል ሰሞን ደግሞ ይለያል፡፡ አብዛኛው ኗሪ የዶሮ እጣቢውኔ፣ የበግ ቆዳና ጭንቅላትን፣ አጥንትና ፈርሱን ጭምር ከመቅበር  ይልቅ ከግቢው አውጥቶ በየ ጥጋጥጉ እና በየፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ መወሸቅ ነው የሚቀናው፤ በፌስታልና ጆንያ እየጠቀለለ በየመንገድ ዳር የሚጥለው ይኽው የእንስሳት ቅሪት ታዲያ ከበዓሉ ማግሥት እና ሳልስት ጀምሮ ለሳምንታት ያህል ክርፋቱ በቃላት የሚገለፅ ባለመሆኑ በተለይ የመተንፈሻ አካል ህመም እና አስም ላለባቸው ሰዎች ምናለ አመትባል ባይምጣ እስከማለት አንገፍግፏቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱን ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ እና ለህዝብ ደንታቢስነትን የሚያሳይ ድርጊት የምንታቀበው መቼ ነው? ጉድጓድ ቆፍሮ በመቅበር ሊወገድ የሚችልን ችግር ለህዝብ ማሸከም ሰውኛ ነው ትላላችሁ?

የአወጋገድን ነገር ካነሳን የሰለጠነው ዓለም ብቻ ሳይሆን እዚሁ እኛው ክልል እንኳ በአዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ቆሻሻን ወደ ማገዶነት እና ወደ ማዳበሪያነት የቀየሩ በርካታ ግለሰቦች እና ማህበራት አሉን፡፡ ቢቻለን ወደ ዚህ ደረጃ ብንሸጋገር መልካም ነው፤ ቢያንስ ግን ህዝብን በሚጐዳ መልኩ ገመናን የትም መጣል ለዚህ ዘመን ትውልድ አይመጥንምና ልንታቀብ ይገባል እላለሁ፡፡

ሦስተኛ ችግር ነው ወዳልኩት ስገባ አካባቢን በማስዋብ ተግባር ላይ ያለንን እጥረት አነሳለሁ፡፡ አሁንም በማሳያነት ከመረጥናት ባሕር ዳር ከተማችንን  “ውብ” ካስባሏት ሀብቶቿ አንዱ ዘንባባ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ከዛሬ 70 እና 80 ዓመታት በፊት ዘንባባዎቹን ከአስመራ አስመጥተው ላስተከሉት ፊትአውራሪ ሀበተማሪያም እና ባልደረቦቻቸው ምስጋና ይግባቸውና ዘንባባ የከተማችን የውበት መገለጫ ሆኗል፡፡

ይሁንና ዘንባባዎቹ በአሁኑ ወቅት በእድሜአቸው መግፋት ሳቢያ ጥንቃቄ የተሞላበት ክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ  ማንችንም የተረዳን አይመስለኝም፡፡ አንዳንዶቹ ግንዳቸው ተቦርቡሯል፤ ብዙዎቹ ቅርንጫፎቻቸው ከቆሙበት የዘንባባው አናት ላይ በርካታ  መወገድ የሚገባቸው ያረጁ ቅርፊቶች ተከማችቶባቸዋል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተቀጥላ የሚባሉ የዛፍ ዝርያዎች በቅለውባቸዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ዘንባባዎቹን እንዲወድቁ ማድረጋቸው አያጠያይቅም፡፡ ከአሁን በፊትም ናቪጋጣና ፊት ለፊት የነበረ አንድ ዘንባባ ባጃጅ ላይ ወድቆ የመመረቂያ ልብስ ለመግዛት ወደ ከተማ የወጡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመግደሉ ያደረሰብንን መሪሪ ሀዘን መዘንጋት ተገቢ አይሆንም፡፡ “ብልህ ከሌሎች ይማራል፤ ሰነፍ ግን ከራሱ ስህተት እንኳ አይማርም” ይባላልና ዘንባባዎቻችንን በመጠበቅ ለአካባቢ ውበት ትኩረት መስጠትን እንማር፡፡

ለምሳሌ ያህል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርና ፋኩልቲ የዕፅዋት ሳይንስ ምሁራን ዘንባባዎቹን በመንከባከብ የማህበረሰብ አገልግሎት የማበርከት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግሥት የኮሪደር ልማት በሚል የጀመረውን ሥራ ተከትሎ እየተከላቸው ያሉትን ችግኞችም ሌሊት ሌሊት ስድ በሚለቀቁ እንስሳት ሲበሉ እያየን ነውና መንግሥት ሲሰራ ህዝብ አፍራሽ ከሆነ አያቀባበርም እና ልናስብበት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የከተሞች ፅዳት እና ውበት ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ  የሚተው እዳ አይደለም፡፡ ፅዳት እና ውበት ሲኖር ተጠቃሚው ህዝብ የመሆኑን ያህል ጠባቂውም ተንከባካቢውም ህዝብ ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲያምርብን ብቻ ሳይሆን በንፅህና ጉድለት እንዳናልቅም ነውና “ልብ ያለው ልብ ይበል!” የትዝብቴ መቋጫ ነው፡፡

 

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018  ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here