ፆታዊ ጥቃት

0
194

“ለፆታ ጥቃት” ከሕግ አንጻር የሚሰጡት ትርጓሜዎች /ፍቺዎች/ ከሀገር  ሀገር ቢለያዩም  ድርጊቱ  በሰዎች ላይ አካላዊ ፣ ወሲባዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን የሚያስከትል እና ጾታን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም የኀይል ድርጊት ነው:: ድርጊቱ በልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት፣ በሥጋ ዘመዶች መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ አስገድዶ መድፈር እንዲሁም ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ለምሳሌ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች ወይም የሃይማኖት መሪዎች አምነው የቀረቧቸውን ሰዎች የፆታ መጠቀሚያ ማድረጋቸው በዚህ ድርጊት ውስጥ ሊካተት ይችላል።

በንግግርም ይሁን በድርጊት የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ጉዳዩን ለሌላ ሰው እንዳይናገሩ ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ በየዓመቱ ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የፆታ ጥቃት ደርሶባቸዋል:: ከእነዚህ መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት ከ12 እስከ 18 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ባጠቃላይ ሲገለፅ ግን ጾታዊ ጥቃት ካለግለሰቡ ስምምነት እና ፈቃድ ውጪ በግለሰቡ ላይ የሚደረግ ጥቃት ነው:: በተጨማረም በሕይወት አጋር፣ በትዳር ጓደኛ ወይም በቤተሰብ አባል ላይ ጾታዊ ጥቃት ማድረስ ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው::

የጾታዊ ጥቃት ዓይነቶች እና መገለጫዎች

አካላዊ ጥቃት ድብደባ ፣ጥፊ፣ ግርፋት እና በተለያዩ መሳሪያዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ያካትታል:: ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅ እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝን ያመላክታል:: ወሲባዊ ጥቃት አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋ፣ ወሲባዊ ትንኮሣ፣ በትዳር ጓደኛ የሚፈፀም ተገዶ መደፈር፣ ሴቶችን ለወሲባዊ ትንኮሳ መጠቀም የመሣሰሉት ድርጊቶችን ያጠቃልላል::

 

ጾታዊ ጥቃት በማን እና የት ይፈፀማል?

ፆታዊ ጥቃት  በቤተሰብ አባል፣ በጐረቤት፣ በጓደኛ፣ በቅርብ በሚታወቁ ሰዎች፣ በትዳር አጋር እንዲሁም ምንም ግንኙነት በሌላቸው ወይም በማያውቋቸው ግለሰቦች በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በመንገድ፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ይፈፀማል::

ጾታዊ ጥቃት የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች የአካል ጉዳት፣ ሞት፣ ፊስቱላ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን ጨምሮ የአባላዘር በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃና ከወርጃ ጋር የሚከሰት የሥነ ልቦና አለመረጋጋት፣ በወሲብ ጊዜ ሕመምን እና በወሊድ ወቅት ለአደጋ የመጋለጥ ችግሮችን ያጠቃልላል:: ስሜታዊ፣ ማሕበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ደግሞ ሐፍረት፣ ፀፀት ፣ ድብርት ፣ ድንጋጤ፣ ፍርሃት፣ ተስፋ መቆረጥ፣ ራስን መጥላት፣ አለመረጋጋት  በብቸኝነት መገለልና መድሎ፣ የአእምሮ ሕመም /ራስን ለማጥፋት ማሰብ/ ፣ በራስ ያለመተማመን እና ትምህርት ማቋረጥ የመሳሰሉት ይጠቀሣሉ::

 

ኢኮኖሚያዊ ችግሮች

ሴቶች በሚደርስባቸው ጥቃት የተነሣ ፍርሀትና አለመረጋጋት ስለሚፈጠርባቸው ራሣቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ከሥራ፣ ከትምህርት ቤትና ከመዝናኛ ራሣቸውን ያገላሉ::

በዋናነት ለጾታዊ ጥቃት አጋላጭ ከሆኑት ውስጥ  የአልኮልና የአደገኛ ሱስ ተጠቃሚ መሆንን ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና እውነታዎች በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣውን መረጃ ይጠቁማል:: መረጃው በዓለማችን ከሚገኙ ሴቶች 35 ከመቶ ያህሉ በቅርብ ጓደኞቻቸው ወይም ሌላ አካል ከፍቃዳቸው ውጪ የሆነ ጾታዊ ጥቃት በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ እንደሚፈፀምባቸው አስፍሯል::  30 ከመቶ ያህል ሴቶች ደግሞ በጓደኞቻቸው ወይም በባሎቻቸው አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል:: በዓለማችን በሴቶች ላይ ከተፈጸሙ ግድያዎች ውስጥ 38 ከመቶው የተፈጸሙት በጾታዊ ጓደኞቻቸው ወይም በባሎቻቸው ነው::

በማንኛውም ፍርድቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ወ/ሪት አፀደ አለባቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ስለሴቶች ጥቃት /አስገድዶ መድፈር እና ፆታዊ ትንኮሳ/  በዝርዝር ግልፅ ተብሎ በሕጉ የተቀመጠ ነገር  የለውም:: በሴቶች ላይ የሚፈፀም  ፆታዊ ጥቃት በወንጀል ሕግ በሚገባ ሳይተረጎም ከአንቀፅ 558 እስከ 661 በተበታተነ መልኩ ሰፍሮ ይታያል::

ባለሙያዋ እንደሚሉት ከሰፆታዊ ጥቃት ዋናው አስገድዶ መድፈር ነው፤ በሕጉም  ድርጊቱ በተለያዩ ሀገራት በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነና  የተለያዩ የቅጣት እርምጃዎችንም በጥፋት አድራጊዎች ላይ ያስተላልፋሉ።

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አስገድዶ መድፈር የፈፀመ ሰው በኢፌዲሪ በወንጀል ሕግ መቅጫ አንቀፅ 620 ንኡስ ቁጥር አንድ “ማንም ሰው የኀይል ድርጊት በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም ህሊናዋን እንድትስት ወይም በማንኛውም ሌላ መንገድ መከላከል እንዳትችል በማድረግ ከጋብቻ ውጪ አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር የግብረ ስጋ  ግንኙነት ከፈፀመ  ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

በአንቀፅ 620 ንኡስ ቁጥር ሁለት ሀ/ዕድሜው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ ሆኖ አስራ ስምንት ዓመት ባልሞላት ሴት ልጅ ላይ ሲሆን ወይም  ለ/በጥፋተኛው መሪነት፣ ቁጥጥር ወይም ሥልጣን ሥር በሆነ የመጦሪያ ቤት፣ የሕክምና፣ የትምህርት፣ የጠባይ ማረሚያ፣ የመታሠሪያ ወይም የተያዙ ሰዎች መቆያ ተቋማት ውስጥ በምትገኝ ወይም በተከሳሹ ጥበቃ ወይም በቁጥጥር ስር በምትገኝ ወይም የእሱ ጥገኛ በሆነች ሴት ላይ ሲሆን ወይም  ሐ/ በዕድሜ መግፋት፣ በአካል ወይም በአዕምሮ ሕመም፣ በመንፈስ ድክመት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የድርጊቱን ምንነት /የሚያስከትለውን ውጤት/ ለይታ ለማወቅ ወይም ለመከላከል በማትችል ሴት ላይ ሲሆን ወይም መ/ በጭካኔ ወይም  በማሰቃየት ወይም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች ህብረት ሲሆን  ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ሕጉ ደንግጎ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አስገድዶ መድፈር  አንቀፅ 620 ንኡስ አንቀፅ ሦስት ላይ እንደሰፈረው በአስገድዶ መድፈር ከባድ የአካል እና የአዕምሮ ጉዳት ወይም ሞት ካስከተለ  ቅጣቱ የዕድሜ ልክ እስራት እንደሚሆን በግልፅ አስቀምጧል። እንዲሁም   የወንጀል ሕጉ 564 የቤት ውስጥ ጥቃት  የሴት ልጅ ብልት መስፋት፣ አስገድዶ መድፈር በሴት ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃትን መስረት ያደረገ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ጥቃትን ያካትታል::

አሁን እንደምናየው ግን ፆታዊ ጥቃት በየዕለቱ ለፓሊስ ሪፓርት የሚደረገው   እየጨመረ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: ይሄ  ሲሆን  ደግሞ በጥፋተኛው ላይ ተገቢ ርምጃ ለመውሰድ   የህክምና ማስረጃዎች ፣የፓሊስ ሪፖርት ያስፈልጋሉ::ይሁን እንጅ በአብዛኛው  የተሟላ የመረጃ  የማቅረብ ክፍተት በመኖሩ የሚሰጠውን ፍርድ  አነስተኛ እያደረገ ነው:: ለአብነት ክሱ ለፍርድ ቤት ደርሶ ከፓሊስ ጀምሮ የህክምና ማስረጃ እና የአቃቢ ሕግ መረጃዎች ተቀናጅቶ አስፈላጊውን ማስረጃ አለማቅረቡ ጉዳዩ በበቂ ሁኔታ  ከፍተኛው ፍርድ እንዳይሠጥ እያደረገው  ነው::

በቀጣይም  በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት የሚደረስ ፆታዊ ትንኮሳ በሕፃናት እና ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መብዛትን መቀነስ ብሎም ማስቆም የሚቻለው የፍትሕ አካላት በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ ሳይዘገይ በመስጠት  ቅጣቱ ለሌሎችም  አስተማሪ እንዲሆን መሥራት ሲጠበቅባቸው ብቻ እንደሆነ ባለሙያዋ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ፍርድ ቤቶች በተለየ ሁኔታ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ በተለያየ መንገድ ጥቃት የሚያደርሱትን አጥፊዋች ለፍርድ አቅርበው መቅጣታቸው ከችግሩ በላይ በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚደርሰው ጥቃት ማህበረሰቡን ጭምር እንዳይጎዳ ያግዛል ያሉት ባለሙያዋ፤  ፓሊስ እና  አቃቤ ሕግ የአስገድዶ መድፈር ምርመራ ወንጆሎችን ትኩረት አድርጎ መርምሮና ክሱን አጠናክሮ ወንጀለኛውን ተገቢ ቅጣት እንዲያገኝ ተገቢውን እርምጃ ማግኘት እንደሚገባው ጠቁመዋል::

እንደ ባለሙያዋ እምነት መረጃው ሲቀርብ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ጥቃት አድራሾች ላይ ፈጣንና ተመጣጣኝ የሕግ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፤ የጸጥታ አካላት ደግሞ ችግሩ ሳይደርስ ጾታዊ ጥቃቶችን የመከላከል ሥራዎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል:: በተጨማሪም ማህበረሰቡም ቢሆን  ጾታዊ ጥቃቶች ሲደርሱ ብቻ ሳይሆን ከጅምሩ አበክሮ የመቃወም እና ማውገዝ ባህሉን በማዳበር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል:: በአሁኑ ጊዜ እንደምናየው እና እንደምንሰማው ሁኔታ  በሴቶች ላይ አሰቃቂ ጥቃት እየተፈፀመ ይገኛል:: ነገር ግን ለጉዳዩ በአብዛኛው አጥጋቢ እና ትክክለኛ ፍርድ ስለማይሰጣቸው ማህበረሰቡ እርካታ እያገኘ እንዳለሆነ ይስተዋላል:: ስለዚህ ጥፋተኞች በሕጉ በተቀመጠው አግባብ ፍትሕ እንዲገኝ ከተፈለገ ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ሊተባበር ይገባል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር 30  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here