ፆታዊ ጥቃት ለምን?

0
129

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው ጥናት ከ2019 እ.አ.አ በኋላ ያለው መረጃ እንዳመለከተው ከሦስት ሴቶች አንዷ ፆታዊ ጥቃት ይደርስባታል፤ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 34 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይደርስባቸዋል እንደ ማለት ነው::

በአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ተሳታፎ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ደስታ ፈንታ የሴቶችን ጥቃት አስመልክቶ ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተብሎ የሚገለፀው ከሰዎች ፍላጐት ውጭ ኃይልን በመጠቀም የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንደሆነ አመላክተዋል::

 

ጥናት አቅራቢዋ ጾታን መሸረት ያደረገ ጥቃት በተለይ በጦርነት ወቅት የከፋ ስለመሆኑ ጠቁመዋል:: ለአብነትም  በሰሜኑ ጦርነት ወቅት   ሕጻናት፣ ወጣቶች፣  መነኩሴዎች፣ የአልጋ ቁራኛዎች እና የአዕምሮ ችግር ያለባቸው…  ዜጎች  ተገዶ የመደፈር ጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ አመላክተዋል::

የጥቃቱ መንስኤ በዋናነነት ማኅበረሰቡ  በሴቶች እና በወንዶች መካከል የፈጠረው  የተዛባ ማኅበራዊ አመለካከት ወይም ሥርዓተ ፆታ ነው:: ታዲያ ይህንን ጥቃት ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቡ እና በቡድን የተደራጁ አካላት  በቀላሉ መብታቸውን ማስከበር በማይችሉ ሴቶች ላይ በብዛት ሲፈጽሙ ይስተዋላል::

ወ/ሮ ደስታ ፈንታ በጥናታቸው  ፆታዊ ጥቃትን በሦስት ከፍለውታል፤ የመጀመሪያው አካላዊ ጥቃትን /ድብደባ/፣ ግርፋትን፣ በአሲድ መቃጠልን እና ሲከፍ ደግሞ ግድያን ያካትታል::

ሁለተኛው የሥነ ልቦና ጥቃት የሚባለው ደግሞ ስድብ፣ ዛቻ፣ ማሸማቀቅ እና የመሳሰሉት ናቸው::   ሌላው (ሦስተኛው) ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት የሚባለው ሲሆን  ሀብትን እና መሬትን መንጠቅ፣ ንብረትን መከልከል፣ ከምርት እና ከሥራ ውጭ ማድረግ፣   ንብረት ማንቀሳቀስ መከልከልን …  ያካተተ ነው::

 

ጥናቱ እንደሚያሳየው የጾታዊ ጥቃት ሰለባ ከሚሆኑት ሕጻናት፣ ወጣቶች፣  መነኩሴዎች፣ የአልጋ ቁራኛዎች እና የአዕምሮ ችግር ያለባቸው…  ዜጎች    ውስጥ  10 ከመቶው ወሲባዊ ጥቃት፣ 21 ነጥብ ስድስት ከመቶ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም 27 ከመቶ ያህሉ አካላዊ  ጥቃቶች ይደርስባቸዋል:: በጠቅላላው ዕድሜ ክልላቸው ከ15 እስከ 49 በሚገኙ ሴቶች 25 ከመቶ አካላዊ፣ 24 ከመቶ ሥነ ልቦናዊ ፣ 12 ከመቶ   ወሲባዊ (ተገዶ መደፈር) ጥቃት እንዲሁም  ስምንት ከመቶ ደግሞ አካላዊ ድብደባ እና ወሲባዊ ጥቃት ተደጋግሞ ይፈፀምባቸዋል::

ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መንስኤ ምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ በዋናነት የሚነሳው ማኅበረሰቡ ስለ ፆታ ያለው የተዛባ አመለካከት ተንሰራፍቶ መቆየቱ እንደሆነ  ወ/ሮ ደስታ ያነሳሉ:: ለአብነትም መጥፎ ድርጊት  የፈፀመን ወንድ ጀግና፣ ተጎድታ የመጣችን ሴት አስጠቂ፣ ከፍ ብለው ሲወጡ (አለባበስን ጨምሮ ራሳቸውን ጠብቀው) ደግሞ  ማንቋሸሽ  የተለመደ ድርጊት ነው::

 

የተዛባ የማኅበረሰብ እሳቤ መኖር በተለይም “ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ” እየተባለ ሴቶች ምንም ነገር ሲሠሩ ማንቋሸሽ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ችግር መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለጥቃት ተጋላጭ ያደረጋቸው በየአካባቢው ያለውን የሠላም እጦት እና ድህነት (የኢኮኖሚ ጥገኝነት) በምክንያትነት ይነሳሉ::

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በርካታ ሪፖርት ያልተደረጉ ጥቃቶች ቢኖሩም ከአምስት ሺህ በላይ ሴቶች ፆታዊ (አስገድዶ መድፈር) ጥቃት ደርሶባቸዋል:: ከ2016 እስከ 2017 ዓ.ም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ደግሞ  ከአንድ ሺህ 324 በላይ ሕጻናትን ጨምሮ አዋቂ ሴቶች ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል::   ከነዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 159 አዋቂ ሴቶች፣ 745 ሕጻናት 22 ደግሞ ወንድ ሕጻናት ጥቃት እንደተፈፀመባቸው  በዋን ስቶፕ ሴንተር ተቋማት የተደረገው ሪፖርት ያመላክታል::

 

በአማራ ክልል ጥቃት ለሚደርስባቸው ሰዎች ጊዜያዊ የመጠለያ፣ የምገባ፣ የሥነ ልቦና፣ … አገልግሎት የሚሰጥ 17 የዋን ስቶፕ ሴንተር መኖሩን ያነሱት ወ/ሮ ደስታ ጥቃት ደርሶባቸው በማዕከሉ ከተቀመጡት ውስጥ 466 ሴቶች ተጠርጣሪ ጥቃት ፈፃሚዎች  ላይ ክስ መሥርተዋል፤ 183 አጥፊዎች ደግሞ ውሳኔ አግኝተዋል:: ከነዚህ ውስጥ 111 አጥፊዎች በፅኑ እስራት፣ 38ቱ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ስምንቱ ደግሞ በገንዘብ የተቀጡ ሲሆን 12ቱ ነፃ ወጥተዋል::  የቀሪዎቹ ክስ በሂደት ላይ  መሆኑን ነው ወ/ሮ ደስታ ያመላከቱት::

በግጭቱ መደፈራቸውን ሪፖርት ያላደረጉ መምህራንን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ ታውቆ ክስ እንዲመሠርቱ ቢጠየቁም “ዳግም ጥቃት ይደርስብናል” በሚል ስጋት ክስ መመሥረት አለመፈለጋቸው ደግሞ ፊደል ቆጥረዋል የሚባሉት ሴቶችም ጭምር በስጋት ውስጥ እንደሚኖሩ ማሳያ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የገለፁት::

 

በሕጉ በኩልም የላላ ውሳኔ መኖር፣ ምርመራ ለማድረግ  መረጃ የሚሰበሰብበት እና የሕክምና ውጤት የሚገኝበት ተቋም ተገቢውን መረጃ አለመስጠት፣ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔው ሌሎችን የማያስተምር (ውሃ የማያነሳ) መሆኑ በጥናቱ ተለይቷል::  በዚህም ለአጥፊዎች የሚሰጠው ፍርድ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት አካላት ችግራቸውን በአግባቡ የሚያካክስ  እንዳልሆነ ነው የተገለጸው::

ቢሮውም  አስፈላጊውን  አካላዊም፣ ሆነ ሥነ ልቦናዊ ሕክምና ካገኙ በኋላ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላለባቸው ከረጅ ድርጀቶች ጋር በመተባበር ወደ ገቢ ማስገኛ ሥራ ለማስገባት እንደየ አካባቢው ሁኔታ ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር በመስጠት ሥራ እንዲጀምሩ እያደረገ መሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: ችግሩ አሁን ባለው ፍጥነት እንዳይቀጥል ደግሞ ኅብረተሰቡም ቢሆን ጥቃት አድራሹን ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ፣ ለሴቶች መብት መከበር ለቆመ አካል በመተባበር እና ተገቢውን ማስረጃ በማቅረብ አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ነው ባለሙያዋ የጠየቁት::

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባሕር ዳር እና ደሴ ጽ/ቤት  ሴቶች እና ወጣቶች ዴስክ ካርዲኔተር ወ/ሮ ሃና ጆርጅ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ጾታዊ ጥቃት በአማራ ክልል ወደ መጥፋት አቅራቢያ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል:: አሁን ባለው ግጭት እና ወቅታዊ ችግር ምክንያት ግን በጣም መሥፋፋት እንደጀመረ ነው የጠቆሙት::

 

በተለይም ፆታዊ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን  ወ/ሮ ሃና አስታውሰዋል:: ለዚህም ምክንያቱ  ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው በቤት በመቀመጣቸው የተነሳ በአካባቢያቸው ለጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ መሆናቸው ነው:: የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃት እንዲስፋፋ ካደረጉት ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ፣ መጤ ልማዳዊ ድርጊት (ግብረ ሰዶምን ጨምሮ)፣ በታዳጊዎች እየተለመደ የመጣውና አላግባብ የተስፋፋው  የማሕበራዊ ሚዲያ (የሶሻል ሚዲያ) አጠቃቀም እንደሆኑ ጠቁመዋል::  የወላጆች  ልጆችን አዋዋል በአግባቡ መከታተል አለመቻል ደግሞ  ችግሩ ይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን ገልፀዋል::

በቀጣይ ወላጆች ልጆቻቸውን በየሃይማኖታቸው  በሚገባ በማስተማር ሰብዕና ግንባታ ላይ መሥራት እንደሚገባቸው ነው ወ/ሮ ሃና ያስገነዘቡት:: ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚወሰነው የፍትሕ  ውሳኔ ሂደት እና ቅጣቱ አስተማሪ እንዲሆንም ከተጎጂዎች የዕድሜ ልክ ጉዳት አንፃር ተመጣጣኝ ሆኖ መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል:: በዚህ ላይ ኅብረተሰቡ በንቅናቄ ሊሠራ ይገባል ያሉት ወ/ሮ ሃና፤ ሁሉም በየእምነቱ ከመሰባሰብ ጀምሮ በስብከት ወቅት በተለይ ለወጣቶች በአግባቡ ባሕርይን ሊለውጥ የሚችል ትምህርት እንዲሰጥም ጠይቀዋል::

 

ማናት

የሸዋሉል መንግሥቱ

የሸዋሉል መንግሥቱ ገጣሚ እና ዜማ ደራሲ ጋዜጠኛ እንዲሁም ፀሐፌ ተውኔት ነበረች::

ውልደቷ በያኔው አጠራር ምሥራቅ ሃረርጌ ጃርሶ (ኤጀርሳ ጎሮ) አካባቢ በ1937 ዓ.ም ነው:: ብዙዎች በስሟ አጠራር ዙሪያ ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ አንድም ሴት በወቅቱ በዚህ ስም የማትጠራ በመሆኑ ነው:: ልዑል የሚለው ስያሜ የሚሰጠው ለወንድ እንጂ ለሴት ባለመሆኑ ነው ብዙዎች ሲጠሯት ‹‹የሸዋልዑል መንግሥቱ›› እያሉ ሲሆን እርሷ ግን ስሟን በፅሑፍ በምታሰፍርበት ጊዜ ‹‹የሸዋሉል መንግሥቱ›› በማለት ነበር።

ትምህርቷን ተወልዳ ባደገችበት ምሥራቅ ሀረርጌ ጃርሶ (ኤጀርሳ ጎሮ) አካባቢ ሲሆን ከሥነ-ፅሁፍ ጋር የነበራት ትውውቅም ገና በ10 ዓመቷ ነበር:: የመጀመሪያው የድርሰት ሥራዋም  “የኢዮብ ትዕግስት›› የተሰኘ ድርሰቷ ሲሆን ከ 9 ዓመታት በኋላ ማለትም በ19 ዓመት እድሜዋ ጥቂት መሻሻያ ተደርጎበት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ‹‹የትያትር ጊዜ›› በተባለ ፕሮግራም ላይ ተላልፎላታል:: ይህ ሥራም በድርሰት ዓለም የመጀመሪያው ሥራዋ ነው::  “ወይ ሆቢ ሆቢ” ለድምፃዊ አሊ ቢራ ያበረከተችው ብዙዎች የወደዱላት አይረሴ የሙዚቃ የግጥም ሥራዎቿ ነው:: የሸዋሉል መንግሥቱ ሙዚቃ “ዘሃረር” የተባለ መፅሔትንም በማዘጋጀት ትታወቃለች። በጊዜውም የ27 ዓመት ወጣት ነበረች::

ሸዋሉል መንግሥቱ ብዙ ጊዜዋን ያሳለፈችው በሀረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል በየሁለት ወሩ የሚታተመውን “የምስራቅ በረኛ” መፅሄትን በማዘጋጀት ነበር::በዚህ ክፍል ለሀረር ምሥራቃዊ ሰጎን ኦርኬስትራ አያሌ ግጥሞች እና ዜማዎችን ቲያትሮች እና ዝማሬዎችን ታዘጋጅ ነበር:: የሸዋሉል መንግሥቱ የመፅሐፍ ደራሲም ነበረች። በ1962 ዓ.ም ተፅፎ በ1968 ዓ.ም የታተመው ‹‹እስከመቼ ወንደላጤ›› የተሰኘ ሥራዋ በዚህ ዘመን እምብዛም የሚታወቅ ባይሆንም በዘመኑ ብዙ የተነበበ ነው:: በ32 ዓመቷ  አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው የሸዋሉል በአዲስ አበባ በቆየችባቸው ጥቂት ጊዜያት ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች። በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በዜና አንባቢነት፣ በፕሮግራም አዘጋጅነት እና በሬዲዮ ድራማ ፀሐፊነት ሠርታለች::

በደርግ ዘመን በቀበሌ ሊቀ መንበርነት ያገለገለች ሲሆን በወቅቱም የመኢሶን አባል ነበረች:: የሸዋሉል መንግሥቱ የአምስት ልጆች እናት ስትሆን ግንቦት 1969 ዓ.ም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው።

ምንጭ – የኢትዮጵያ ታሪክና ቱሪዝም

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here