ፈረሰኞቹ

0
112

ዐፄ ምኒልክ ወደ ዙፋን ሲመጡ የጣሊያን ወራሪ ጦር የኢትጵያን ድንበር ዘልቆ እስከ መረብ ምላሽ ተቆጣጥሮ ነበር:: ጣሊያን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ እና ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ ሽፋን በእጅ አዙር በሴራ የተተበተበውን የውጫሌ ውል አቅርባ እንድትፈራረም አደረገች:: በወቅቱ ሴራውን የተረዱት ዐፄ ምኒልክ ጣልያን አቋሟን እንድትለውጥ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ቢያደርጉም ጣሊያን አሻፈረኝ አለች:: አብዛኞቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሀገራት ከጣሊያን ጎን ቆሙ:: በዚህም ንጉሡ ለሀገራቸው ነጻነት እና አንድነት ለማይቀረው ጦርነት የክተት አዋጅ አስነገሩ:: የሀገሪቱ ታላላቅ ባላንጣ መሳፍንቶች የዙፋን ሽኩቻቸውን ትተው ለሀገራቸው ነጻነት በአንድ ላይ ቆሙ:: ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተወጣጡ አርበኞችም የንጉሡን ጥሪ ተቀብለው ታላቅ ተጋድሎ ፈጸሙ:: የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነው የአድዋ ድል በአርበኞቹ እና በመሪዎቻቸው ተጋድሎ እውን ሆነ:: በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈረስ ጦር እና በስለላ አገልግሎት ከጠላት ጦር የበለጠ ጠንካራ እንደነበር ጦርነቱን በአይናቸው አይተው የመዘገቡት ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ ‟ታሪክ ዘመነ ዘዳግማዊ ምኒልክ” በተሰኘው ጽሑፋቸው አትተዋል::

በጦርነቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ፈረሰኞች ተሳትፈዋል:: በአድዋ ጦርነት ከሌሎች የኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በመሆን ተጋድሎ ከፈጸሙ እና የድሉ ተቋዳሽ ከሆኑት መካከል ደግሞ የአገው ህዝቦች ይጠቀሳሉ:: ይህ የታሪክ አካል በጸሐፊያን ዘንድ እምብዛም ሲተረክ አይስተዋልም:: የአገው ፈረሰኞች ከአድዋ ጦርነት እና ከአምስት ዓመቱ የጣሊያን ዳግም ወረራ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲሁም ሁለቱን ድሎች ለመዘከር የተመሰረተውን የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ሰሞኑን ባከበረበት ወቅት በቦታው ተገኝተን ከታሪክ ባለሙያዎች እና ከአባቶች መረጃዎችን አሰባስበን ለመቃኘት ወደድን::

የአገው ሕዝብ ከፈረስ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ካላቸው የሀገራችን ህዝቦች መካከል አንዱ ነው:: ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ጀምስ ብሩስ እና ሌሎች በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች በሰሜኑ ክፍል በተለይ በጎጃም ምድር ፈረስን ከፈረስ እንዲሁም ከበሬ ጋር አቆራኝተው የሚያርሱ ሕዝቦች ማስተዋላቸውን ጠቅሰዋል:: እነዚህ ሕዝቦች የአዊ ማህበረሰቦች እንደሆኑ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ እና ቅርስ አሰራር ትምህርት ክፍል ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ የሚገኙት አቶ አለማየሁ ወርቅነህ ያስረዳሉ::

አዊዎች በትውልድ ቅብብሎሽ ፈረስን ለተለያዩ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎቶች ለረጅም ዘመናት ሲጠቀሙ ቆይተዋል፤ አሁንም ይጠቀሙበታል:: ከእነዚህ ውስጥ ለእርሻ፣ ለሰረገላ እና ጋሪ መጎተቻ፣ ለዕቃና ሰው ማጓጓዣ፣ አስከሬን፣ ሙሽራና ታቦት ማጀቢያ ተጠቃሽ ግልጋሎቶች ናቸው:: ፈረስን ከዚህም ባሻገር የሀገርን ዳር ድንበር ከወራሪ ለመጠበቅ እና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በተደረጉ ጦርነቶች ተጠቅመውበታል::

አለቃ ጥላየ አየነው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር ሊቀመንበር ናቸው፤ በ18 ዓመታቸው ነው ማህበሩን የተቀላቀሉት:: ማህበሩ ሲመሰረት አላማ አድርጎ የተነሳው የአድዋ ድልን እና አርበኞችን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ገድል እንዲሁም በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ የተሳተፉ እና የተሰው አርበኞችን እንዲሁም የፈረስን አስተዋጽኦ ለመዘከር እንደነበር ተናግረዋል:: ሀገራችን በጠላት በተወረረች ጊዜ የንጉሡን የክተት አዋጅ ተከትሎ የአዊ አርበኞች በፈረስ ስንቅ እና መሳሪያቸውን ጭነው መዝመታቸውን ይናገራሉ:: በጦርነቱ ጊዜ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን የጣሊያን ሰራዊት በጦር በጎራዴ እንዲሁም ውጅግራ በሚባል አንድ ጎራሽ መሳሪያ እያበረሩ ድባቅ መምታታቸውን ከቀደሙ አባቶች ሲሰሙ እንዳደጉ ይተርካሉ:: ስንቅ በማዘጋጀትም ሆነ በተጋድሎ የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንደነበርም ገልጸዋል:: ኢትዮጵያ በጣልያን ላይ በተቀዳጀቻቸው ሁለቱም ድሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርበኞች እና ፈረሶች መሰዋታቸውን እና መቁሰላቸውን በመግለጽ ለድሉ የተከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት አያይዘው አስረድተዋል::

ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳየ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአገው ጥናት ኢንስቲቲዩት (ተቋም) ዳይሬክተር  የአዊ ፈረሰኞች ከሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ጋር በአድዋ ተራሮች አጥንታቸውን መከስከሰቸውን፤ ደማቸውን ማፍሰሳቸውን ገልጸዋል:: በዚህ ላይ የፈረሶች አስተዋጽኦ የጎላ ነውም ብለዋል:: የአዊ ፈረሰኞች ገድል ከአድዋ ጦርነት ባሻገር በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ላይም መደገሙን ገልጸዋል:: ከጦርነቱ ተጋድሎ በተጨማሪም አርበኞች ራሳቸውን ለውጠው የጠላት ሰራዊት በሰፈረበት አካባቢ ስለላ ያካሂዱ ነበር:: በዚህም የጠላት ጦር ያለበትን ሁኔታ በመሰለል እንዲሁም የተዛባ መረጃ በመስጠት ለወገን ጦር ከፍተኛ እርዳታ ያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል:: ይህም ለተገኙት ድሎች ድርሻው የጎላ እንደነበር ያወሳሉ::

አለቃ አሳየ ተሻለ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር ምክትል ሊቀ መንበር ናቸው:: አባታቸው ግራዝማች ተሻለ በሁለተኛው የኢትዮ ጣሊያን ጦርነት (1928-1933) መዝመታቸውን እና ከድል በኋላ የፈረሰኞች ማህበርን ከመሰረቱት ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ:: ከ1933 ዓ.ም በፊት ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በስምምነት የተደራጁ ፈረሰኞች እንደነበሩ ከአባታቸው መስማታቸውንም ተናግረዋል:: አለቃ አሳየ አባታቸው በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ከድል በኋላ ቆስለው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውን ይተርካሉ:: ከድሉ መልስ አባታቸውን ግራዝማች ተሻለ ተሰማን ጨምሮ፣ ቀኛዝማች ከበደ ንጉሴ፣ ግራዝማች መኮንን አለሙ እና ግራዝማች ንጉሤ የተባሉ ባላባቶች ከጦርነቱ መልስ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበርን እንደመሰረቱ ተናግረዋል:: የአባታቸው አባት በአድዋ ጦርነት መዝመታቸውንም አለቃ አሳየ ጠቅሰዋል::

አለቃ አሳዬ እንደሚሉት በድል የተመለሱ አባቶች በአድዋ እንዲሁም በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን አጥንታቸውን ለከሰከሱት አርበኞችና ፈረሶች ብሎም በድል ለተመለሱት መታሰቢያ ለማድረግ በ1933 ዓ.ም በይፋ ተመስርቷል። በየዓመቱ ጥር 23 ቀን በሚከበረው የአዊ የፈረሰኞች ማህበር ክብረ በዓል ላይ ፈረሰኞች የሽምጥ ግልቢያ እና በጉግስ አባሮ የተፎካካሪን ጋሻ የመምታት ትርኢት ያቀርባሉ:: ይህም አርበኞች ጠላትን እንዴት በፈረስ እያሳደዱ ይወጉ እንደነበር የሚዘክሩበት አንዱ ማሳያ መሆኑን አባቶች ይናገራሉ::

ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ በጦር ጀት የሚታገዘውን የጣሊያን ፋሽስት ጦር ድል የነሱት ፈረስን እንደ ትልቅ መዋጊያ መሳሪያነት በመጠቀም ነበር:: ፈረስን የውጊያቸው የጀርባ አጥንት አድርገው ድልን ይቀዳጁ እንጂ፣ በርካታ አርበኞች እና ፈረሶቻቸው ተሰውተዋል። የአምስት ዓመት የአርበኝነት ዘመን አጥንታቸውን ለከሰከሱ አርበኞች እና ፈረሶች፤ በድል ለተመለሱ ፈረሰኞች መታሰቢያ ለማድረግ ሲባል ማኅበሩ በ1932 ዓ.ም በሃሳብ ደረጃ ተጠንስሶ በዓመቱ 1933 ዓ.ም በይፋ ተቋቋመ። አርበኞች ጣሊያንን ካባረሩ በኋላ የፈረስንና የአርበኞችን ገድልና ውለታ ለመዘከር ከባንጃ ወረዳ 16፣ ከአንከሻ ወረዳ ደግሞ 16 ፈረሰኞች በድምሩ 32 ሆነው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር መሰረቱ በማለት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያስረዳሉ::

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር አየነው ማሞ የአገው ምድር ሕዝብ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት የነበረውን  ተጋድሎ አጥንተዋል:: ከማይጨው ጦርነት ጀምሮ ከዚያ በኋላ ጣሊያን ወደ መሃል ሀገር ሲገባ የነበረውን አልገዛም ባይነት አሳይተዋል:: በጄኔራል አቺሊ የተመራውን ጦር ረፍት ከነሱት ኢትዮጵያዊያን መካከል አገዎች ተጠቃሽ ናቸው:: ለዚህ ደግሞ ፈረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው::

 

ሳምንቱ በታሪክ

 

እቴጌ አረፉ

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ » በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ባለቤት፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም አረፉ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ። በኋላ ግን አጽማቸው ተነስቶ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለአባታቸው ለዐፄ ምኒልክ ባሠሩት  አጽም ማሣረፊያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ተቀብሯል።

እቴጌ ጣይቱ ሰኞ የካቲት አራት ቀን 1910ዓ.ም በመንፈቀ ሌሊት ህመም ፀንቶባቸው ከሚወዱትና ከሚወዳቸው ሕዝብ በሞት ተለዩ። የዕረፍታቸውን ዜና የኀዘኑንም ሥነ ሥርዓት ለማወጅ የቤተ መንግሥቱ መድፍ ሃያ አምስት ጊዜ ድምፁን አሰማ። በኀዘኑ ሥርዓትም ላይ እቴጌ በአድዋ ጦር ሜዳ ላይ ያሳዩትን የቆራጥነትና የጀግንነት ሙያቸውን እየጠቀሱ በግጥም እየገለጡ በማሞገስ ይሸልሉ ይፎክሩና ያቅራሩ ነበር።

የእቴጌም አስክሬን በወርቅ ሐረግ በተከበበ የእንጨት ሳጥን ተደርጐ በብረት ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ በቀድሞ ቤተ ፀሎታቸው ውስጥ ሸራ ቤት እየተባለ ይጠራ በነበረው መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤት ውስጥ በታላቅ ክብር አረፉ። ለተሰበሰበው ሕዝብ ትልቅ ግብዣ ተደርጐ የቀብሩ ፍፃሜ ሆነ።

እቴጌ ጣይቱ ከማረፋቸው አስቀድመው ለንግሥት ዘውዲቱ «ልጄ ማሚቴ ሆይ አደራዬን ሰጥቼሻለሁ» ብለው መናዘዛቸው በታሪክ ይወሳል።

በዚሁ መሠረት ንግሥት ዘውዲቱ በታኅሣሥ ወር1920 ዓ.ም የአፄ ምኒልክን ዓፅም ከቤተ መንግሥቱ አስወጥተው ለማረፊያው በታዕካ ነገሥት በአታ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በነበረ ጊዜ የእቴጌንም ዓጽም እዚሁ እንዲያርፍ ቢፈልጉም የእንጦጦ ማርያም ካህናት እቴጌ ጣይቱ ለኛም እናታችን ናቸውና መታሰቢያነታቸውን እንሻለን በማለት የተቃውሞ ድምፅ አሰሙ። ቢሆንም የኑዛዜውን ቃል አብራርተው በማስረዳታቸው ፈቅደውላቸዋል።

እቴጌ ጣይቱ ስማቸውን የሚያስጠራ ታሪካቸውን የሚያስታውስ አንድ የምኒልክ የደም ቋጠሮ ሀረግ ሳያሠሩ ማለፋቸው ሳያሳዝናቸው እንዳልቀረ መገመቱ ቀላል ነው። ይህንም ሀዘን ለግዞት ወደ እንጦጦ ከመውጣታቸው ጥቂት ጊዜ በፊት ሊሸኟቸው በተሰበሰቡት መኳንንትና ወይዛዝርት ፊት የገጠሙት ግጥም አንጀት የሚበላ ነበር።

«ተወዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ

ማን ያይብኝ ነበር ይህን ሁሉ ጉድ»

ምንጭ:- ‘ዐፄ ምኒሊክ እና የኢትዮጵያ  አንድነት’ ጳውሎስ  ኞኞ

 

ኮምፒውተር

በዓለም የመጀመሪያው ሁለ-ገብ መቀምር (Electronic Numerical Integrator And Computer) ወይም ኮምፕዩተር የካቲት 6 1938 ዓ.ም  ይፋ ተደረገ። ለብዙ ሰዎች ኮምፒዩተር ሲባል ዐዕምሯቸው ላይ የሚመጣው የግል (ፐርሰናል) ኮምፒዩተር ነው። ነገር ግን ኮምፒዩተር ሲባል በጣም ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል። ላኘቶፕ፣ ዴስክቶፕ ፣ ማይክሮ-ኮምፒዩተር ፣ ሱፐር-ኮምፒዩተር ፣ ካልኩሌተር ፣ዲጂታል ካሜራ እና ሌሎችንም ያጠቃልላል።

ምንጭ:- ብሪታኒካ

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here