ፈተናን በፈተና

0
188

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ ለመጨረሻ ጊዜ ካስፈተናቸው አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ያሳለፈው በ2012/13 የትምህርት ዘመን ነው። በወቅቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባውን ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 55 ነጥብ 7 በመቶ ነበሩ። ከዚያን ወዲህ ባሉ ዓመታት የተፈታኞች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የማለፊያ ነጥብ የሚያስመዘግቡት ግን እጅግ አናሳ ናቸው። በየዓመቱ  የሚመዘገበው ውጤት ማሽቆልቆል ዋና ምክንያት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት አስተማማኝ ፀጥታ በሌለበት ሁኔታ ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸው ነው:: የጸጥታ ስጋቱ ግን አሁንም ቀጥሏል:: በተለይ በአማራ ክልል ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በክልሉ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ዘግይተው እንዲጀምሩ አድርጓል፤ አሁንም የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ይገኛሉ። ይህ ሆኖ እያለ ትምህርታቸውን ዘግይተው ለጀመሩ ተማሪዎች የተጠናከረ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲወስዱ ቀነ ቀጠሮ ተቆርጧል። በበይነ መረብ እና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በወረቀት ይሰጣል የተባለው ፈተናው ከሐምሌ 3 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል። ተማሪዎች እና የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትም ከወዲሁ የክልሉን የቀደመ ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል  የቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ ይገኛሉ።

አሚኮ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ ተፈታኝ ተማሪዎችን አነጋግሯል:: የዘንድሮው ዓመት ትምህርት በጸጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል:: መምህራንም ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማድረግ ጀምሮ ይዘቶች በወቅቱ እንዲሸፈኑ እየሠሩ ነው ብለዋል:: ተማሪዎችም በዓመቱ ለሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል::

በሰሜን ሸዋ ዞን የአቤቶ ነጋሲ ክርስቶስ ወረደ ቃል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2016 ዓ.ም 150 የተፈጥሮ ሳይንስ እና 294 የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ኩራ ድፋባቸው አስታውቀዋል:: ባለፈው ዓመት የተፈጠረው የውጤት ቀውስ በዚህ ዓመትም እንዳይደገም ከወዲሁ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው::  ዘንድሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተማሪዎችን ትኩረት እንዳይሰርቅ፣ እንዴት ማጥናት እንዳለባቸው እና ግብ ጥለው መዘጋጀት እንዳለባቸው ተከታታይ የስነ ልቦና ግንባታ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል:: መምህራን ይዘቶችን በወቅቱ ለመሸፈን መደበኛውን ክፍለ ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ ተማሪዎች ርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ እና ቤተ መጻሕፍት እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል::

ትምህርት ቤቱ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ላላቸው 134 ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል::

የሰሜን ሸዋ ዞን መመዝገብ ከነበረበት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ማሳካት የቻለው 54 በመቶውን ብቻ ነው:: ተመዝግበው በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙት 35 ሺህ (75) በመቶ ብቻ መሆናቸውን ለበኩር በስልክ ያስታወቁት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ኩራባቸው ናቸው:: ከዚህ ውስጥ 10 ሺህ 145 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል::

የጸጥታ ችግሩ የመማር ማስተማር ሥራው ሳይቆራረጥ እንዲሄድ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል:: የተሻሉ መምህራንን መመደብ እና መጻሕፍትን በትኩረት ማሰራጨት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::

የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ትምህርት ቤቶች ወጪያቸውን ችለው የአዳር ጥናት እንዲያደርጉ ዕድሎች እየተመቻቹ መሆኑንም ገልጸዋል:: መምህራን ያለፉ የፈተና ጥያቄዎችን ለተማሪዎች ከመሥራት ባለፈ አዳዲስ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግም ይሠራል ብለዋል:: ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ የቤተ ሙከራ ክፍሎችን እንደ አዲስ በማደረጃት ትምህርቱ አይረሴነት እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል:: በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ቤቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለተማሪዎች ክፍት ሆነው የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል:: ተማሪዎች ከቀውሱ ወጥተው ትምህርታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆኑ የሥነ ልቦና ድጋፍ ስልጠናዎችን ለመስጠት ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል::

ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው ያሉት ኃላፊዉ፣ ታጣቂ ኃይሉም ሆነ ሌላው ሕዝብ ለትምህርት ልዩ ከለላ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል:: የአማራ ክልል ተፈታኝ ተማሪዎች የሚወዳደሩት ሰላማቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ ሌሎች አካባቢ ተማሪዎች ጋር በመሆኑ ሕዝቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል:: ወላጆችም ልጆቻቸው ካልባሌ ቦታ እንዲርቁ ክትትል በማድረግ፣ ካልተፈለገ ጭንቀት እና መረበሽ ወጥተው ለፈተናው ብቻ እንዲዘጋጁ በማድረግ የክልሉን ተወዳዳሪነት ማስቀጠል እንደሚገባ መክረዋል::

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2016 ዓ.ም 1ሺህ 823 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናል:: ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከተማ አስተዳደሩ ተፈታኞችን ለማብቃት የተጠናከረ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ ነው:: የቀደሙ ዓመታት የፈተና ጥያቄዎችን መሥራት፣ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በሁሉም የሳምንቱ ቀናት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት መስጠት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን የመምሪያዉ ኃላፊ እየበሩ አዕምሮ አስታውቀዋል::

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል:: በመሆኑም ተማሪዎች እንደ ሀገር በሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የስነ ልቦና ግንባታ  የማነቃቂያ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል:: ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው እና መምህራንም ተማሪዎቻቸውን በስነ ምግባር እና በዕውቀት ለመገንባት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቋል።

የወልድያ ዩኒቨርሲቲም በሰሜን ወሎ ዞን በ2016 ዓ.ም ለሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል:: ዩኒቨርሲቲው በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በዩኒቨርሲቲው መምህራን ለሁለት ወራት የሚቆይ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ያቀደው ባለፈው ዓመት የማጠናከሪያ ትምህርት በተሰጠባቸው ትምህርት ቤቶች የተመዘገበው ውጤት የተሻለ መሆኑ እንደሆነ በዩኒቨርሲቲዉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ቢሆን (ዶ/ር) አስታውቀዋል:: በመሆኑም የማጠናከሪያ ትምህርቱ በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 2ሺህ 285 ተፈታኝ ተማሪዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል::

የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦን ላይን ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል:: ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በአጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በዓመቱ መጨረሻ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ለመስጠት ባይቻልም በሁሉም ክልሎች በተመረጡ ከተሞች እንደሚሰጥ ግን አረጋግጠዋል:: ቀሪዎቹ ደግሞ በተለመደው አግባብ ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሏል::

የሀገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር (ዶ/ር) እሸቱ ከበደ በበኩላቸው እንዳስታወቁት ፈተናውን በኦን ላይን ለመሥጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: ከትምህርት ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ተማሪዎች የሙከራ ፈተና የሚለቀቅላቸው ሲሆን ደጋግመው እንዲሞክሩ እና እንዲለማመዱ ይደረጋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here