“ፈጣሪን ለአንድ ዓመት ዕድሜ አልጠይቅም …”

0
228
ዛሬ ላይ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ሠራተኞች ቀደምት በሸለቆ ውስጥ መንገድ ጠርገው አስፓልት ላይ እንዲራመዱ እንዳደረጓቸው ይረዱ ይሆን? በተሠራ መንገድ እንድንራመድ ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል፣ መስዋእትነት ጭምር።
በተሠራ ቤት የምንኖር ያህል ቀደምቱ ታግለው ሳይንሱን እና ጥበብን በሙከራ አላምደው ምቹ የሙያ ዘርፎችን ፈጥረዋል።
ዛሬ የምናቀርብላችሁ ሰው ታሪክም ሙያው ባልነበረበት ዘመን ጋዜጠኝነትን ለመፍጠር፣ ለማሳደግና መስመር ለማስያዝ ከተጉት መካከል አንዱ ነው፤ ጋዜጠኛ ጥላሁን ወንዴ::
ንግሥት ኤልሳቤት ባሕርዳርን በጎበኙበት ቀን በከተማዋ ቀበሌ 03 በ1957 ተወለድሁ ይላል።
አፍላ ወጣትነቱን በደርግ ዘመን አሳልፏል። ከስድስት ዓመት በላይ በወታደርነት ፣ከ29 ዓመታት በላይ ደግሞ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሰርቷል። በጥቅሉ 36 ዓመታትን በሥራ ላይ አሳልፏል።
አሁንም በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአርታኢነት በመስራት ላይ ይገኛል። የዚህን አንጋፋ ሰው ረጂም የሙያ ልምድ እናቀርባለን።
የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን ሦስት ጊዜ ለማቋረጥ ተገዷል። ምክንያቱ ደግሞ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ተሳታፊ በመሆኑ ነው።
በ1977 የሁለተኛው ዙር ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሲጀመር አብዮት ጠባቂዎች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ቤት መጥተው ወሰዱት። በወቅቱ የኤፍሬም ታምሩ “ልመደው ሆዴ” ዘፈን ወጥቶ በስፋት እየተደመጠ ነበር። ጥላሁን እና ጓደኞቹ ይህንን ሙዚቃ እያደመጡ ጉዞ ከባህርዳር ከተማ ወደ ዴዴሳ የውትድርና ማሰልጠኛ አደረጉ።
ከጥር ወር 1977 ጀምሮ ለስድስት ወራት የውትድርና ስልጠና ወሰደ። ስልጠናው ሲጠናቅም ጎንደር ምድብ ቦታው ሆነ። በተጨማሪም ጎርጎራ አጠገብ ይገኝ በነበረው አበርጃ በተባለ ቦታ ለአንድ ወር የተሃድሶ ስልጠና ወስዶ አጠናቀቀ። በሰባተኛ ክፍለ ጦር 78ኛ አየር መቃወሚያ ሻለቃ፤ የዙ 23 አየር መቃወሚያ ምድብተኛ ሆኖ በአዘዞ፣ በመተማ ዮሐንስ፣ በደለጎ፣ ሽንፋ እና ሸህዲ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ተሳትፎ አድርጓል። የሁለት ዓመት አገልግሎቱን አጠናቆ በ1979 ዓ.ም መጨረሻ ወደ ባሕርዳር ተመለሰ።
በ1977 ዓ.ም ወደ ውትድርና ሲሄድ የ11ኛ ክፍል የመጀመሪያ መንፈቀ ትምህርት አጋማሽ ፈተና ወስዶ ነበር ትምህርቱን ያቋረጠው። ከሁለት ዓመት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በኋላ እንደገና በ1980 መስከረም ወር ላይ የተቋረጠውን የ11ኛ ክፍል ትምህርት ቀጠለ። የመጀመሪያውን መንፈቀ ትምህርት እንደተማረ በድጋሚ የብሔራዊ ውትድርና ጥሪ ቀረበለት።
ጥላሁን ትምህርቱን የመቀጠል ብርቱ ፍላጎት ነበረውና ተሰወረ። አብዮት ጠባቂዎች አባቱን አሰሩበት። አባቱን ለማስፈታት ሲል በድጋሚ ወደ ውትድርና ተመለሰ። በዚህ ጊዜም 11ኛ ክፍል መንፈቅ ላይ ተቋርጦ ቀረ።
የድጋሜ ብሔራዊ ውትድርና ግዳጁ ጉዞ ወደ አፋር ሆነ። ለወራት በሚሌ ቆይታ አደረገ። ጉዞው ወደ አሰብ ቀጠለ። ከዚያም የአሁኑ ኤርትራ ጫፍ ላይ ደረሰ። ያ የቀይ ባህር ዳርቻ ቦታም ጼዎ ይባላል። በግዳጅ ለዘጠኝ ወራት በዚያው ቆየ።
“ውትድርናን እስከ መጨረሻው ልቆይበት አልፈልግም ነበር” የሚለው ጥላሁን ከ1981 መጨረሻ ወራት አንስቶ እስከ 1982 ቆይታውን በሁርሶ ጦር መኮንኖች አካዳሚ አደረገ። ፈታኝ የነበረውን የአንድ ዓመት የእጩ መኮንንነት ስልጠና አጠናቀቀ። በ1982 በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ተመረቀ።
በመቀጠልም ለሜካናይዝድ ጦር ምድብ ስልጠና አዋሽ አርባ ገባ። ወቅቱ ሻዕቢያ እና ሕወሐት እንቅስቃሴያቸውን ያስፋፉበት ነበርና፣ ስልጠናው ፍሬ ሳያፈራ ተቋረጠ። ጥላሁን ወያኔን በሙከጡሪ፣ በወለጋ እና በጂማ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ተዋግቷል። ወቅቱ የደርግ መንግሥት አቅም ያጣበት ሆነ። ሠራዊቱ በየአካባቢው ተዳከመ፣ ጥላሁንም አዲስ አበባ ገባ። ሕወሐት አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። በዚህ ጊዜ”ቤተሰቦቼ ልጃችን ሞቷል ብለው ተስፋ ቆርጠው ነበር” በማለት ወቅቱን ያስታውሳል። ሰኔ ወር 1983 ጥላሁን ለቤተሰቦቹ ደስታን ይዞ ባሕርዳር ገባ፣ በሕይወት መገኘቱ ደስ አሰኛቸው።
ያቋረጠውን የ11ኛ ክፍል ትምህርት ለሶስተኛ ጊዜ እንደገና የቀጠለው ጥላሁን “ትምህርቱ እምቢ አለኝ፣ በተለይ ሒሳብ ከበደኝ” ይላል ውጤቱም አልተሳካም።
1985 ዓ.ም የ12 ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ ውጤቱ ለከፍተኛ ትምህርት የማያስቀጥል ሆነ። “1986 በሕይወቴ የመጨረሻ ተስፋ የቆረጥሁበት ነበር፣ ከዚያ በኋላ በባሕርዳር ውስጥ እንደ እኔ ወንበዴ አልነበረም” ይላል ።
የአልኮል ሱሰኛ ሆነ፣ ይደባደባል፣ ይታሰራል ይፈታል፣ መጥፎ ሕይወትን አሳለፈ። ወቅቱ የአማራ ክልል ቢሮዎች የሚደራጁበት ነበር፤ ብዙ ቦታዎች ስራ ለመቀጠር አመልክቶም እንዳልተሳካለት ጥላሁን ይናገራል። ከብዙ ሙከራዎች በኋላ የቀድሞውን ማስታወቂያ ቢሮ በጋዜጣ ስርጭት ባለሙያነት ተቀላቀለ። 127 ብር ደግሞ የወር ደመወዙ ነበር። ከዚህ የሚጀምረው የጥላሁን ወንዴ የጋዜጠኝነት ሕይወት የፊታችን ሰኔ ወር 30 ዓመት ይሞላዋል።
ጥላሁን የተቀጠረበት ተቋም መጀመሪያ የአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ፣ ሁለተኛ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ፣ ሦስተኛም የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት አሁን ደግሞ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሚል የስም እና የመዋቅር ለውጥ አድርጓል ። “ድርጅቱ አራት ጊዜ የስም ለውጥ ሲያደርግ እኔ ዛሬም በጋዜጠኝነቱ አለሁ” ሲል በኩራት ይናገራል።
ጥላሁን በእስካሁን የሥራ ቆይታው በጋዜጣ ስርጭት ባለሙያነት፣ በረዳት ካሜራ ባለሙያነት፣ በበኩር ጋዜጣ እና መጽሔት ሪፖርተርና አርታኢ፣ በአማራ ቴሌቪዥን ዜናቴሌዥ ሪፖርተርና አርታኢ፣ የበኩር ጋዜጣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት አምድ ዋና አዘጋጅ፣ የቴሌቪዥን ዜናና ወቅታዊ ቲም አስተባባሪ፣ የእቅድ ዝግጅትና ግምገማ ምክትል ዳይሬክተር እና በሌሎችም ኀላፊነቶች አገልግሏል።
ጥላሁን ስለጋዜጠኝነት ሥራ ጅማሮ ሲናገር ”ጋዜጠኛ ምን እንደሚያደርግ አላውቅም ነበር፣ አንድ የጋዜጣ መጣጥፍ ለመስራት ሦስት ካሴት ቀርጫለሁ፣ ስለ ዘገባ ስራ ያስተማረኝ እና ያሳየኝ አልነበረም” በማለት ወደ ኋላ ያስታውሳል።
ስለ ዘገባ እና አሰራሩ ምንም ባለማወቁ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው ዘገባ ለህትመት እንዳልበቃ ይናገራል። በወቅቱ የጋዜጠኝነት ትምህርትን የቀሰመ አንድ ሰው ብቻ እንደነበረም ይናገራል። ሌሎቹ ጋዜጠኞች ከመምህርነት እንደመጡ በመጠቆም።
በድርጅቱ የአማራ ቴሌቪዥን ሪፖርተር ሆኘ እንደተመደብኩ አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሠራሁ የሚለው ጥላሁን አለቆቹ በሰራው ፕሮግራም ላይ የሰጡት አድናቆት በሙያው ውስጥ እንዲቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተለት ይገልጻል::
በ1992 ዓ.ም የአማራ ቴሌቪዥን የ30 ደቂቃ ሳምንታዊ ስርጭቱን ሲጀምር የመጀመሪያውን ፕሮግራም ያዘጋጀው ጥላሁን ወንዴ ነው። ለ18 ቀናት በተደረገ የመስክ ስምሪት የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳስስ ዝግጅት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር አሰናዳ። ይህ ዝግጅት የአማራ ክልል ቅኝት በሚል ርዕስ በአምስት ክፍሎች ተሰናድቶ የተላለፈ ነበር ።
ጥላሁን በጋዜጠኝነት ሕይወቱ እንደፈተና የገጠሙትን እንዲህ ያስታውሳል:: አንድ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ ድርጅት በባህርዳር ተመስርቶ ነበር። ያ ድርጅት ከተመሰረተበት ዓላማ ውጪ ሕገ ወጥ ተግባራትን በመከወኑ ጥላሁን የምርመራ ዘገባ ለመስራት ተነሳ። ለሁለት ወራት የድርጅቱን ገመና ከመርመረ በኋላ ፕሮግራሙን አጠናቀቀ። ነገር ግን ይህ ዝግጅት እንዳይተላለፍ የወቅቱ መሪዎች ከለከሉ። ጥላሁን ይህንን ሲያስብ በጣም የሚቆጭበት ነው።
ጥላሁን መልካም መልካሙን ንግግሬን ብቻ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አድርገህ ስራ የሚሉ የስራ ኅላፊዎችም ገጥመውት ያውቃሉ። የሰሜን ሸዋ አስተዳዳሪ የነበሩ አንድ አመራር በተጠየቁት ጉዳይ ላይ በብስጭት ይናገራሉ። ዘገባው ከተላለፈ በኋላ ለጥላሁን አለቃ “የላክኸው ጋዜጠኛ ስንት ጥሩ ጥሩ ነገር ተናግሬ እንዴት ጅል ጅሉን መርጦ ያስተላልፋል?” ብለው ከሰሱት። ጥላሁን አለቃው ፊት ቀረበ። ለምን ተብሎ ሲጠየቅም “ሰው ካሜራ ፊት ለምን ጅል ንግግር ያወራል፣ መርጦ አይናገርም ነበር?” ብሎ ምላሽ ሰጠ። አለቃውም ደግ አደረግህ ብለው አለፉት።
ጥላሁን ከ1987 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት እየሰራ ዲፕሎማውን የተቀበለበት ጊዜ ነውና “ብዙ ዋጋ የከፈልሁባት ናት” የበለጠ ክብር ለዲፕሎማ ትምህርቱ እንዳለው ይናገራል። ቀጥሎ ጥላሁን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን በዲግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ጊዜም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ሁለተኛ ዲግሪውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ጥላሁን ወንዴ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው። “ትዳር መስፈርት አያስፈልገውም” የሚለው ጥላሁን ያለፉትን 24 ዓመታት በትዳር ውስጥ ቀጥሏል። ከባለቤቱ ጋር የተገናኘበትን አጋጣሚም በማስታወስ ይደነቃል። በድንገት ትውውቅ የተጀመረ ፍቅር አድጎ በልጅ ፍሬ ለመባረክ በቅቷል።
“የኔ ባህሪ በጣም አስቸጋሪ ነው፣ ባለቤቴ ይህንን ሁሉ ችላ መኖሯ ይገርመኛል፣ በጣም የተሳካለት ጥሩ ትዳር አለን” ሲል የትዳር ሕይወቱንም ይናገራል። በስራ ቦታ የሚገጥመውን ብስጭት እና መጥፎ ነገር ቤት ባለመውሰድ ሰላማዊ ትዳር እንዲኖረው ጥንቃቄ እንደሚያደርግም “ብስጭቴን ወደ ቤት አልወስደውም” ሲል ይገልጻል።
“በትዳር ውስጥ አንድም ቀን አልተጣላንም የሚሉ ሰዎች አብረው አይደሉም፣ ወይም እየዋሹ ነው” የሚለው ጥላሁን “ከሚስቴ ጋር እንጋጫለን፣ አንድም ቀን ሽማግሌ አስቀምጠን ግን አናውቅም፣ ራሳችን ችግራችንን እንፈታለን” በማለት ትዳር ከግጭት ነጻ እንደማይሆን ተናግሯል።
ሐሜት አይወድም፣ ቀልድና ጨዋታ፣ አሳ ማጥመድ ይመቹታል። ተንኮለኛ እና ሁሉንም አውቃለሁ የሚል ሰው አልወድም ይላል።
ቁጡ፣ ተናዳጅና ቅጽበታዊ ውሳኔ የእኔ መገለጫዎች ናቸው ይላል፤ ሀብት ብዙ እንደማያጓጓውም ይናገራል። ድሮ 10 ብር ዛሬ ደግሞ 200 ብር በኪሱ ካለ በጣም ደስተኛ ነውና “ፈጣሪን ለአንድ ዓመት ዕድሜ አልጠይቅም፣ በየዕለቱ ጠዋት ለ12 ሰዓት ሲመሽ ደግሞ 12 ሰዓት እጠይቀዋለሁ” በማለት ስለ ነገ ከፈጣሪ በላይ መጨነቅ እንደማይገባ ያምናል።
በጣም ተናጋሪ መሆኔ ዋጋ አስከፈለኝ የሚለው ጥላሁን ዛሬ ላይ ትምህርት ወስጄባቸዋለሁ ይላል፤ አሁን ከመናገር ተቆጥቦ ማድመጥ ላይ ማተኮሩን በመግለፅ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here