ፈጣኑ የአስፋልት ግንባታ

0
20

በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በአራተኛው የቀለበት አውራ ጐዳና ሥራ ሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር መንገድ በስድስት ሰዓታት አስፋልት ለብሶ መጠናቀቅ መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ድረ ገጹ እንዳስነበበው በቤጂንግ አራተኛው የቀለበት መንገድ ስምንት ሺህ ቶን ወይም ስምንት ሚሊዬን ኪሎ ግራም አስፓልት በሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር መንገድ ላይ በስድስት ሰዓታት ውስጥ ተነጥፎ ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆኗል፡፡

በሌሎች ሀገራት በሚገኙ ከተሞች ለመንገድ ስራ አውራ ጐዳናዎች ሲዘጉ መጨናነቅ እና መሰል ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ በቻይና ግን በፍጥነት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ማከናወን የተለመደ ቢሆንም በሩብ ቀን ወይም በስድሰት ሰዓታት ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ መስራት ግን አዲስ ክብረወሰን ሊሆን እንደሚችል ነው የተገለፀው፡፡

የቻይና የመሰረተ ልማት አስተዳደር ኃላፊዎች ለጥገና ሥራ መንገዶችን መዝጋት የሚያደርሰውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በውል በመገንዘብ ለችግሩ ከወዲሁ መፍትሄ መሻታቸው ነው የተጠቆመው፡፡ የተበላሸውን መንገድ በአዲስ መልኩ ለመስራትም ሆነ ለመጠገን ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰኑትን በከፊል ከመዝጋት በጥቂት ሰዓታት ሌሊት ሰርቶ ማጠናቀቅን ነው በመፍትሄነት ተግባራዊ ያደረጉት፡፡

በሀገሪቱም በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያሉ አካላት “ከሰው በላይ” በሆነ ፍጥነት መሥራትን የሚገልጹበት “ቻይና ስፒድ” የተሰኘ መርህ (ሞቶ) በተግባር ማሳየት ችለዋል፡፡

በቻይና ከተሞች የሚዘረጋ አዲስም ሆነ የሚጠገን አውራ ጐዳናን ማታ ኗሪዎች ወደ ቤት ገብተው ጠዋት ለሥራ ከመውጣታቸው በፊት ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለመቻሉም የተጠቀሰው የአስፋልት መንገድ ስራ አብነት መሆኑን ነው በማደማደሚያነት ያስነበበው – ድረ ገጹ፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here