ፉክክሩ የቀዘቀዘበት መድረክ

0
118

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ውድድር በድሬዳዋ እና አዳማ ከተማ ተደርጎ ተጠናቋል። የመጀመሪያው ዙር  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጥቂት የማይባሉ ተስፈኛ ተጫዋቾች ራሳቸውን ያሳዩበት፣በርካታ ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭ ሽፋን ያላገኙበት፣ አነስተኛ ግቦች የተቆጠሩበት፣  የአምናው ሻምፒዮን ክለብ ላለመውረድ ትግል ያደርገበት ነበር።

ኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በበላይነት አጠናቋል። ሀድያ ሆሳዕና እና ቅድስ ጊዮርጊስ በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ባሕር ዳር ከተማ አምስተኛ እና ፋሲል ከነማ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው የመጀመሪያውን ዙር ጨርሰዋል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ዓመቱን ሙሉ እየተንገዳገደ የጨረሰው ኢትዮጵያ መድን ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በአሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ የሚመራው ቡድን የመጀመሪያውን ዙር 35 ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆኖ ነው ያጠናቀቀው። ኢትዮጵያ መድን በሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ነው።

የፊት መስመሩ  ከመቻል ቀጥሎ  የሊጉ ጠንካራው የአጥቂ ክፍል ነው። እስካሁን 21 ግቦችን አስቆጥሯል። የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የማይረበሽ እና የሊጉ ቀዳሚው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መሆኑን ቁጥሮች ያሳያሉ። በአቡበከር ኑራ፣ በያሬድ ካሳዬ፣ ንጋቱ ገብረ ስላሴ፣ ሚሊዮን ሰለሞን እና በረከት ካሌብ የሚመራው የኋላ ክፍል አምስት ግቦች ብቻ ነው የተቆጠረበት።

ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች ውስጥ ዐስሩን ድል አድርጓል። ኢትዮጵያ መድን አምስት ጨዋታዎችን ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ በቀሪው ሁለት መርሀግብር ብቻ ተሸንፏል። ይህም እስካሁን በሊጉ አነስተኛ ጨዋታዎችን የተሸነፈ ቀዳሚ ክለብ ያደርገዋል።

ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ውድድር ይበልጥ ተጠናክሮ የሚመጣ ከሆነ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በዋንጫ ታጅቦ ለማጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ያሳምርለታል። ኢትዮጵያ መድን በ2015 ዓ.ም ድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከተመለሰ በኋላ ወጥ የሆነ አቋም ሲያሳይ ዘንድሮ ለመጀምሪያ ጊዜ ነው።

ባስላፍነው ዓመት በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ ዓመቱን የጨረሰው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የመጀመሪያውን ዙር ጨርሷል። ነብሮቹ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ከመሪው ኢትዮጵያ መድን በአምስት ነጥብ አንሰው  በ30 ነጥብ ይከተላሉ።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደስ የሚመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ካደረጓቸው 17 ጨዋታዎች ዘጠኙን አሸንፈዋል። ሦስቱን መርሀግብር ነጥብ ሲጋሩ በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል። ሀድያ ሆሳዕና በማጥቃት እና በመከላከሉ እንደ ኢትዮጵያ መድን ጠንካራ የሚባል አይደለም። ክለቡ በሁለተኛው ዙር ያለበትን ክፍተት ሞልቶ ካልተመለሰ ለዋንጫ ይፎካከራል ተብሎ አይጠበቅም፤ አሁን የያዘውን ሁለተኛ ደረጃም ይዞ ለማጠናቀቅ ይችገራል- የብዙዎች አስተያየት ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የአቋም መውረድ የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ዘንድሮም የቀድሞ አቋሙን ለመድገም ሲቸገር ተስተውሏል። አንጋፋው ክለብ በመጀመሪያው ዙር 29 ነጥብ በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነው የጨረሰው። ፈረሰኞቹ ከመቻል እና ኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ አስፈሪ የፊት መስመር አላቸው።

የፊት መስመሩ በመጀመሪያ ዙር ውድድር 20 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ወጥ አቋም ማሳየት የሚሳነው የኋላ ክፍሉ ደግሞ 14 ግቦች ተቆጥረውበታል። በቀድሞ ተጫዋቹ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና ይበልጥ ተፎካካሪ ለመሆን የቀድሞ አቋሙን መመለስ ይጠበቅበታል።

በዚህ ዓመት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው የጣናው ሞገድ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች ሰባቱን ረቷል። አምስቱን ሲሸነፍ በተመሳሳይ በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።  ባሕር ዳር ከነማ ጠንካራ የኋላ ክፍል ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ነው። ክለቡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቡና 11 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት።

ይህም ከኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብ ያደርገዋል። 17 ግቦች ደግሞ አስቆጥሯል። ባሳለፍነው ዓመት ደካማ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው የጣናው ሞገድ ዘንድሮም ገና ከወዲሁ ከመሪው ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ዘጠኝ ደርሷል። በሁለተኛው ዙር ውድድር የፊት መስመሩ ያለበትን ግብ የማስቆጠር ችግሩን ካልቀረፈ  ወደ መሪው መጠጋት የሚያስችለውን ውጤት በማስመዝገብ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

ፋሲል ከነማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀድሞ ጥንካሬው ከድቶታል፤ ጉልበቱ ዝሎ በተደጋጋሚ አቅም አንሶት ታይቷል። አፄዎቹ ዘንድሮም በሁሉም የሜዳ ክፍል ያሉ ተጫዋቾቻቸው የማሸነፍ ስነ ልቦናቸው እና ወኔያቸው ተሰልቦ እየተመለከትን ነው። በመጀመሪያው ዙር ውድድር በ23 ነጥብ ዐስረኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ካከናወኗቸው 17 ጨዋታዎች ያሸነፉት አምስቱን መርሀግብር ነው። አራት ጨዋታዎችን ደግሞ ተሸንፏል።

በመጀመሪያው ዙር ውድድር የፋሲል ከነማን ያህል በፕሪሚየር ሊጉ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ የወጣ ክለብ የለም። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ያለው ክለብ ስምንት ጨዋታዎችን አቻ ተለያይቷል። በጌታነህ ከበደ የሚመራው የፊት መስመር 17 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። 15 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። አፄዎቹ በሁለተኛው ዙር ውድድር ያሉባቸውን ክፍተቶች ማረም ካልቻሉ ከአምናው የከፋ የውድድር ዓመት ሊያሳልፉ ይችላሉ- የብዙዎች ሀሳብ።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ በሁሉም የሜዳ ክፍል ተዳክሞ ተስተውሏል። ክለቡ በ22 ነጥብ 12ኛ ላይ ይገኛል። ንግድ ባንክ አሁን ላይ ያን ያህል የመውረድ ስጋት ባይኖርበትም ከወራጅ ቀጠናው ግን በስድስት ነጥብ ብቻ ነው ርቆ የሚገኝው።

ባለፉት ዓመታት በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በ15 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የመጀመሪያውን ዙር ጨርሷል። ሐይቆች ካደረጓቸው 17 ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት። ሀዋሳ ከነማ ከተጋረጠበት የመውረድ አደጋ ለመውጣት ሁለተኛው ዙር ውድድር ሳይጀመር የቀድሞ አሰልጣኛቸውን ሙሉጌታ ምህረትን ድጋሚ ዋና የክለቡ አሰልጣኝ አድርገው ሾመውታል።

ከሀዋሳ በተጨማሪ አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን አንተነህ ተፈራ ከኢትዮጵያ ቡና በስምንት ግቦች እየመራ ይገኛል። አህመድ ሁሴን ከአርባ ምንጭ እና ያሬድ ብርሃኑ ከመቀሌ 70 እንደርታ በተመሳሳይ በሰባት ግቦች ይከተላሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረገው የውል ስምምነት በዓመት 60 ጨዋታዎችን የቀጥታ ስርጭት ሸፋን እንዲያገኙ ተዋውሏል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት እንደ ባለፉት አራት ዓመታት ዘንድሮ በርካታ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዳላገኙ ይታወቃል። የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኙ ጨዋታዎች ከአራት ሳምንታት እንደማይበልጡ ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመጀመሪያው ዙር ውድድር ጠንካራ ፉክክር ያልታየበት እና ብዙ ግቦች ያልተቆጠረበት ሆኖ አልፏል፡፡ በተለይ ውድድሩ ከድሬዳዋ ወደ አዳማ ከተማ ከተዛወረ በኋላ የግቦች  መጠን ቀንሰዋል። ለአብነት እስከ 15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሀግብር 222 ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ይህ ማለት በአንድ የጨዋታ ሳምንት 14 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩት።

በኢትዮጵያ ያለው የክለቦች የዝውውር አካሄድ ለወጣት ተስፈኞች ዕድል እንዳይሰጥ እና ራሳቸውን እንዳያሳዩ  እንቅፋት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ታዲያ የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት መድረክ በመጀመሪያው ዙር ውድድር  የተሰጣቸውን የመሰለፍ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ያሳዩ የመጪው ዘመን ከዋክብትን ተመልክተናል።

የዐፄዎቹ አጥቂ አንዋር ሙራድ እና ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ተከላካይ ዘረሰናይ ብርሀነ፣ የፈረሰኞቹ ተከላካይ ሔኖክ ዮሐንስ፣ የመድኑ ተከላካይ በረከት ካሌብ፣ የባሕር ዳር ከነማው ሄኖክ ይበልጣል እና የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ  ኦካይ ጁል በመጀመርያው ዙር ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተሰፈኛ ታዳጊዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ውድድር ከ17 ቀናት እረፍት በኋላ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ እንደሚጀምር አወዳዳሪው አካል አሳውቋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here