ፋሲል ግቢ

0
127

በታሪካዊቷ ጎንደር፣ በአስደማሚው የፋሲለደስ ግቢ እየተንሸራሸርን አብረን እንድንቆይ በአክብሮት ጋበዝኳችሁ። ጎንደር የተቆረቆረችው በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደነበር ይነገራል። በንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ የተቆረቆረችው ዉቢቷ ጎንደር እስከ 1854 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት መናገሻ መዲና በመሆን ያገለገለች እድሜ ጠገብ ከተማ ናት። በአፈታሪክ እንደሚገለፀው አንድ መነኩሴ ናቸው አሉ ለንጉሡ  በ”ገ” ቃል በሚጀምር ስፍራ ላይ መናገሻውን እንዲገነባ ነገሩት። በዚህ መሰረት ንጉሡ የመነኩሴውን ምክር ተቀብሎ በተለያዩ ገዥዎች አማካይነት ጎንደር ላይ ዋና ከተማውን እንደገነባ ይነገራል። ታዲያ ጎንደር ከተቆረቆረች ጀምሮ በርካታ ቤተመንግሥቶች፣  አብያተ ክርስቲያን፣  ገዳማት፣ ቤተመጻህፍት፣ እና የግለሰብ እና የመንግሥት ህንፃዎች ተገንብተውባት እናገኛለን።

በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ ጎንደር ዋና ከተማቸው እንደሆነች በማወጅ ቤተ መንግሥት በመገንባት ከተማዋን ቋሚ መኖሪያቸው አድርገዋል። ከዚያ በፊት ነገሥታት መኖሪያቸውን ከቦታ ቦታ እያንቀሳቅሱ  እና በድንኳን ይኖሩ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። ይህ ልማድ የቀረውም ንጉሥ ፋሲለደስ ጎንደርን መዲናቸው አድርገው ከቆረቆሩበት በ1628 ዓ.ም በኋላ ነበር። መኖሪያ ቀየውን “የፋሲል ግቢ” ብለው እንደሰየሙትም ታሪክ ያስረዳል።

አሁን ታዲያ በዚሁ ታሪካዊ ግቢ ዓፄ ፋሲለደስ ለቤተመንግስት የገነቡትን ጨምሮ ተከታትለው የነገሱት ነገሥታት በየዘመናቸው የገነቧቸውን  አብያተመንግሥት አሻራዎች ይገኙበታል። ዐፄ ዮሀንስ፣ ዐፄ እያሱ፣ ዐፄ ባካፋ፣ ዐፄ ዳዊት ሳልሳዊ እንዲሁም እቴጌ ምንትዋብ የገነቧቸው ለአብነት ይጠቀሳሉ። በ70ሺህ ካሬም ሜትር ስፋት ላይ የሚገኘው የፋሲለደስ ግቢ ዙሪያውን 900 ሜትር ርዝመት ባለው ግንብ ታጥሯል።

ንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ ያስገነቡትን ቤተመንግሥት በመጎብኘት እንጀምር። የቤተመንግሥቱ ህንፃ ንድፍ የትም ዓለም የሌለ የኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ አስጎብኛችን ነግሮናል። ቢሆንም የወቅቱን የመካከለኛውን ዘመን የኪነህንፃ ጥበብ የተከተለ እጅግ ውብ ቤተ መንግሥት ነው። ለንጉሠ ነገሥት ፋሲለደስ የግል መኖሪያቸውም ነበር።

ፋሲል ግንብ ውስጥ ያሉት ሕንጻዎች የምድር እና ፎቅ ቤት ያሉት ሲሆን በአሁኑ ወቅት  በሙዝየምነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዋናው ወለል ላይ የመጀመሪያው ክፍል የፍርድ መስጫ ሲሆን ቀጣዩ 1ኛ ፎቅ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ ግብር የሚካፈሉባቸውን አዳራሾችን ይዟል። ሁለተኛው ፎቅ የንጉሥ ፋሲለደስ የመልበሻ ክፍል ሲሆን ቀጣዩ 3ኛ ፎቅ የመዝናኛ ስፍራን አካቷል። ግቢውን በተሻለ መልኩ ማየት የሚያስችለው ማማ ደግሞ የግንቡ ማደማደሚያ ነው።

ወደ ቀጣዩ ግንብ እንለፍ ዐፄ ዮሀንስ የንጉሥ ፋሲለደስ ልጅ ናቸው። በደንብ የሚታወቁበት መለያ ባህሪ ግብር አለማስከፈላቸው እና የእንስሳት መብት ቀደምት ተሟጋችነታቸው ነው። በግንቡ ጀርባ አንድ ደወል አሰቅለውም ነበር። ፍትህ እንደተጓደለ ያመነ ማንኛውም ሰው እንዲደውለው ነው የተሰቀለው።

የዐፄ ዮሐንስ የመንግሥት ስራቸውን ያስኬዱበት የነበረ ነው። ህንፃው በመጀመሪያው ፎቅ ቤተመጻሕፍት፣ በሁለተኛው ፎቅ የንጉሡ እንግዳ መቀበያ ክፍሎች አሉት።

ሦስተኛው ግንብ  የዐፄ ዮሐንስ ልጅ ዐፄ እያሱ ያስገነቡት የቤተመንግሥት ህንፃ ነው። ህንፃው ከዋናው ከፋሲል ግንብ ጀርባ የሚገኝ ሲሆን ውስጡ በብር፣ በወርቅ፣ በከበሩ ደንጋዮች እና በዝሆን ጥርስ ያጌጠ ነው። ዐፄ እያሱ ከአባታቸው ዐፄ ዮሐንስ በተለየ አይነቱን መጠነ ሰፊ ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲሉ ግብር ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ ይሰበስቡ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

ቀጣዩ 4ኛ ግንብ የንጉሥ ዳዊት ሳልሳዊ ሲሆን ባስገነቡት የቤተመንግሥት ኮምፕሌክስ የሙዚቃ አዳራሽ አበርክተዋል። አዳራሹ ወፈር ባለ የድንጋይ ግድግዳ የተከፈለ ሲሆን በግራ በኩል ያለው መንፈሳዊ መዝሙር ይዘመርበታል፤ በቀኝ በኩል ያለው ክፍል ደግሞ ዓለማዊ የሙዚቃ ድግስ የሚዘጋጅበት ነው። አዳራሹ በአራቱም አቅጣጫ ወደ ውስጥ የሚያስገቡ ሁለት ደረጃዎች እና ሁለት በሮች ተሰርተውለታል።

የአንበሳ ቤት ሌላው በፋሲል ግቢ ከሚገኙ የጥንት አሻራዎች አንዱ ነው። በውስጡ ባለጥቁር ጋማ አንበሶች ይኖሩበት ነበር።.

ዐፄ ፋሲል ግቢ ስሜን ምእራብ በኩል የሚገኘው አንድ ትልቅ ቤተመንግሥት ደግሞ የዐፄ በካፋ ነው። ንጉሡ የግብር አዳራሽ እና የፈረሶች ማረፊያ አዳራሽም አሰርተዋል። የፈረሶች ማደሪያ ለእያንዳንዱ ክፍል ያለው ሲሆን እንደ ባለቤቶቻቸው ማእረግ ክፍላቸው ይለያያል።

የዐፄ በካፋ ሚስት እቴጌ ምንትዋብም የራሷን ቤተመንግስት በማሳነፅ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። በጎንደሮች ዘመን የባሏን ሞት ተከትላ ለአርባ ዓመታት ያህል እንደገዛች ይነገርላታል። ቤተመንግሥቷ ከፋሲል ግቢ ጀርባ በኩል የተገነባ ነው። ሁለት ፎቆች ያሉት ከኖራ ድንጋይ የተሰራ ውብ ህንፃ ነው። ከእርሷ መኖሪያ አጠገብም የቀጭን ፈታዮች ትምህርት ቤት ከፍታ እንደነበር ታሪክ ይዘክራል።

12ቱ በሮች

የፋሲል ግቢ 900 ሜትር በሚረዝም ግንብ የታጠረ ሲሆን አስራ ሁለት በሮች አሉት። የመጀመሪያው የፊት በር ወይም ጃንተከል በር ይባላል፣ ከቤተ መንግሥቱ ደቡባዊ አቅጣጫ ወደ አደባባዩ ያስወጣል። ሌላው ወንበር በር ወይም የዳኞች በር ይባላል። ሶስተኛው በር ተስካር በር ሲሆን በዐፄ ዳግማዊ እያሱ ዘመን በተካሄደ ጦርነት የወደመ አንድ ድልድይ ነበረው። ሌላው አዛዥ ጥቁሬ በር ሲባል ከግንቡ በስተምእራብ ከአደባባይ ተክለ ሀይማኖት ቤተክርስቲያን ጋር በአንድ ድልድይ የተገናኘ እንደነበር የሚያመላክተው ፍራሽ አሁንም ቆሞ ይታያል። አደናግር በር በተመሳሳይ በቀጭን ፈታዮች በኩል ካለው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ጋር በአንድ ድልድይ የተገናኘ በር ነው። ኳሊ በር ከእልፍኝ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መግቢያ ቀጥሎ ያለ በር ነው። እምቢልታ በር የሚባለው ደግሞ የሙዚቀኞች መግቢያ ነው። ሌላው እልፍኝ በር የሚባለው ሲሆን ከፋሲል ግቢ የግል መኖሪያዎች ጋር የሚያገናኝ ነው። ባልደራስ በር ወይም የፈረሰኛው አዛዦች መግቢያ ይባላል። ራሶች የሚገቡበት ራስ በር ወይም የቋራ ሰዎች የሚገቡበት ቋረኞች በር ሌላው በር ነው። እርግብ በር፣ ወይም ቀጭን አሸዋ በር እና እንኮየ በር የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ ልእልት እንኮይ መግቢያ ነው። ከግምጃ ቤት ማሪያም ቤተክርስትያን ግቢ ጋር የሚያገናኘው 12ኛ በር ደግሞ ግምጃ ቤት ማሪያም በር ይባላል።

የፋሲል ግንብ በ1971 ዓ.ም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ጥንታዊ ታሪክን እያስቃነ የሚገኝ ሰው ሰራሽ ቅርስ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ትናንት እየመሰከሩ የዛሬዎቹ የእኛ ትውልድ የነማን ፍሬ እንደሆነ አፍ ሞልቶ የሚናገር የታሪክ ማስረጃ እየሰጡንና እየነገሩን፣ በአባቶቻችን እንድንኮራ እያደረጉን ከ600 ዓመታት በላይ የዘለቁት የፋሲለደስ ግቢ ቤተመንግስቶች ክብራችን ናቸው። በዘመኑ የነበሩ አባቶቻችንን ማንነት፣ የእውቀት እና የጥበበኝነት ደረጃ ፍንትው ብሎ በሚታይባቸው በእነዚህ ቅንጡ ቤተመንግስቶች ላይ የሚስተዋለው ውበት አስደማሚ ነው። ዕድሉን አግኝቶ ለጎበኛቸው ሁሉ እጅግ የተለየ ስሜት ውስጥ አስገብተው በዝነ ህሊና 600 ዓመታትን ወደኋላ በምናብ ይወስዳሉ። በዚህ ስፍራ ያኔ እነዚህ ዕፁብ ድንቅ ቤተመንግስቶች ሰርተው ቅንጡ ህይወት ይኖሩ ስለነበሩ አባቶቻቸው እንዲያስብ የማድረግ ኃይል አላቸው። ለፋሲል ግቢ በተጨማሪ በጎንደር እና ዙሪያዋ በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት የተመዘገቡ 11 ቦታዎች ያሉ ሲሆን መዋኛ፣ ቁስቋም፣ የራስ ግምብ፣ ዶሮ ቤት፣ ከጎንደር ከተማ ውጪ ደግሞ ወደ ጎርጎራ በኩል ጉዛራ ቤተ መንግስት፣ ደብረ ብርሃን ስላሴ፣ ቁስቋም ይጠቀሳሉ።

አጭር እውነታ

ስለ ጎንደር አስገራሚ እውነታዎች በአጭር እና በግልፅ፦

የኢትዮጵያ ንጉሳዊ ከተማ – ጎንደር በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነገሥታት ዋና ከተማ ነበረች።

ፋሲል ግንብ (ፋሲል ገቢ) – የአፍሪካ ብቸኛው የነገሥታት ካስተል ኮምፕሌክስ ሲሆን በUNESCO የዓለም ቅርስ ተመዝግቧል።

ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን – በውስጥዋ ያሉ የመላእክት ስዕሎች በዓለም የታወቁ ናቸው።

የጥምቀት በዓል በዓመት አንድ ጊዜ በታላቅ ስነ-ሥርዓት ይከበራል።

“የአፍሪካ ካሜሎት” በመባል በአውሮፓውያን መጻህፍት ጎንደር በዚህ ስም ተጠርታ ታወቀች።

  • የትምህርት እና ስነ-ጥበብ ማዕከል – በታሪክ የመጻፍ እና የሃይማኖት ትምህርት ማዕከል ነበረች።

የተራራ አየር ንብረት – ጎንደር ቀዝቃዛ እና ምቹ አየር ንብረት አላት።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here