በኢትዮጵያ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማፋጠን ዲጂታል ዘርፉ ትልቁን ሚና ይጫወታል። ይህን ታሳቢ በማድረግም ዲጂታል 2030 በሚል ማዕቀፍ ወደ ሥራ ተገብቷል። የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ደግሞ አንደኛው ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማሕበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስነበበው የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን እና አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ የማሻሻያ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ዲጂታል መታወቂያ ቁልፉ መሣሪያ እንደሆነ ነው ያስታወቀው።
ከዚህ ጋር በተገናኘ ታዲያ ሁሉም የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሒሳብ ቁጥራቸውን ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያቸው ጋር እንዲያስተሳስሩ ብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ይህን ተከትሎም ደንበኞች ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛል።
ለመሆኑ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ከባንኮች ጋር መተሳሰሩ ፋይዳው ምንድን ነው? ጉዳዩን በተመለከተ በብሔራዊ መታወቂያ ኘሮግራም የባለድርሻ አካላት እና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዋና ዓላማውም የፋይናንስ ተቋማት ወጥ የመታወቂያ አጠቃቀም እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
የብሔራዊ ባንክን ማሳሰቢያ ተከትሎ ባንኮች ደንበኞቻቸው የዲጅታል መታወቂያቸውን ከባንክ ሒሳብ ቁጥራቸው ጋር እንዲያስተሳስሩ እያደረጉ ነው፤ በአካል ወይም ባሉበት ሆነው የሚያስተሳስሩበትን አማራጭ በማቅረብ ነው አየሠሩ የሚገኙት፡፡
አሁን ላይ ባንኮች ደንበኞቻቸው በአካል ወደ ቅርንጫፍ ሳይመጡ የፋይዳ መታወቂያቸውን የሚያስተሳስሩበትን ማስፋንጠሪያ እያጋሩ ይገኛል፤ አማራጩን በመጠቀም እንዲያስተሳስሩ ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ ከባንኮች ጋር ለማስተሳሰር ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድሞ መፈጸም ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ትስስሩ ከወረቀት ወደ ዲጂታል የሚደረገውን ሽግግር ይፈጥራል። የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕቅድም ለማሳካት አብነት ነው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ግልጽ አሠራርን ከመፍጠሩ ባለፈ ማጭበርበርን ያስቀራል። ከዚህ በተጨማሪም በተቋማት እና በዜጎች መካከል መተማመን ይፈጥራል፤ ደንበኞችን በልዩነት ለመለየትም ያስችላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከደህንነት ጋር በተያያዘ ደንበኞች ስጋት እንዳለባቸው ያነሳሉ፤ ይህን በተመለከተ ማብራያ የሰጡት አቶ ሳሚናስ ሰይፉ በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ላይ ያሉ መረጃዎች ለሌላ ተቋም ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ የመረጃው ባለቤቶች በሚላክላቸው የይለፍ ቃል መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና ወጭ ቆጣቢ አማራጭ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።
አቶ ሳሚናስ እንዳሉት በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ቋት ላይ የሚቀመጡ የግል መረጃዎች ተመስጥረው (በምስጢር) የሚቀመጡ ናቸው።
የዲጀታል መታወቂያ ፕሮግራም 32 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን በቋቱ መዝግቦ የዲጀታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ከማድረጉ ባለፈ ከአንድ መቶ ተቋማት ጋርም የትስስር ሥርዓት ፈጥሯል። 32ቱ ደግሞ ባንኮች ናቸው።
የኢትዮጵ ብሔራዊ ባንክ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ዙሪያ ያተኮሩ ሁለት መርሀ-ግብሮችን መጀመሩ ይታወሳል።
የመጀመሪያው መርሃ-ግብር ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ወደ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በማስገባት የተሻለ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ዓላማውም የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማስፋፋት ነው፤ ይህም ሂደት የተመዝጋቢውን ግላዊ መረጃዎች ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት እና የመረጃ ደህንነትን በማረጋገጥ የሚከናወን ይሆናል።
ሁለተኛው መርሀ-ግብር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ እና የፋይናንስ ሥርዓት ደህንነትን ለማስጠበቅ ነው፤ የዲጂታል መታወቂያን መጠቀም ደግሞ ወሳኝ ይሆናል።
የመርሃ ግብሮቹ ትግበራም የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚን ትክክለኛ ማንነት በማረጋገጥ የፋይናንስ ግብይቶች ደህንነትን ለመጠበቅ እና ተያያዥ ስጋቶችን ለመቀነስ እንደሚያስችሉ ነው ብሔራዊ ባንክ ያስታወቀው፤ ከዚህ ባሻገር ነዋሪዎች በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው በዲጂታል አማራጭ ብቻ ደንበኛ ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።
የብሔራዊ መታወቂያ ትግበራው (ትስስሩ) ታዲያ የገንዘብ መጭበርበርን በመቀነስ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር እና የተሻሻሉ የደንበኞችን የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓቶች በመዘርጋት የተጠናከረ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
በዲጂታል 2030 ጅማሮ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራባቸው ከሚገኙት መካከል የዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት አንዱ ነው፡፡ ባንኮችም ታዲያ ወጥ በሆነ መንገድ ደንበኞቻቸውን ለመለየት ይችሉ ዘንድ ከሥርዓታቸው ጋር ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያን (ፋይዳን) የማስተሳሰር ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በመላ ሀገሪቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ የምዝገባ ሂደቱ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።
አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በቀን ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን የመመዝገብ አቅም ያላቸው ስድስት ሺህ ማሽኖች በመላው ሀገሪቱ ሥራ ላይ መዋላቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀን እስከ 140 ሺህ ሰዎች ለፋይዳ መታወቂያ እየተመዘገቡ ነው፤ ከተለያዩ መዝጋቢ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትም ተደራሽነቱን ለማስፋት እየተሠራ ይገኛል።
መረጃ
ለዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባ አስፈላጊ ሰነዶች፡-
የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የልደት የምስክር ወረቀት፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የንግድ ምዝገባ ወይም የንግድ ፈቃድ የምስክር ወረቀት፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣ መንጃ ፈቃድ፣ የባንክ አካውንት ደብተር፣ የመኪና ሊብሬ፣ የቤት ካርታ፣ የሙያ ፈቃድ ማስረጃ፣ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር፣ የጤና መድኅን መታወቂያ፣ የጡረታ መታወቂያ፣ የሥራ ፈላጊ መታወቂያ፣ የተማሪነት መታወቂያ፣ የእድር እና የእቁብ ደብተር ዋናዎቹ ሲኾኑ በማንኛውም የመንግሥት አካል የሚሰጥ መታወቂያ እና የቀበሌ ሥራ አስኪያጅ የሚሰጠው ማረጋገጫም ተቀባይነት አላቸው፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት ሰነዶች መካከል አንዱን በመጠቀም መመዝገብ እና ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያውን ማግኜት ይቻላል፡፡
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


