ስሙ ሀሰን ይባላል፤ የ25 ዓመት ወጣት ነው:: በምዕራብ ዳርፉር አል – ኑር በምትባል ትንሽ መንደር ነው የተወለደው:: አል – ኑር (ብርሃን እንደ ማለት ነው) በአንድ ወቅት ልክ እንደ ስሟ የብርሃን እና የተስፋ ምድር ነበረች:: ይሁን እንጂ አሁን ላይ ምድራዊ ሲኦል ሆናለች:: በአካባቢው ካለው እረፍት የለሽ ግጭት በተጨማሪ ተፈጥሮ ፊቷን እንዳዞረችባቸው ወጣቱ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል::
ታዲያ ሀሰን በዚህ ጊዜ ሁሉን ነገር ትቶ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አደገኛ ከሆኑ የስደት ጉዞዎች አንዱ በሆነው የምሥራቁ መስመር ከሚጓዙት ከመቶ ሺዎች አንዱ ሆነ። ይህ የእርሱ ብቻ ታሪክ አይደለም:: በ2025 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ 238 ሺህ የሚገመቱ እንደ እርሱ ያሉ ግለሰቦች ይህንን ጉዞ አድርገዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት መረጃ::
ይህም የሚያቃጥሉ በረሃዎችን እና ሞት የሚጠራውን ጨካኙን የኤደን ባሕረ ሰላጤ በማቆራረጥ ወደ አረብ ባሕረ ገብ መሬት የሚደረግ የዘመናችን አደገኛ ጉዞ ነው። በዚህ አደገኛ መስመር ብቻ የሚጓዙ ሕገ ወጥ ስደተኞች ታዲያ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የወጡ መረጃዎች እና ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከ123 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ይገኛሉ:: ከ2023 እ.አ.አ ጋር ሲነጻጸር ይህ ቁጥር በ11 ነጥብ አምስት በመቶ መጨመሩን መረጃው ያስነብባል::
ለአብነት እስከ 2025 ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል:: በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። በዓለም ላይ ሁለት ቢሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ወይም ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች መኖሩ ቁጥሩ እንዲጨምር አድርጎታል ይላል መረጃው::
በሶሪያ ከዐሥር ዓመታት በላይ የዘለቀው ግጭት ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል:: የዓለም ፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በመስከረም 2025 ሪፖርቱ እንዳመላከተው ደግሞ በየመን የቀጠለው ቀውስ በየሳምንቱ ለአዲስ መፈናቀሎች ዋነኛ ምክንያት ሆኗል::
እንደ ሳህል እና ምዕራብ አፍሪካ ባሉ ክልሎች ውስጥ ያለው አካባቢያዊ አለመረጋጋት የማያቋርጥ ስደት እንዲኖር አድርጓል:: በማያንማር የሚገኙ የሮሂንጊ ብሄር ሕዝቦችም ቋሚ ቦታ የሌላቸው ሙሉ በሙሉ ሀገር አልባ ሰደተኛ ሕዝቦች ሆነዋል።
ከጦርነት እና ግጭት በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥም ሌላኛው የስደት ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል:: ባሳለፍነው ነሐሴ ወር እንደ ገዳሪፍ እና ደቡብ ዳርፉር ባሉ በርካታ የሱዳን ግዛቶች ከባድ የጎርፍ አድጋ ተፈጥሯል:: ይህም ከ500 በላይ አባወራዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አስገድዷል። የድርቅ እና የዝናብ እጥረት መጨመርም የ2025 የፈረንጆች ዓመት ከገባ ወዲህ ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች መሰደድ ምክንያቶች ናቸው::
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በአየር ንብረት ለውጥ ለሚከሰት ፍልሰት አዲስ መፍትሄ እንዲኖር አሳስቧል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ አብዲከር በስብሰባው መክፈቻ ላይ በአየር ንብረት ምክንያት የሚፈጠር ስደት እና መፈናቀል ከፈተኛ መሆኑን ተናግረዋል::
የአፍሪካ አህጉር ከዓለም አቀፍ የአየር ብክለት ልቀት መጠን ከአራት በመቶ በታች ድርሻ ቢኖረውም በአየር ንብረት ለውጥ ግን ክፉኛ ከተጎዱት መካከል አንዱ ነው። እየጨመረ የመጣው ድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የአካባቢ መራቆት በአህጉሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ሳህል፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የቻድ ሐይቅ ተፋሰስ ባሉ ክልሎች ለሚከሰቱ ስደት እና መፈናቀሎች ዋናኛው ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንዲሁም ድህነት ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል እና መሰደድ ሌላኛው ትልቁ ምክንያት መሆኑን የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድረጅት መረጃ አመልክቷል:: ይህ ችግር በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በእስያ ባሉ ሀገራት የጠነከረ መሆኑን መረጃው ያስረዳል:: በቬንዙዌላ እና በአፍጋኒስታን የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት የተሰደደው እና የተፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር ጦርነት ካስከተለው ችግር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ሪፖርቶች አመልክተዋል::
በ2025 ጦርነትን እና ግጭትን የሸሹ ሶሪያውያን፣ ዩክሬናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን ሀገራቸውን ለቀው እግራቸው ወደ መራቸው ሀገራት ተሰደዋል:: ከመካከለኛው ምሥራቅ ሶሪያ እና የመን፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ፣ ከሳህል ክልል እና ከመካከለኛው አፍሪካ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሁም ከእስያ አፍጋኒስታን እና ማያንማር (በተለይ የሮሂንጊያ ብሄር) ዜጎቻቸው የሚሰደዱባቸው ሀገራት ናቸው::
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር ትልቁ የስደተኞች ቁጥር የተመዘገበው በዩክሬን ነው:: ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ተሰደዋል:: ቬንዙዌላ፣ ሆንዱራስ፣ ጓቲማላ እና ኤል ሳልቫዶር ከላቲን አሜሪካ አህጉር በርካታ ሰዎች ለስደት የሚዳረጉባቸው ሀገራት ናቸው::
የሜዲትራኒያንን መስመር፣ የአሜሪካ – ሜክሲኮ ድንበር እና ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን ያለውን “የምሥራቁ መስመር” ስደተኞች ለመተላለፊያነት የሚጠቀሙት ዋነኛ መስመር ነው:: ባሳለፍነው የነሐሴ ወር በምሥራቁ መስመር አንድ ጀልባ በመስጠሟ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም:: ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በሰሃራ በረሃ በውኃ ጥም እና በወንበዴዎች በአሰቃቂ መንገድ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች በርካታ ናቸው::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ወይም ዓለም አቀፍ ድንበር ያላቋረጡ ነገር ግን ቀያቸውን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የለቀቁ ሰዎች ቁጥር ከ73 ሚሊዮን በላይ ደርሷል:: ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን ስደተኞች ከአህጉራቸው ሳይወጡ በጎረቤት ሀገራት ይጠለላሉ። በተመሳሳይ አብዛኞቹ የሶሪያ ስደተኞች በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኛሉ።
ችግሩን ለመቀነስ ሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሱ ቢሆንም ችግሩ ግን ሲቀንስ አይሰተዋልም:: ብቸኛው እና ዘላቂ መፍትሄ ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያስገድዷቸውን ምክንያቶች መቀነስ እንደሆነ የሪሊፍ ዌብ መረጃ ያመለክታል። ይህ ካልሆነ ግን ዓለም ባንክ እ.አ.አ እስከ 2050 ድረስ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለስደት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጧል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም