ፍልስጤም

0
324

በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፋችን ስለፍልስጤም ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ ማስነበባችን ይታወሳል፤ ቀጣዩ ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል፤

መልካም ንባብ!

“ሕዝብ አልባ መሬት፣ መሬት ለሌለው ሕዝብ”  እና “እናንት አረቦች ንቁ እና ተነሱ!” የሚሉ እንደ ቅደም ተከተላቸው ፂዮናዊነት እና አረባዊነት የሚያቀነቅኗቸው ጠንካራ አስተሳሰቦች ናቸው። በሁለቱ  ብሔራዊ ንቅናቄዎች ተሀድሶ ውስጥ እንግዳ የሆኑ ተመሳሳይ ክስተቶች  ተስተናግደዋል።

የአረብ ብሔርተኝነት በብዙ መሰናክሎች መሀል ቢያልፍም እየተጠናከረ ነበር። ከኦቶማን ቱርክ ጨቋኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን የማግኘት ፍላጎቱ እና ትግሉ እየሰፋ በመጣበት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ከዓለማችን የፖለቲካ ሁኔታ መቀያየር ጋር የብሔርተኝነቱ ጉዞ እና የትግል መልኩ ተቀየረ።

አንደኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረበት ወቅት ነበር፤ ኃያላን ጎራ ፈጥረው የሚቆራቆሱበት አስከፊ ጊዜ።  በዚያም በዚህም ወገን እሳት ይተፋል፤ ይዘንባል፤ አሸናፊ መሆን እንዲህ በቀላሉ የሚተነበይ ወይም የሚታሰብ አልነበረም። ስለዚህ ኃያላኑ ጦርነቱን ማሸነፍ የሚያስችላቸውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ከመሞከር አልቦዘኑም። በተለይ አጋር ፍለጋው የጦፈ ነበር።  እንግሊዝ ክብሯንም፣ ጥቅሟንም ለማስጠበቅ የክት ያለችው ጦርነቷ ነበር ማለት ይቻላል።

“በፍልስጤም ድራማ” ዙሪያ አንደኛው የዓለም ጦርነት የራሱን ቁልፍ ሰዎች፣ ረቂቅ የስምምነት ሰነዶችን እና ምስቅልቅሎችን ወልዷል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመሩትን የሁለቱንም ንቅናቄዎች (የአረባዊነት እና ፅዮናዊነት) ተስፋዎች እና ህልሞች በማበላሸት ወይም በማረጋጋት ረገድ የኃያላኑ፣ በዋናነት የታላቋ ብሪታኒያ ትወና፣ የፍልስጤምን ግጭት ወራሽ ሁለት ቡድኖችን ፈጥሯል።

በዲፕሎማሲያዊ ወይም በስትራቴጂያዊ ምክንያቶች ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሰነዶች በ1907 እና በ1910 ዓ.ም መካከል ባለው ጊዜ ተፈጥረዋል። እነዚህ በአይሁድ አረብ የግጭት መዝገበ ቃላት ውስጥ መሰረታዊ ስፍራ የያዙ ሰነዶች ናቸው። እነርሱም የማክማሆን-ሁሴን ደብዳቤዎች (1907)፣ የሳይኮስ-ፒኮት ስምምነት (1908)፣ የባልፈር አዋጅ (1909) ይጠቀሳሉ። የዛሬውን የቀጣናውን ግጭት መሰረታዊ ምክንያቶች ለመገንዘብ እነዚህን  ሰነዶች አንድ በአንድ ባጭሩ መመልከት ይገባል።

ቱርክ ከሕብረ ብሔሩ ሀገራት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፋ አንደኛውን የዓለም ጦርነት በታህሣሥ ወር 1906 ዓ.ም መቀላቀሏ የኦቶማን ኢምፓየርን መፃኤ እድል ትኩረት ውስጥ አስገባው። ቱርኮቹን አንገት ለማስደፋት እንግሊዝ የሀምሻይት ቤተሰብ መሪ በሆነው፣ በመካው ሸሪፍ ሁሴን በተባለ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ በኩል አረቦችን ለማግባባት ተዘጋጀች። ይህም የማግባባት እንቅስቃሴ የማክማሆን-ሁሴን የደብዳቤ ልውውጥ በመባል ይታወቃል።

የደብዳቤዎቹ ልውውጥ በመካው ሸሪፍ ሁሴን እና በግብፅ እንዲሁም በሱዳን የእንግሊዝ ከፍተኛ ኮሚሽነር በነበረው ሰር ሄንሪ ማክማሆን መካከል የተደረጉ ናቸው። ሸሪፍ ሁሴን በአረቡ ዓለም ውስጥ በጣም ወሳኝ ሰብእና ያለው ከመሆኑም በላይ በአረብ ጉዳይ የማይበገር ተሟጋች ቁልፍ ሰው ነው። የአረቦችን ጥቅም ለማስከበርም ሸሪፍ ከእንግሊዝ ጋር የደብዳቤ ድርድር መጀመሩን ለይላ ሦስተኛው የአረብ እስራኤል ጦርነት በተሰኘ መፅሀፏ አስፍራለች።

መጪውን ዘመን የሚወስኑ የእንግሊዝ እና የአረቦች የደብዳቤ ድርድሮች ከሃምሌ ወር 1907 እስከ ታህሣሥ ወር 1908 ዓ.ም የተለዋወጧቸውን ስምንት ደብዳቤዎች ይዟል። የደብዳቤዎቹ ፅንሰ ሀሳብም እንግሊዝ ለአረቦች ነፃነት ቃል መግባቷ እና ለዚህ ምላሽም ከቱርክ ጋር ለነበረው ጦርነት የአረብ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲኖር የሚገልፅ እንድምታ ያላቸው ነበሩ። የአረብ ሀገርን ወሰኖችም መበየን የቻለ ነበር።

በዚህ መሰረት የመካው ሸሪፍ ሁሴን በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ፣ የአረብ ብሔርተኛ ማህበረሰቦች በጥንቃቄ ያዘጋጁትን የሚከተሉትን ወሰኖች እንደገና የሚያውጅ ምክረ ሀሳብን አቀረበ። በዚህም በሰሜን በመርሲና አዴርና እስከ ፋርስ፣ በምሥራቅ በፋርስ ድንበር አድርጎ እስከ ባዝራ ያለውን፣ በደቡብ ሕንድ ውቅያኖስ እንዲሁም በምዕራብ በኩል እስከ ሙርሲና ድረስ የሜዲትራኒያን ባህር የሚያዋስኑት ክልል አንድ የአረብ ሀገር እንዲባል የሚገልፅ ደብዳቤ ላከ።

በታህሣሥ ወር 1908 ዓ.ም ከእንግሊዙ ማክማሆን ጫን ያለ መልእክት ያለው ደብዳቤ ለሸሪፍ ሁሴን  ደረሰው። “ወሳኙ ነገር ምንም ጊዜ ሳታባክን መላውን የአረብ ሕዝብ ለጋራ አላማችን ማስተባበር እና ለጠላት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳይሰጡ ማሳመን  አለብህ” ሲል ይገልፅ እና የዚህ ስምምነት ተፈፃሚነት እና ጥንካሬ የአረብ ሕዝብ በአስፈላጊው ጊዜ ለእኛ ሊሰጥ በሚችለው ድጋፍ እንደሚወሰን ያሳስባል።

በአጭሩ የእንግሊዝ መንግሥት በእነዚህ የደብዳቤ ልውውጦች ለአረቦች የገባው ቃል በግልጽ ቃላት ሲቀመጥ፦ “ታላቋ ብሪታኒያ የመካው ሸሪፍ ሁሴን ደብዳቤ ያካተታቸው ወሰኖች እና ድንበሮች ላይ ለአረቦች ነፃነት እውቅና ለመስጠት እና ለመደገፍ ተዘጋጅታለች” የሚል ነበር። ፍልስጤም በዚህ ክልል ውስጥ ተካትታ ነበር። እነዚህን በእንግሊዝ መንግሥት የተገቡ ግልፅ ቃል ኪዳኖች መነሻ በማድረግ ነበር በቱርክ ላይ የአረብ አመፅ የተጀመረው።

ይሁን እንጂ ከማክማሆን- ሁሴን ከመጨረሻው የደብዳቤ ልውውጥ ሦስት ወራት በኋላ እና የአረቦችን ውግንና ማግኘቷን ካረጋገጠች በኋላ ለንደን ፊቷን ወደ ሌላኛዋ የሌቫንት ግዛት ተጋሪ ወደ ፈረንሳይ አዞረች። እናም ከፈረንሳይ ጋር አንድ ሌላ ሚስጢራዊ ስምምነት በ1908 ዓ.ም የመፈራረም ርምጃ ወሰደች፤ የሳይከስ – ፒኮት ስምምነት።

የሳይከስ-ፒኮት ስምምነት በሚል የሪሰርች አሶሴት አና ሳዮድላክ ባዘጋጀችው ጽሑፍ ላይ እንደተገለፀው ስምምነቱ ሌቫንትን ለእንግሊዝ እና ለፈረንሳይ የሚከፋፍል ነው። እነዚህ የወሰን መስመሮች እስከዛሬ ድረስ በኢራቅ፣ በዮርዳኖስ፣ በሊባኖስ፣ በፍልስጤም እና በሶሪያ ድንበሮች ላይ ይስተዋላሉ። በእነዚህ አዲስ ወሰኖች የተፈጠረው ፖለቲካዊ እና ዲሞግራፊያዊ ነውጥ ከነፃነት በኋላ የቀጠለ እና ለቀጣናዊ የድንበር ውዝግብ በተለይ በጣም የቅርብ በሆነው የሶሪያ እና ኢራቅ አለመረጋጋት አስተዋፅኦ አድርጓል።

ኦቶማን ኢምፓየር፣ ተጠሪነታቸው ለኮኒስታንቲኖፕል አስተዳደር የሆነ በርካታ አካባቢያዊ አገረ ገዥዎችን የያዘ ነበር። የሳይከስ-ፒኮት ስምምነት ታዲያ ይህን ግዛት ለማዳከም ለየኃያላኑ ሸንሽኗል። በዚህ መሰረት ፈረንሳይ አብዛኛውን የኦቶማን ሶሪያ ግዛትን (ሶሪያን እና ሊባኖስ) እንዲያገኝ ወሰነ፤ ለእንግሊዝ ደግሞ የኦቶማን ሜሶፖታሚያን እና ደቡባዊውን ኦቶማን ሶሪያን (ኢራቅ እና ትራንስ ጆርዳንን) ሰጥቷል። ፍልስጤም  በዓለማቀፍ ደረጃ እንድትተዳደር አስቀምጧል:: ነገር ግን መሬት ላይ የነበረው እውነታ ከ1909-1940 ዓ.ም ድረስ በእንግሊዝ ሞግዚታዊ አስተዳደር ስር መቆየቱ ነበር።

በተጨማሪም በድህረ ጦርነቱ ጊዜም ሩሲያ በቀጥታ ፊርማዋን ባታኖርም ስምምነቱን በመደገፏ የወረረችውን ሰሜናዊ የኦቶማን ግዛት አፅድቆላታል። ስምምነቱ ሕጋዊ ሰውነትን ያገኘው በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ስብሰባ ላይ የተሰጠው የእንግሊዝ የበላይ ጠባቂነት በፍልስጤም እና ትራንስ የጆርዳን ላይ፣ እንዲሁም የፈረንሳይ የሶሪያ እና የሊባኖስ የበላይ ጠባቂነት በ1915 ዓ.ም ነበር።

ስምምነቱ የተደረገው ለንደን ውስጥ በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ መካከል በ1908 ዓ.ም ነበር። ምንም እንኳ በይፋ የሚታወቀው የትንሹ እስያ ስምምነት ተብሎ ቢሆንም፣ በተለምዶ የሚጠራበትን ስሙን የወሰደው ከዋና ተደራዳሪዎች ስም፣ ማለትም ፍራንኮይስ ጆርጅስ ፒኮት ከተባለው አንድ የፈረንሳይ ዲፕሎማትነት እና የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ፖለቲከኛ እና የዲፕሎማሲ አማካሪ፣ ሰር ማርክ ሳይከስ  ነው።

ስምምነቱ ውስብስብ የሀይል የበላይነት ትግል ነው። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ላይ ጀርመን እና የኦቶማን ቱርክ ኅብረት መፍጠር በአውሮፓ ውስጥ ባሉት ጥምር ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ስጋት ጋርጧል። በመሆኑም እንግሊዞች ለመካው ሸሪፍ ሁሴን ቢን አሊ ከኦቶማን ኢምፓየር መፈራረስ በኋላ የአረብ ነፃነትን እንደምትሰጥ ቃል በመግባት በኦቶማን ኢምፓየር ላይ የአረብ አመፅ እንዲካሄድ አበረታታች። በተመሳሳይ ሁኔታም የእንግሊዝ ካቢኔ ሚኒስትሮች ጎን ለጎን ለአይሁዶች ሀገር ለመፍቀድ እየሰሩ ነበር። የሳይከስ-ፒኮት ስምምነት ከአወዛጋቢ የስምምነት ጋጋታዎች አንዱ ሆነ፤ ሁሉም ስምምነቶች ከፖለቲካ እና ኢምፔሪያል መነቃቃት  በተቃራኒው የተቀረፁ ናቸው።

ጀርሚ ፕረስማን፣ ኤ ብሪፍ ሂሰቶሪ ኦፍ ዘ አረብ ኢስራኤል ኮንፍሊክት፣ በተሰኘ መፅሀፉ ላይ እንዳሰፈረው፣ 1909 ዓ.ም የክረምት ወቅት ላይ የእንግሊዝ መንግሥት የፅዮናዊነት ንቅናቄን እንደ ሌላ የጦርነቱ አጋር አድርጎ መመልከት ጀምሮ ነበር። የእንግሊዝ መንግሥት “የጨነቀው…” እንዲሉ ለጦርነቱ እስከጠቀም ድረስ ማንኛውንም ነገር ለመጨበጥ ጉጉቱ ከፍ ያለ ነበር። በውጤቱ፣ እ.አ.አ ኖቬምበር 2 ቀን 1917 የብሪቲሽ ፂዮናዊነት ፌዴሬሽንን እርግጥ  ያደረገው የባልፈር ድንጋጌ ነበር።

“የክቡርነታቸው መንግሥት የአይሁድ ሕዝብ በፍልስጤም ምድር አንድ ብሄራዊ ሀገር  መመስረት  ይደግፋል፤ እናም ይህ አላማ እንዲሳካ የተሻለ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ያመቻቻል፤ በፍልስጤም የሚኖሩ አይሁድ ያልሆኑ ማህበረሰቦችን የሲቪልና ሀይማኖታዊ መብቶች ወይም  የአይሁድ ማህበረሰብን በሌሎች ሀገራት ያገኟቸውን መብቶች እና ፖለቲካዊ አቋማቸውን የሚጎዳ ምንም ነገር የማይደረግ መሆኑ በግልፅ የታወቀ ነው።”

ይህ የሆነው የእንግሊዝ ሠራዊት ኢየሩሳሌም ከገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነበር። ይህም አረቦችን ያስከፋ ሀያላኑ በፍልሥጤም መሬት ላይ የሠሩት ድራማ አንዱ እና ቀጣናውን ወደ ለየለት ግጭት የመራ ነው።

በተለያዩ ጊዜያት የታላቋ እንግሊዝ መንግሥት ከአረቦች እና ሌሎች አጋሮቹ ጋር ያደረጋቸው ርስ በርስ የሚጣረሱ ሰነዶች እስካሁን አካባቢው ለገባበት ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል። ሁለቱም ቃል በተገባላቸው መሰረት ለጦርነቱ የከፈሉለትን መስዋእትነት ፍሬውን ሊቀበሉ ሲዘጋጁ የጠበቁት እና መሬት ላይ የነበረው እውነታ አለመጣጣም ተስፋቸውን እንደገና አጨለመው።

የአረብ ሕዝብ የጠበቀው የራሱን ባህል፣ ታሪክ እና እምነት የመሰለ አስተዳደር እንዲገነባ እና አንድነቱን እንዲጠብቅ የተገለሉት ቃል ኪዳኖች ሁሉ ከሸፉበት። አረቦች በአያሌ የወሰን ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ መንገድ ጠርገዋል።

ከ1930ዎቹ ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ የአረብ ብሔርተኞች የሳይከስ-ፒኮት ምስጢራዊ ስምምነትን አንደ አንድ የምዕራባውያኑ ደባ በመግለፅ የተቃውሞ ጥሪ አሰምተዋል። ምእራባውያኑ የአረቦችን በአንድ ሀገር ውስጥ የመዋሃድ ተፈጥሯዊ ዝንባሌያቸውን ማኮላሸቱን አስተጋብተዋል። በተጨማሪም እስራኤልን እንደ ሀገር እንድትመሰረት ረድቷል:: አንድ ወቅት የቀድሞው የግብፅ መሪ ገማል አብድል ናሰር፣ “በአረቡ ዓለም እምብርት ላይ የተሰነቀረ ጩቤ” ሲሉ አስቀምጠውታል።

ከ1970ዎቹ እስከ አሁኑ ወቅት ድረስ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች፣ በተለይ ከአልቃኢዳ እና ከአሁኑ አይ ኤስ አይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ የእስላሙን ዓለም ለማዳከም እና ለመከፋፈል የምእራባውያን ሴራ እንደሆነ በፕሮፓጋንዳቸው አካትተው የሚጠቅሱት “የስይከስ-ፒኮትን ወሰኖችን” ነው።

እንግሊዝ ለአረቦች ነፃነት ከገባችው ቃል ጎን ለጎን ለእስራኤል ሀገርነት ቃል የገባችው የባልፈሩ ስምምነት በኋላ ላይ ማጣፊያው እስኪያጥራት ድረስ ለእስራኤል እና ለአረቦች ማባሪያ ያልተገኘለትን የፍልስጤም ግጭትን አውርሳቸው ገለል ብላለች። ሁለቱ ወገኖች እስከዛሬ ድረስ የሚጋጩት በዚህ የምእራባውያኑ የፍልስጤም ድራማ መዘዝ ነው።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here