ፍትሐዊነት ወይስ ጠቅላይነት?

0
33

“የማይታየው እጅ” የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በምጣኔ ሀብታዊ ትንታኔዎች ተደጋግሞ ይነሳል:: የጽንሰ ሐሳቡ ጠንሳሽ ደግሞ የዘመናዊ ምጣኔ ሀብት (Modern Economics) አባት የሚባሉት አዳም ስሚዝ ናቸው:: ጽንሰ ሐሳቡ በነፃ እና ተወዳዳሪ ገበያ ውስጥ በሸቀጦች አቅርቦት እና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ራስን የመቆጣጠር ሂደት ሃብትን በብቃት ለመመደብ ያስችላል፣ ይህም የተሻለ ዕድገትን ያመጣል የሚል ዕይታ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የነጻ ገበያ ምንነትን በተመለከተ የዘርፉ ምሁራን የተለያዩ ብያኔዎችን ቢሰጡትም በእጅጉ በተገደበ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የዕቃዎች እና የአገልግሎቶች ዋጋ በገዢዎችና በሻጮች ፈቃደኝነት የሚወሰንበት የምጣኔ ሀብት ሥርዓት ነው የሚለው አብዛኛዎቹን ያስማማል።

ውጤታማ የሀብት ክፍፍል፣ ፈጠራ እና ጥራት፣ የሸማቾች ምርጫ እና እርካታ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እና የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲሁም የግለሰቦችን ነፃነት እና ኃላፊነት ማረጋገጥ የሚሉትም ዓላማዎቹ ናቸው።

በሌላ በኩል በነጻ ገበያ አተገባበር፣ ፋይዳ እና መሰል ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ምሁራን ተመሳሳይ ሐሳብ የላቸውም:: ገሚሱ ሐሳቡን ሙሉ ለሙሉ በመደገፍ የዓለማችንን ሕዘብ ፍትሐዊ ተጠቃሚ በማድረግ እኩልነትን ያሰፍናል ባይ ናቸው:: ቀሪዎቹ ደግሞ ሐብትን በተወሰኑ ፈርጣማ ሰዎች እና ድርጅቶች እጅ እንዲሆን በማድረግ ሕዝብን ያጎሳቁላል ሲሉ ይከራከራሉ::

ነፃ ገበያ እና ውዝግቦቹ

የተለያዩ ምሁራን ስለ ነፃ ገበያ ሥርዓት ደጋፊ እና ተቺ ሐሳቦችን (ክርክሮችን) አቅርበዋል። የዘርፉን ዕውቅ ምሁር አዳም ስሚዝን ጨምሮ ሚልተን ፍሪድማን እና ፍሬድሪክ ሃይክ ያሉ ደጋፊዎች የነፃ ገበያን ውጤታማነት እና ከግል ነፃነት ጋር ያለውን ግንኙነት አፅንዖት በመስጠት ስለ አስፈላጊነቱ ይከራከራሉ:: እንደ ካርል ማርክስ እና ጆን ሜይናርድ ኬይንስ ያሉ ተቺዎች ደግሞ ነፃ ገበያ ውስጣዊ አለመረጋጋትን፣ ኢ – እኩልነትን እና ብዝበዛን ያስከትላል ሲሉ ይተቻሉ።

ፍሬድሪክ ሃይክ “ነፃ ገበያ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ግለሰቦች እጅ የሚገኘውን የተበተነ እና ተጨባጭ ዕውቀት ለመጠቀም ብቸኛው ውጤታማ መንገድ ነው“ በማለት ነው የሚያስገነዝበው።

ነጻ ገበያ ለፖለቲካዊ ነጻነት መሠረት ወይም ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው በማለት የነጻ ገበያን አስፈላጊነት የሚያስገነዝበው ደግሞ ሚልተን ፍሪድማን የተባለው ምሁር ነው። በፈቃደኝነት ልውውጥ ላይ የተመሠረተ ነፃ ገበያ አምባገነናዊ የሥልጣን ክምችትን ይከላከላል ሲልም ነው አስረጂ ሐሳብ የሚያቀርበው።

በተመሳሳይ 40ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የቀድሞው የሆሊውድ ተዋናይ እንዲሁም በአሜሪካ ወግ አጥባቂ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበሩት ሮናልድ ሬገን የነጻ ገበያን አስፈላጊነት በእጅጉ የሚያምኑ ናቸው:: “ዕድገት፣ ብልጽግና እና የሰዎች ፍላጎት የሚሟላው ከታች ወደ ላይ እንጂ ከላይ /ከመንግሥት/ ወደ ታች አይደለም” የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው:: ይህ ሁሉ የሚሳካው ታዲያ ነጻ ገበያን በሚከተል ነጻ ማሕበረሰብ ነው ባይ ናቸው።

በሌላ በኩል ታዋቂው የሶሻሊዝም አቀንቃኝ ካርል ማርክስን ጨምሮ ነጻ ገበያ ገበያን የማያረጋጋ፣ ሠራተኞችን የሚበዘብዝ፣ ሀብትንም በተወሰኑ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንዲከማች የሚያደርግ ነው በማለት በርካቶች ይተቹታል:: ካርል ማርክስ ደግሞ ቀዳሚው ሲሆን ነጻ ገበያን ሠራተኛን በመበዝበዝ የገቢ እና የሃብት ልዩነትን ያስከትላል የሚለው ዋነኛ መከራከሪያ ሐሳቡ ነው። ትርፍን ብቻ በማሳደድ ሰዎችን እና አካባቢያቸውን ወደ ሸቀጥነት ይቀይራል የሚል አቋምም ነበረው።

ጆን ሜይናርድ ኬይንስ የተባለው ምሁር ደግሞ ነጻ ገበያ ለገበያ አለመረጋጋት ምንጭ መሆኑን ያነሳል:: ነፃ ገበያ በአጠቃላይ ለድቀት (Recessions) እና ለምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች (Depressions) የተጋለጠ ነው ባይ ነው።

የነጻ ገበያ በረከቶች

የነጻ ገበያ ዋና ጠቀሜታ የሀብት ክፍፍልን በብቃት መምራት መቻሉ ሲሆን ይህም ፈጠራን እና  የሸማቾችን ምርጫ ያበረታታል።

ቅልጥፍና እና የሀብት ክፍፍል፣ ፈጠራ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት፣ የሸማቾች ምርጫ እና ዝቅተኛ ዋጋ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ነፃነት፣ የሀብት ክምችት (ሥርዓቱ ግለሰቦች ሀብት እንዲፈጥሩ እና የላቀ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ትልቅ ዕድሎችን ይሰጣል) እና ተያያዥ ነገሮች የነጻ ገበያ ሥርዓት አበርክቶዎች ናቸው።

የነጻ ገበያ አሉታዊ ጎኖች

የገቢ አለመመጣጠን እና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሁም ለማኅበራዊ ደህንነት በቂ ትኩረት አለመስጠቱ የነጻ ገበያ ዋነኛ  ጉዳቶች ስለመሆናቸው ሪሰርች ጌት ላይ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል:: መረጃው እንዳብራራው የገቢ የገበያ ውድቀቶች እና የውጭ ተጽዕኖዎች (Externalities)፣ ሞኖፖሊ (ብቸኛ የገበያ ተቆጣጣሪነት)፣ የመንግሥት ቁጥጥር እጦት የሥርዓቱ ችግሮች መሆናቸውን ያነሳል፤ በተለይ ብቸኛ የገበያ ተቆጣጣሪነት ከፍተኛ ዋጋ እንዲያስከፍሉ እንዲሁም ውድድርንና ፈጠራን እንዲገድቡ የሚያደርግ ነው በሚል ነው የሚተቸው።

ደካማ የሥራ ሁኔታዎች እና ሥራ አጥነት፣ የምጣኔ ሀብት አለመረጋጋት፣ የገበያ ውድቀቶች፣ የማኅበራዊ ደህንነት እጦት እንዲሁም  ለችግር ተጋላጭነት የነጻ ገበያ ተጨማሪ ጉዳቶች (አሉታዊ ጎኖች) ናቸው።

ነጻ ገበያ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት

የነፃ ገበያ ፖሊሲዎች ትክክለኛ ስኬት እንደየሀገራቱ ደንብ አተገባበር ሁኔታ ይወሰናል። የሚከተሉት ደግሞ በተለይ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የነጻ ገበያ አበርክቶዎች መሆናቸውን ሪሰርች ጌት ይዘረዝራል::

የተሻለ አገልግሎትን በመስጠት ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ለማስገኘት ያስችላል የሚለው ቀዳሚው አበርክቶ ነው:: በአቅርቦትና ፍላጎት የሚመራ በመሆኑም ጤናማ ፉክክርን ያበረታታል፣ ይህም ፈጠራን ይገፋፋል። ጤናማ ፉክክር (ውድድር) በማምጣት ምርታማነትን ያሳድጋል።

ለሸማቾች የላቀ ምርጫ እና ዝቅተኛ ዋጋ እንዲኖር ማስቻሉም የመረጃ ምንጩ ያነሳው ሌላው አበርክቶ ነው፤ ይህ ደግሞ በድርጅቶች መካከል በሚኖረው ጤናማ ፉክክር ምክንያት ለሸማቾች ሰፊ ምርጫን በመስጠት ጥራት ያላቸው ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገኙ ያደርጋል።

በተመሳሳይ ነጻ ገበያ በተለይ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን ለማበረታታት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ነው ያስቀመጠው።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸው ዝቅተኛ ነው፤ ነጻ የንግድ ተግባራዊነት ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ እንዲሁም በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ነው የሪሰርች ጌት መረጃ ያመላከተው።

የመንግሥት ሚና

የነጻ ገበያ ተቺዎች እንደሚያነሱት ዘርፉ በአግባቡ ካልተመራ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ያስከትላል፤ ይህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊ ቀውስን ያስከትላል::

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እጅግ ውስን ቢሆንም ሊያከናውናቸው የሚገቡ ቁልፍ ተግባራት አሉ:: በዋናነት የንብረት መብቶችን መጠበቅ፣ ውሎችን እንዲሁም ሕጎችን ማስፈጸም እና ፍትሐዊ ውድድርን ማረጋገጥ የመንግሥት ቁልፍ ተግባራት ናቸው።

ጤናማ ውድድርን በማስጠበቅ ፍትሐዊ ውድድርን ማስፈን፣ የውጭ ተጽዕኖዎችን (አፍራሽ ጣልቃ ገብነቶችን) መከላከል፣ ገቢን በፍትሐዊነት ማከፋፈል  እንዲሁም ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እንዲሁም ገበያን ማረጋጋት የነጻ ገበያ ሥርዓት የሚፈልጋቸው የመንግሥት ተግባራት ናቸው።

ከሀገራት ምን እንማር?

የነጻ ገበያ አሠራርን በመተግበር የተሞክሮ ማዕከል የሆኑ ሀገራት አሉ፤ ለአብነትም አሜሪካ ባለ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት እንድትሆን ያስቻላት የነጻ ገበያ ሥርዓት መሆኑን ሪሰርች ጌት ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፤ ሲንጋፖር፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ፣ አየርላንድ፣ ታይዋን እና የስካንዲኔቪያ ሀገሮች በምሳሌነት የተጠቀሱ ሀገራት ናቸው።

መረጃው አክሎም አሜሪካ በብዙዎቹ የምጣኔ ሀብታዊ ነጻነት መለኪያዎች ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች፤ ሲንጋፖርም ዝቅተኛ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ ዝቅተኛ ግብር፣ ጠንካራ የንብረት ባለቤትነት መብቶች እና ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የንግድ አካባቢ መፍጠሯ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል።

ኢንዶነዢያን ደግሞ “ነጻ ገበያን በማረጋገጥ ድምጿን አጥፍታ እየተመነደገች ያለች ሀገር” ብሏታል።

ሌሎች በአርዓያነት የተጠቀሱ ሀገራትም (እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ፣ አየርላንድ፣ ታይዋን እና የስካንዲኔቪያ ሀገሮች) ተመሳሳይ አተገባበርን በማስፈናቸው በነጻ ገበያ ምሳሌ መሆን የቻሉ ስለመሆናቸው ነው የጠቀሰው።

ዝቅተኛ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ ዝቅተኛ የታክስ ምጣኔ፣ ለንግድ ምቹ የሆኑ ደንቦችን እና ሕጎችን በማውጣት መተግበር፣ ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል መኖር እና ጠንካራ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ መኖር ለሀገራቱ ውጤታማነት ምሰሶዎች ናቸው።

እንደ መውጫ

በሀገራችን ነጻ ገበያን ለማስፈን ደንቦች እና ሕጎች ወጥተዋል፤ ተግባራዊም እየተደረጉ ነው፤ ይሁን እንጂ የአተገባበር ክፍተቶች የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው። ወቅትን እየጠበቁ ምርትን መደበቅ፣ ያልተገባ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ይህን በሚያደርጉ ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ አለመውሰድ ችግሮች ናቸው፤ ይህም የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ አድርጓል::

የሕግ አንቀጽ

 

የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006

 

የንግድ እና የግብይት አሠራሩ ላይ የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር እና ተግባራት፣ በኢ-ፍትሐዊ የንግድ ተግባር፣ የጥራት መጓደል፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና ለጤና ጎጅ የሆኑ ምርቶችን እንዲሁም ለአገልግሎቶች የሚጠየቅን የተጋነነ ዋጋ ለማስቀረት የወጣ አዋጅ ነው።

የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ እና ነጻ የገበያ ውድድር ለመፍጠር ተሻሽሎ የወጣው የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006

ጸረ ውድድርና ሕገ ወጥ የገበያ ተግባራትን በማስቀረት ነጻ ገበያን ማስፈን፣

ሸማቹ ላይ ደኅንነታቸው እና ለጤንነት ተስማሚ የሆኑና ለወጣባቸው ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል፣

ምጣኔ ሀብታዊ ልማትን (ዕድገትን) ማፋጠን የሚሉት ዋና ዋና ዓላማዎቹ ናቸው።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የሕዳር  22 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here